በ15ኛ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት የሚከናወኑ ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ወላይታ ድቻ ከ ሲዳማ ቡና
የቅርብ ተፎካካሪዎች እና በደረጃ ሰንጠረዡ ተከታትለው የተቀመጡትን ቡድኖች የሚያገናኘው መርሀ-ግብር ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።
በመጨረሻው መርሀ-ግብር ወልዋሎን በማሸነፍ ከአምስት ሳምንታት በኋላ ከድል ጋር የታረቀው ወላይታ ድቻ ከሰባት ሽንፈት አልባ የጨዋታ ሳምንታት በኋላ በመድን ከገጠመው ሽንፈት አገግሞ ያገኘውን ሦስት ነጥብ ዳግም ነገም ለማግኘት ጠንካራውን ፈተና ማለፍ ይጠበቅበታል።
በውድድር ዓመቱ መጀመርያ ከሊጉ መሪዎች ጎራ የነበረው ወላይታ ድቻ በተከታታይ ድል ካደረገባቸው ጨዋታዎችን በወጥነት አለመዝለቁ ነው እንጂ ከሦስተኛ ጀምሮ እስከ አምስተኛ የጨዋታ ሳምንት ድረስ በውጤትም ሆነ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ዕድገት እያሳየ ሳይጠበቅ ተፎካካሪ ሆኖ ነበር።
ከዛ በኋላ ግን ለሳምንታት ድል ሳያደርግ መዝለቁ መጠነኛ የውጤት መፋዘዝ አጋጥሞታል።
በውድድር ዓመቱ አስራ ስድስት ግቦች መረብ ላይ ያሳረፈው ወላይታ ድቻ በሊጉ በርከት ያሉ ግቦች ካስቆጠሩ ሦስት ክለቦች አንዱ ነው። ቡድኑ ግቦችን ለማስቆጠር የማይሰንፍ ጥሩ የፊት መስመር ጥምረት መገንባት ቢችልም በርከት ያሉ ግቦች በማስተናገድ ረገድ ፊት ላይ ከተቀመጡ ሦስት ክለቦች አንዱ ነው። በእርግጥ ወላይታ ድቻ ለፈጣን ሽግግር ማሳለጫነት ምቹ በሆኑ ተጫዋቾች የተገነባ ጥሩ የማጥቃት አጨዋወት ያለው ቡድን ቢሆንም በቀጣይነት የመከላከል አደረጃጀቱ በማስተካከል የሚቆጠሩበትን ግቦች መቀነስ ይጠበቅበታል።
አርባምንጭ ከተማ ላይ ድል ከተቀዳጁበት ጨዋታ በኋላ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች በተከታታይ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት ሲዳማ ቡናዎች ከሳምንታት በኋላ ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች አንድ ሽንፈት የቀመሰውን ወላይታ ድቻ ይገጥማሉ። ምንም እንኳን ውድድሩ ሲጀምር በፉክክሩ ውስጥ ግምት ከተሰጣቸው ክለቦች ቢካተቱም እንዲሁም ሊጉን እስከ መምራት ቢደርሱም አሁን ላይ ሲዳማ ቡናዎች ከመሪው በሰባት ነጥቦች ርቀት ላይ ይገኛሉ።ቡድኑ ምንም እንኳ በተከታታይ አምስት መርሀ-ግብሮች አራት ሽንፈት እና አንድ የአቻ ውጤት ካስመዘገበበት ደካማ ብቃት አገግሞ ነጥቦች መሰብሰብ ቢጀምርም የነገው ፍልሚያ ቡድኑ እንዲገኝ ወደ ሚጠበቅበት የፉክክር ደረጃ የሚያስጠጋ እንደመሆኑ በብዙ መልኩ ተሻሽሎ ዳግም ወደ ድል የሚመለስበት ጨዋታ መሆን ይገባዋል።
ሲዳማ ቡናዎች በውጤት ብቻ ሳይሆን በሜዳ ላይ እንቅስቃሴም መነቃቃት አሳይተዋል ፤ በመጨረሻው መርሀ-ግብር የወሰዱት ብልጫም የዚህ ማሳያ ነው። ሆኖም የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ያላቸው ውስንነት በጥራትም ሆነ በጥልቀት ጥሩ የአጥቂ አማራጮች ላሉት ቡድን ደካማ አስመስሎታል።
ወላይታ ድቻ አብነት ደምሴ በጉዳት የማይኖር ሲሆን ግብጠባቂዎቹ ቢንያም ገነቱ እና አብነት ይስሐቅ ወደ ልምምድ ቢመለሱም ለነገው ጨዋታ የማይደርሱ መሆናቸው ሲታወቅ በተመሳሳይ ወደ ልምምድ የተመለሰው መልካሙ ቦጋለ ለነገ ጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ነው። የተቀሩት የቡድኑ አባላት ከቅጣት እና ከጉዳት ነፃ ሆነው ለወሳኙ ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸውን አውቀናል። በሲዳማ ቡና በኩል ብርሃኑ በቀለ ቅጣቱን ጨርሶ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆን ሌሎች የቡድኑ አባላቶችም ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 20 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ ሁለት ጨዋታ ሲያሸንፍ በሰባት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተው ሲዳማ ቡና አስራ አንድ ጊዜ አሸንፏል። በሁለቱ ግንኙነት እስካሁን 32 ጎሎች ሲቆጠሩ ወላይታ ድቻ 11 ፣ ሲዳማ ቡና 24 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ መቐለ 70 እንደርታ
በእኩል ነጥብ በወራጅ ቀጠናው አፋፍ የሚገኙ ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።
በመጀመርያው ጨዋታ በወላይታ ድቻ ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላ ለዘጠኝ መርሀ-ግብሮች ሳይሸነፉ መዝለቅ ችለው የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ሁለት ተከታታይ ሽንፈት ቀምሰዋል።
ከሁለተኛው እስከ አራተኛው ሳምንት ድረስ በተከታታይ ጨዋታዎች መረቡን ያላስደፈረ እና ጠጣር ቡድን ገንብተው የነበሩት አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ውስን መቀዛቀዞች ቢታይበትም አሁንም በመከላከል ጥንካሬያቸው ቀጥለዋል። ቡድኑ ካከናወናቸው አስራ ሁለት ጨዋታዎች በስድስቱ መረቡን ሳያስደፍር መውጣት ቢችልም በግብ ማስቆጠሩ ረገድ የወጥነት ችግር ይታይበታል።
አስር ግቦች አስቆጥሮ በእኩሌታ አስር ግቦች ያስተናገደው ኤሌክትሪክ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ማስቆጠሩም የዚህ ማሳያ ነው።
በነገው ጨዋታም በመጨረሻዎቹ ሦስት መርሀ-ግብሮች መረቡን ያላስደፈረው እና በጠንካራ የመከላከል ቁመና የሚገኘው ቡድን እንደመግጠማቸው በማጥቃቱ ረገድ ያለባቸው ውስንነት ቀርፈው መቅረብ ይኖርባቸዋል።
ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ድል እና ሁለት የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ቀና ያለው መቐለ 70 እንደርታ በእኩል ነጥብ በሁለት ደረጃዎች የሚበልጠውን ኤሌክትሪክ ነገ በመፋለም ከወራጅ ቀጠናው አፋፍ ከፍ ለማለት ድልን እያሰበ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይታመናል።
በውድድር ዓመቱ ሦስት ድሎችን ያስመዘገበው መቐለ 70 እንደርታ በቀጠናው ካሉ ቡድኖች በአንፃራዊነት በተሻለ አራት ሽንፈቶች ማስመዝገብ ቢችልም ከተደጋጋሚ የአቻ ውጤቶች መላቀቅ አልቻለም። በርከት ያሉ የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ በጣምራ ከሚመሩት ድሬዳዋ ከተማ እና ፋሲል ከነማ በአንድ ዝቅ ብሎ በስድስት ጨዋታዎች ነጥብ የተጋራው ቡድኑ ከአደጋው ቀጠና ለመራቅ ተከታታይ ድሎች ማስመዝገብ ግድ ይለዋል።
አደራደራቸው ወደ ሦስት የተከላካዮች ጥምረት ከለወጡ በኋላ ዋነኛ ራስ ምታታቸው የነበረው የመከላከል ድክመት የቀረፉት አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግዱ መውጣት ቢችሉም ባለፉት አምስት መርሀ-ግብሮች ማስቆጠር የቻሉት ግብ አንድ ብቻ ነው። ቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ከጉዳት መልስ ማግኘቱ ጥሩ ዜና ቢሆንም ከምንም በላይ የማጥቃት አማራጮቹ ውስን መሆናቸው ለተጋጣሚ ቡድኖች በቀላሉ የሚተነበይ አድርጎታል። በቅርብ ጨዋታዎች ከመልሶ ማጥቃት ይልቅ በዋናነት የመስመር እንቅስቃሴ ላይ የተገደበ የጎል ምንጭ ለማግኘት ሲጥር የሚታየው ቡድኑ በነገው ጨዋታ ሲከላከል በቁጥር በርከት ብሎ የሚታየውን ቡድን ማስከፈቻ ሁነኛ መላ መዘየድ የሚጠበቅበት ይመስላል።
ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ሐብታሙ ሸዋለምን ከቅጣት መልስ ያገኛሉ። ባለፈው ጨዋታ በጉዳት ያልነበሩት አብዱላዚዝ አማን እና አሸናፊ ጥሩነህም ወደ ሜዳ ይመለሳሉ። በፍቃዱ አስረሳኸኝ እና አብዱላሂ አላዮ ግን አሁንም በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው። የተቀሩት የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጂ ናቸው። በመቐለ 70 እንደርታዎች በኩል ያብስራ ተስፋዬ፣ መናፍ ዐወል፣ አሸናፊ ሀፍቱ፣ ክብሮም አፅብሀ እና አማኑኤል ልዑል በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም። የመድሀኔ ብርሀኔ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።
ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱንም መቐለ 70 እንደርታ አሸንፏል። በግንኙነቱ መቐለ 3 ግቦች ስያስቆጥር ኤሌክትሪክ 1 አስቆጥሯል።