ሪፖርት | አዞዎቹ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል

አዞዎቹ በቡታቃ ሸመና ብቸኛ ግብ ስሑል ሽረን በመርታት ተከታታይ ድላቸውን አሳክተዋል።

ስሑል ሽረ በ14ኛ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ካስተናገዱበት ቋሚ አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ዊሊያም ሰለሞን እና ፋሲል አስማማውን አሳርፈው በምትካቸው ክፍሎም ገ/ህይወት እና አሌክስ ኪታታን ይዘው ሲገቡ አርባምንጭ ከተማዎች በበኩላቸው አዳማ ከተማን ካሸነፉበት ቋሚያቸው ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ገብተዋል።


ከሽንፈት እና ከድል የተመለሱ ቡድኖችን ያገናኘው የ15ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በርከት ያለ የግብ ማግባት እድሎችን የተፈጠሩበት ነበር።

ስሑል ሽረ ኳስ እያንሸራሸሩ አዞዎቹ ላይ ብልጫ ለመውሰድ ሲጥሩ አዞዎቹ በበኩላቸው የግብ ማግባት ሙከራ አጋጣሚችን በመፍጠር ረገድ የተሻሉ ነበሩ ፤ በዚህም በ5ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን ላይ በተሰራ ጥፋት ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ የቆመ ኳስ አግኝተው ካሌብ በየነ ወደ ግብ በቀጥታ መቶ ለትንሽ በግቡ አግዳሚ በኩል ያለፈችበት እንዲሁም በ10ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ አህመድ ሁሴን ርቀት ላይ ሆኖ አክርሮ የመታውን ኳስ የስሑል ሽረው ግብ ጠባቂ ፋሲል ገ/ሚካኤል የመለሰበት አጋጣሚ ይታወሳሉ።

ጨዋታው ቀጥሎ ወደ ሁለቱም ቡድኖች በፈጣን ኳሶች ወደ ግብ ሲደርሱ ብንመለከትም ጥራታቸው የላቁ ሙከራዎችን ግን በብዛት አልተመለከትንም።

32ኛው ደቂቃ ላይ አዞዎቹ ሌላኛውን አደገኛ ለግብ የቀረበ ሙከራ አህብዋ ብረያን አማካኝነት አድርገዋል። አህመድ ሁሴን በመስመር በኩል ኳስ ይዞ ገብቶ ያሻገረለትን ኳስ ግንባሩ አህብዋ ገጭቶ የሞከራት ኳስ ለጥቂት ዒላማዋን ሳትጠብቅ ቀርታለች።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ ቡድኖች ልክ እንደመጀመሪያ አጋማሽ ወደፊት እየገሰገሱ ሲቀጥሉ አዞዎቹ የግብ እድል በመፍጠር ረገድ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን በዚህም በ50ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን ጥሩ አጋጣሚ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በጨዋታው አልፎ አልፎም ቢሆንም ወደፊት በመሄድ ጥረቶችን ሲያደርጉ የነበሩት አዞዎቹ የጥረታቸው ውጤት የሆነችዋን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። በ74ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ካሌብ በየነ ያሻማውን ኳስ ቡታቃ ሸመና በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

ግብ ከተቆጠረ በኋላ በሂደት ጨዋታው ግለቱ እየጨመረ ሲሄድ ስሑል ሽረ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር አዞዎቹ ደግሞ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት በሚያደርጉት እንቅሰቃሴ የጨዋታ እንቅስቃሴ ሳቢ እየሆነ መቀጠሉን አስተውለናል። 

ጨዋታው ወደመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃ ሲያመራ የስሑል ሽረዎች ጫና እየበረታ የአዞዎቹን ተከላካይ መስመር ላይ በተደጋጋሚ ጥቃቶች ቢሰነዝሩም አዞዎቹ ነጥባቸውን ለማስጠበቅ ወደኋላ አፈግፍገው ኳሶቹን ከግብ ክልላቸው አከባቢ በረጅሙ እያራቁ መከላከሉ ላይ አተኩረው ቀጥለዋል።

ምንም እንኳን የስሁል ሽረዎች ጫና ቢበረታም የአዞዎቹ የተከላካይ መስመር ጥንካሬ ጫናዎቹን በመቋቋም ተልዕኮ ላይ በማተኮሩ ጨዋታው ሌላ ግብ ሳያስመለከት ለአዞዎቹ ሶስት ነጥብ በማጎናፀፍ ተቋጭቷል።