ሪፖርት | ጉሽሚያ የበዛበት ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስራ አምስተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ወላይታ ድቻን ከሲዳማ ቡና ያገናኘው ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።

ወላይታ ድቻዎች ወልዋሎን ካሸነፈው የመጀመርያ አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ለውጥ በማድረግ ምንተስኖት ተስፋዬ በኬኔዲ ከበደ ተተክቶ ወደ ሜዳ ሲገባ በሲዳማ ቡና በኩል ከመቐለ አቻ ከተለያየው ስብስብ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ጊት ጋትኩት በደስታ ዮሐንስ፣ ብርሀኑ በቀለ በአስቻለው ሙሴ፣ ሬድዋን ናስር በፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን እንዲሁም ይገዙ ቦጋለ በመስፍን ታፈሰ ተተክተው ገብተዋል።

ከጅምሩ ጀምሮ በጥፋቶች እና ጉሽሚያዎች ታጅቦ የተካሄደው ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ በአንፃሪዊነት የተሻሉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ታይተዋል። ከነዚህም መካከል በ14ኛው ደቂቃ ፀጋዬ ብርሀኑ ከቀኝ መስመር የመጣውን ኳስ መሬት ሳይወርድ በቮሊ መትቶ በግቡ አግዳሚ ወደ ውጪ የወጣበት በወላይታ ድቻ በኩል ሲጠቀስ ደግፌ ዓለሙ በ30ኛው እና በ31ኛው ደቂቃ ከግራ የሜዳው ክፍል ሞክሮ በግብ ጠባቂው የተያዘበት እና ወደ ውጪ የወጣበት ኳሶች በሲዳማ ቡና በኩል የሚጠቀሱ ናቸው።

ከእረፍት መልስ ተመሳሳይ ይዘት ያለው የጨዋታ እንቅስቃሴ የቀጠለ ሲሆን በሁለቱም በኩል ከቆሙ ኳሶች የግብ እድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በዚህም በ72ኛው ደቂቃ ብርሀኑ በቀለ ከግራ መስመር ሲዳማ ቡናዎች ያገኙትን የቅጣት ምት በቀጥታ መትቶ ወደ ውጪ ሲወጣበት 85ኛው ደቂቃ ላይ ድቻዎች ያ ኙት የማዕዘን ምት ተሻምቶ ውብሸት በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

በተመሳሳይ 88ኛው ደቂቃ ላይ በሲዳማ በኩል ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ደስታ ደሙ ሞክሮ በግቡ ቋሚ የወጣበት እንዲሁም ተቀይሮ የገባው ማይክል ኪፕሮቪ ከቀኝ መስመር በግራ እግሩ ጥሩ ኳስ ሞክሮ ወደ ግብነት ሳይቀየር ጨዋታው ያለ ግብ ተጠናቋል።