ሪፖርት | መቻል የሊጉን መሪነት የሚረከብበትን ዕድል አባክኗል

በትኩረት የተጠበቀው የጨዋታ ሳምንቱ መገባደጃ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

ፋሲል ከነማዎች በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ከገጠመው ቋሚ  ተመስገን ካስትሮ፣ ዳግም አወቀ እና ጃቢር ሙሉ በእዮብ ማቲያስ፣ አሚር ሙደሲር እና ቃልኪዳን ዘላለም ተክተው ሲገቡ መቻሎችም ከድሬዳዋ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ አማኑኤል ዮሐንስ በበኃይሉ ግርማ ብቻ ተክተው ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።


መቻል የኳስ ቁጥጥር ብልጫም ሆነ የግብ ዕድሎች በመፍጠር የተሻለ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመርያው አጋማሽ በርከት ያሉ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። ግሩም ሐጎስ አሻምቷል ዳንኤል ዳርጌ ባደረጋት ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት መቻሎች በአጋማሹ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች መፍጠር ችለዋል፤ በተለይም ዳንኤል ዳርጌ ከበረከት ደስታ የተቀበላትን ኳስ መቶ ዮሐንስ ደርሶ የመለሳት ኳስ እና ምንይሉ ወንድሙ በቀጥታ ከቅጣት ምት መቷት ግብ ጠባቂው የመለሳት ኳስ ጦሩን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም በሽመልስ በቀለ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ኳስና መረብ ማገናኘት ያልቻሉት መቻሎች በሰላሣ ስምንተኛው ደቂቃ ላይ ጥረታቸው ሰምሮ ግብ ማስቆጠር ችለዋል።

በረከት ደስታ በመልሶ ማጥቃት ሂደት የመጣችውን ኳስ በፋሲል ተጫዋቾች ስህተት አግኝቶ ከግብ ጠባቂው ከፍ አድርጎ ያስቆጠራት ግብም ቡድኑን መሪ ማድረግ ችላለች።

ፋሲል ከነማዎች ጌታነህ ከበደ በረዥሙ የተሻገረችውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ካደረጋት ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም።

ከመጀመርያው አጋማሽ በአንፃራዊነት የተሻለ ተቀራራቢ እንቅስቃሴ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ጥቂት ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። በአጋማሹ የመጀመርያ ደቂቃዎች የተሻለ ብልጫ የነበራቸው መቻሎች በዳንኤል ዳርጌ እንዲሁም በአብዱልከሪም ወርቁ በሁለት አጋጣሚዎች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል፤ በተለይም አብዱልከሪም ወርቁ የፋሲል ተጫዋቾች መዘናጋት ተጠቅሞ  ያገኛትን ኳስ መቶ የግቡን ብረት ታካ የወጣችው ኳስ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች። የግብ ዕድሎች መፍጠር ባይችሉም በሂደት ወደ ጨዋታው ቅኝት የገቡት ፋሲሎችም የተጫዋቾች ቅያሪ ካደረጉ በኋላ በተሻለ ፍላጎት በመጫወት የአቻነቷን ግብ አስቆጥረዋል።

በሰባኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው አንዋር ሙራድ ከግራ መስመር ተሻምታ የመቻል ተከላካዮች በአግባቡ ያላራቋትን ኳስ በግሩም መንገድ በመቀስ ምት በማስቆጠር ነበር ቡድኑን አቻ ማድረግ የቻለው።

ከግቧ በኋላ በተለይም መቻሎች ተጭነው መጫወት ቢችሉም ይህ ነው የሚባል የጠራ ዕድል ሳይፈጥሩ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።