መረጃዎች| 60ኛ የጨዋታ ቀን

በ15ኛው ሳምንት 3ኛ የጨዋታ ዕለት የሚከናወኑ ተጠባቂ መርሀ-ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!

ሀድያ ሆሳዕና ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ነብሮቹ ግስጋሴያቸው ለማስቀጠል ሀምራዊ ለባሾቹ ደግሞ ከሳምንታት ጥበቃ በኃላ ያገኙት ድል አስቀጥለው ከወራጀ ቀጠናው ለመራቅ ብርቱ ፍልሚያ ይደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከስድስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ መጋራታቸውን ተከትሎ መሪነታቸውን ያስረከቡት ነብሮቹ በሰንጠረዡ አናት የሚያደላድላቸውን ድል ፍለጋ ሻምፕዮኖቹን ይገጥማሉ።

ነብሮቹ ባለፈው ሣምንት ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ላይ የማጥቃት እንቅስቃሴ እና የፈጠሩት የግብ ዕድል ከሌላው ጊዜ በአንፃራዊነት ያነሰ ነበር። በነገው ዕለትም በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ለመውሰድ አቅደው ከሚገቡት ንግድ ባንኮች ጋር በምን መንገድ ይቀርባሉ የሚለው የሚጠበቅ ነው። በውድድር ዓመቱ ስምንት ግቦች ብቻ ያስተናገዱት ሀድያ ሆሳዕናዎች ከኢትዮጵያ መድን እና ባህርዳር ከተማ በመቀጠል ጥቂት ግቦች ያስተናገደ ክለብ ነው። ቡድኑ በውድድር ዓመቱ ስምንት ግቦች ብያስተናግድም ከተቆጠሩበት ግቦች ውስጥ ስድስቱ በሦስት ጨዋታዎች ብቻ የተመዘገቡ ናቸው። በሰባት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር የወጣው የነብሮቹ የኃላ ክፍል በነገው ዕለትም በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረ ቡድን እንደመግጠማቸው ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል ተብሎ አይጠበቅም፤ ሆኖም በመጨረሻው ጨዋታ በወሳኝ ተጫዋቾች ጉዳት ምክንያት ውስን መቀዛቀዝ የታየበት የፊት መስመር መሻሻል የሚገባው የቡድኑ ክፍል ነው።

ባለፈው የውድድር ዓመት የሊጉ ክብር ያነሳው እና ከሊጉ ምርጥ ቡድኖች አንዱ የነበረው ንግድ ባንክ ዓምና ከነበረበት ስኬት አንጻር ዘንድሮ በላይኛው የሰንጠረዡ ክፍል ቢጠበቅም ሳይታሰብ በአደጋው ክልል ይገኛል።

ንግድ ባንክ ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ድል አድርጎ መጠነኛ እፎይታ ማግኘት ቢችልም ከወራጅ ቀጠናው ይበልጥ ለመራቅ ተከታታይ ድሎች ማስመዝገብ ይኖርበታል። ለአራት የጨዋታ ሳምንታት ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኖት ከቆየ በኋላ በመጨረሻዎች ሁለት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ያስቆጠረው የአሰልጣኝ በፀሎት ልዑል ሰገድ ቡድን በውጤት ረገድ ፈታኝ ወቅት ላይ ቢገኝም የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ግን ለክፉ የሚሰጥ አይደለም። በወራጅ ቀጠና የሚገኘው ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ወደ ግብ ማስቆጠሩ ከመመለሱም ባለፈ ድል ማስመዝገብ ቢችልም የደረጃውን አናት ለመቆጣጠር በትልቅ ተነሳሽነት ከሚገቡት ነብሮቹ ጋር የሚጠብቃቸው ፈተና ቀላል እንደማይሆን ይጠበቃል።

በሀድያ ሆሳዕና በኩል ተመስገን ብርሀኑ፣ ጫላ ተሺታ፣ መለሰ ሚሻሞ፣ በረከት ወንድሙ እና ዳግም ንጉሴ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው። እዮብ አለማየሁ እና ብሩክ ማርቆስ ግን ከጉዳታቸው አገግመው ለነገው ጨዋታ የሚደርሱ ይሆናል።በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ፉአድ ፈረጃ እና ሱሌማን ሀሚድ ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው እንዲሁም ዮናስ ለገሰ በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን የተቀሩት የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።

ቡድኖቹ በሊጉ አራት ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3 አሸንፎ 4 ጎሎችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን በአንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል፤ ሀድያ ሆሳዕና በግንኙነቱ ግብ ማስቆጠር አልቻለም።

ባህርዳር ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን

በጨዋታ ሳምንቱ በጉጉት ከሚጠበቁ መርሀ-ግብሮች አንዱ የሆነው ባህርዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን የሚያገናኘው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ሀያ ሦስት ነጥቦች ሰብስበው ከመሪው በሦስት ነጥብ ርቀት ላይ የሚገኙት የጣና ሞገዶቹ ከመሪዎቹ ጎራ ሆኖ ለመቀጠል እና ደረጃቸው ለማሻሻል በነገው ጨዋታ ድል ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ባህርዳር ከተማዎች አንድ ተጨማሪ ጨዋታ ከመጫወታቸው ውጭ በብዙ ቁጥራዊ ነገሮች ከነገው ተጋጣሚያቸው በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። ተጋጣሚያቸው በውድድር ዓመቱ አራት ግቦች ብቻ በማስተናገድ ጥቂት ግቦች የተቆጠሩበት ቡድን ሲሆን የጣና ሞገዶቹም በአንድ ግብ ብልጫ በሁለተኛነት ተቀምጠዋል፤ በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ብናይም በቡድኖቹ መሀከል ያለው ልዩነት ሁለት ብቻ ነው። ይህንን ተከትሎም ጨዋታው ተቀራራቢ እና ጠንካራ ፍልምያ ይደረግበታል ተብሎ እንዲጠበቅ ያደርገዋል።

የጣና ሞገዶቹ ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ ድል መመለሳቸው እንደ አወንታ የሚነሳላቸው ነጥብ ቢሆንም አንዴ ሞቅ አንዴ ደግሞ ቀዝቀዝ የሚለው የፊት መስመራቸው ጥንካሬ በዘላቂነት መፍታት ይኖርባቸዋል። የነገው ተጋጣሚያቸውም የሊጉ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድን እንደመሆኑ ከሌላው ጊዜ በተለየ የአፈፃፀም ደረጃ መቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

በአዳማ ከተማ ቆይታቸው ካከናወኗቸው ሦስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ነጥቦች ማግኘት የቻሉት ኢትዮጵያ መድኖች ስኬታማው የአዳማ ቆይታቸው ለማሳመር ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ የማግኘት የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።

መድኖችች በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎቻቸው ያሳኳቸው ዘጠኝ ነጥቦች ወደ ሰንጠረዡ አናት አስጠግተዋቸዋል። ያም ሆኖ ሊጉን የመምራት ዕድላቸውን በእጃቸው ለማስገባት ከነገው ተጠባቂ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት አስፈላጊያቸው ነው።

ከጠንካራ እንቅስቃሴ ጋር አሳማኝ ድል እየተቀዳጀ የቀጠለው መድን በጉልህ ከሚጠቀስለት የመከላከል ጥንካሬ በተጨማሪ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ማስቆጠሩ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ስለመገኘቱ ማሳያ ነው።

በውድድር ዓመቱ በአንድ ጨዋታ ብቻ ሽንፈት የቀመሰው ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ዘጠኝ ጨዋታዎቹ ራሱን ከሽንፈት ከማራቁም ባለፈ በሁሉም መለክያዎች ጥሩ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል። በነገው ጨዋታም ጥቂት ግቦች ያስተናገደ፣ ጠጣር የመከላከል አደረጃጀት ያለው እንዲሁም በሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል ባለው ፉክክር ውስጥ የሚገኝ ቡድን እንደ መግጠማቸው ፈተናው ቀላል ይሆንላቸዋል ተብሎ ባይገመትም ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ከፊት እና ከኋላ ክፍላቸው ያላቸውን ጥንካሬ የተሻለ ግምት እንዲሰጣቸው ያስገድዳል።

በሁሉም ረገድ የተሟላ ቡድን ገንብተው ወደ ሊጉ መሪነት በመንደርደር ላይ ያሉት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ቡድናቸው ከሌላው ጊዜ በተለየ ለመልሶ ማጥቃቶች ተጋላጭ እየሆነ መምጣቱ ብቸኛ የሚያሳስባቸው ጉዳይ ይመስሳል።

ወሳኙ አማካያቸው ጋቶች ፓኖም ካጡ በኋላ ባከናወኑት የመጀመርያው ጨዋታ በውስን መልኩ ለወላይታ ድቻ ፈጣን ሽግግሮች መጋለጣቸውን ተከትሎ ከሀዋሳ ከተማ ከተደረገ ጨዋታ በፊት ቡድኑ በተፈጥራዊ የተከላካይ አማካይ ያለመግባቱ እንደምክንያት አንስተን የመልሶ ማጥቃቶች የማቆም አቅማቸው ከፍ ማድረግ እንደሚገባቸው መጥቀሳችን ይታወሳል። በመጨረሻው ጨዋታም በአንፃራዊነት ከሌላው ጊዜ በተለየ ለፈጣን ሽግግሮች ሲጋለጥ መታየቱ እንዲሁም የነገው ተጋጣሚው በተመሳሳይ እንደነ ሽመክት ጉግሳ የመሳሰሉ ፈጣን ተጫዋቾች የያዘ እና ጥሩ የሽግግር ተጫዋቾች የያዘ እንደመሆኑ በቅርብ ሳምንታት የተስተዋለበት ክፍተት ከወዲሁ መድፈን ይኖርበታል።

በሊጉ አራት ጊዜ የተገናኙት ክለቦቹ አንድ አንድ ጊዜ ሲሸናነፉ በሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። 14 ግቦች በተቆጠሩበት የሁለቱም ግንኙነት ቡድኖቹ 7 ግቦች በእኩሌታ አስቆጥረዋል።