የጨዋታ ሳምንቱ ማሳረግያ የሆኑ መርሀ-ግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ
በወራጅ ቀጠናው የሚገኙ እና የውድድር ዓመቱ የሚያቃና ወሳኝ ድል ፍለጋ ወደ ሜዳ የሚገቡትን ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሀ-ግብር ነው።
ከድል ከራቀ ዘጠኝ ጨዋታዎች ያለፉት ሀዋሳ ከተማ ነገ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሞት ሽረት ትግል እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
እንደ ተጋጣሚው ወራጅ ቀጠናው ውስጥ ያለው ሀዋሳ ከአንድ ነጥብ ውጪ ማስመዝገብ ያልቻለውን ተጋጣሚውን ያህል የውጤት ቀውስ ውስጥ ባይገኝም በቶሎ ወደ አሸናፊነት መመለስ ግን ይጠበቅበታል። በውድድር ዓመቱ ሁለት ድል፣ አራት አቻ እና ሰባት ሽንፈቶች ያስመዘገበው ቡድኑ ከአሰልጣኝ ለውጡ በኋላም ከድል ጋር ተራርቋል።
ሀዋሳ ከተማ ምንም እንኳን ተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች ብያስተናግድም የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ግን በጎ ለውጥ እየታየበት ይገኝል። በመድን ሽንፈት በገጠመበት ጨዋታ ከሌላው ጊዜ በተለየ በርከት ያሉ ዕድሎች የፈጠረው ቡድኑ በነገው ዕለት በጨዋታ በአማካይ 1.5 ግቦች እያስተናገደ የዘለቀው ቡድን እንደመግጠሙ ከባለፉት ጨዋታዎች በአንፃራዊነት የተሻለ ፈተና ስለሚጠብቀው ከአምስት የጨዋታ ሳምንታት የግብ ድርቅ በኋላ ወደ ግብ ማስቆጠሩ ይመለሳል ተብሎም ይገመታል።
የእስካሁኑ የሊጉ ቆይታውን ድል ማስመዝገብ ያልቻለው ወልዋሎ በደረጃ ሰንጠረዡ በአንድ ከፍ ብሎ የሚገኘውን ሀዋሳ በሚገጥምበት መርሀ-ግብር የመጀመሪያውን ሦስት ነጥብ ለማሳካት ያልማል።
እጅግ በተዳከመ አቅም ከአስራ ሁለት ጨዋታ አንድ ነጥብ ያሳካው ቡድኑ የውድድር ዓመቱን የሚያስተካክልበትን ሌላ ዕድል ነገ የሚሞክር ይሆናል። በውድድር ዓመቱ አስራ ዘጠኝ ግቦች አስተናግዶ ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው እና በመከላከሉም በማጥቃቱም ረገድ ብዙ መሻሻል የሚገባው ቡድኑ ያለበት የውህደት ችግር በግልፅ የሚታይ ሆኗል። በርካታ ክፍተቶች ያሉበት የቢጫዎቹ ቡድን በሊጉ የሚቆይበት ዕድል ከዚህ በላይ እንዳይመናመን እና የተስፋ ጭላንጭሉን ለማስቀጠል በየትኛውም መንገድ የሚገኝ ድል በእጅጉ አስፈላጊው ነው።
ሁለቱ ቡድኖች አራት ጊዜ ተገናኝተው ወልዋሎ ሁለት ሲያሸንፍ፣ ሀዋሳ አንድ አሸንፎ በቀሪዋ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። በአራቱ ጨዋታዎች 5 ጎሎች ሲቆጠሩ ወልዋሎ 2፤ ሀዋሳ 3 አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 ጨዋታ አልተካተተም)
በወልዋሎ በኩል ዳዊት ገብሩ፣ ሱልጣን በርሀ፣ ታዬ ጋሻው እና ናትናኤል ዘለቀ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም ዳዋ ሆቴሳ ግን ከጉዳት አገግሟል። በሀዋሳ ከተማ በኩል መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።
ፋሲል ከነማ ከ መቻል
በጉጉት የሚጠበቀው እና የጨዋታ ሳምንቱ መገባደጃ የሆነውን ፋሲል ከነማ እና መቻል የሚያገናኘው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።
ከአስራ ሦስት ጨዋታዎች አስራ ስድስት ነጥቦች የሰበሰቡት ዐፄዎቹ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ዳግም ወደ ድል መንገድ ተመልሰው ደረጃቸው ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ።
የድሬዳዋ ከተማ ቆይታቸው በተከታታይ ድሎች ታጅበው ካገባደዱ በኋላ ውጤታማ ጉዞው በአዳማ ማስቀጠል ያልቻሉት ፋሲል ከነማዎች ከ12ኛ ደረጃነት ከፍ የሚሉበትን ዕድል ለማመቻቸት ወደ መሪነት ለመመለስ ወደ ሜዳ ከሚገባው መቻል ይፋለማሉ። ባለፉት ሥስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥቦች ሁለቱን ብቻ ያሳካው ቡድኑ ያለፉትን አምስት መርሀ-ግብሮች ሽንፈት አልባ ጉዞ ማድረግ ቢችልም በመጨረሻው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት አስተናግዷል። በነገው ዕለትም በዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ላለማስተናገድ እንዲሁም አሁን ካለበት የሰንጠረዡ አካፋይ ላለመንሸራተት ድል ማድረግ አስፈላጊው ነው።
ከተከታታይ ውጤታማ ሳምንታት በኋላ ባለፉት አራት መርሀ-ግብሮች ውስን መንገራገጮች የገጠማቸው መቻሎች በአዳማ ቆይታቸው የጣሏቸው ስድስት ነጥቦች በሊጉ አናት ተደላድለው እንዳይቀመጡ እክል ሆነውባቸዋል።
በመጀመርያዎቹ ዘጠኝ ጨዋታዎች በተከታታይ አስራ ዘጠኝ ግቦች ማስቆጠር የቻለ ስል የፊት መስመር ጥምረት የነበራቸው መቻሎች በቅርብ ሳምንታት ውስን መቀዛቀዞች አሳይተዋል፤ ቡድኑ ከመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ውስጥ በሦስቱ ኳስ እና መረብ ሳያገናኝ መውጣቱም ከዚ ቀደም በጨዋታ በአማካይ 2.1 ግብ ያስቆጠረው ውጤታማው የፊት መስመሩ መቀዛቀዙ ማሳያ ነው።
በነገው ዕለት ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመምጣትም በባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ካስተናገደው የዐፄዎቹ የመከላከል አደረጃጀት የሚጠብቃቸው ፈተና በድል መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በጉዳት እያጡ ያሉት ፋሲል ከነማዎች ዮናታን ፍስሐ ፣ ኪሩቤል ዳኜ ፣ በረከት ግዛው እና ቢኒያም ላንቃሞ አሁንም በጉዳት ላይ ሲሆኑ በተጨማሪ ተመስገን ካስትሮም በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆኗል። በመቻል በኩል የቡድን ዜና ለማግኘች ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 13 ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከነማ ስድስት ጨዋታ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖራቸው መቻል አራት ጨዋታዎች አሸንፏል። ቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ናቸው። ፋሲል 16 ሲያስቆጥር መቻል 9 አስቆጥሯል።