መረጃዎች| 62ኛ የጨዋታ ቀን

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ16ኛ ሳምንት ፍልሚያ ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀምራል ፤ መርሀ-ግብሮቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

በአንድ ነጥብ እና በሁለት ደረጃዎች የሚበላለጡ ቡድኖች የሚያገናኘው መርሀ-ግብር ለጨዋታው አሸናፊ ብያንስ የአንድ ደረጃ መሻሻል የሚያስገኝ እንደመሆኑ ብርቱ ፍልምያ ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።

ሁለት ተከታታት ድሎች ማስመዝገባቸውን ተከትሎ ከአደጋው ቀጠና ርቀው ከሰንጠረዡ አካፋይ ከፍ ብለው የተቀመጡት አዞዎቹ በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ሦስት ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ።

አዞዎቹ ተከታታይ ድሎች ከማስመዝገባቸው በዘለለ በውድድር ዓመቱ አስራ ሁለት ግቦች ያስተናገደው የኃላ ክፍላቸው በቅርብ ሳምንታት ጉልህ መሻሻሎች አሳይቷል። ቡድኑ በሁለት መርሀ-ግብሮች አምስት ግቦች ካስተናገደ ወዲህ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በሦስቱ ግቡን ሳያስደፍር በመውጣት አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዱም አንዱ ማሳያ ነው።
ቡድኑ በሊጉ በርከት ያሉ ድሎች ካስመዘገቡ ክለቦች ተርታ ቢመደብም እንዲሁም በሊጉ በአንድ ጨዋታ ብቻ ነጥብ ተጋርቶ በመውጣት ዝቅተኛ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ቀዳሚ ቢሆንም ያስተናገዳቸው ስድስት ሽንፈቶች በሰንጠረዡ ከፍ ብሎ እንዳይቀመጥ አድርገውታል። የነገው ተጋጣሚው በአንድ ነጥብ ከፍ ብሎ የተቀመጠ እንደመሆኑም በጨዋታው ድል ማስመዝገብ የደረጃ መሻሻል ያስገኝለታል።

ከአራት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች እና ከአንድ ሽንፈት መልስ ወልዋሎን አሸንፈው ወደ ድል መንገድ መመለስ ችለው የነበሩት የጦና ንቦች በመጨረሻው መርሀ-ግብር ከሲዳማ ቡና ነጥብ ተጋርተው ወደ ነገው ጨዋታ ይቀርባሉ።

የጦና ንቦቹ በውድድር ዓመቱ ሀያ ሁለት እና አስራ ሰባት ግቦች ካስቆጠሩት መቻል እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥሎ በርከት ያሉ ግቦች ያስቆጠረ የፊት መስመር ገንብተዋል። በሊጉ ከሚገኙ ቡድኖች ውስጥ ለቀጥተኛ አጨዋወት የሚያደላ አቀራረብ ያላቸው የጦና ንቦቹ ውጤታማ የማጥቃት አጨዋወት እንዳላቸው የማያጠያይቅ ጉዳይ ቢሆንም ጥንካሬው ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች አልገላገላቸውም። ቡድኑ ከመጨረሻዎቹ ሰባት ጨዋታዎች በአምስቱ ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱም ማሳያ ነው። በነገው ዕለትም ከሁለት ተከታታይ ድሎች መልስ ወደ ጨዋታው የሚቀርብ እና በጥሩ መንፈስ የሚገኝ ቡድን እንደመግጠማቸው ፈተናው ቀላል አይሆንላቸውም።

በአርባምንጭ ከተማ በኩል ሳሙኤል አስፈሪ ፣አበበ ጥላሁን እና አሸናፊ ተገኝ አሁንም በጉዳት የነገው ጨዋታ ሲያመልጣቸው እንዳልካቸው መስፍንም ከጉዳቱ ተመልሶ ልምምድ ቢጀምርም የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው። በወላይታ ድቻ በኩል አብነት ደምሴ ወደ ልምመድ ቢመለስም ለነገው ጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ነው። ግብ ጠባቂው ቢንያም ገነቱም ከህክምና ዕረፍት መልስ በሜዳ ላይ የእጅ ስራዎችን ቢጀምርም ለጨዋታው በቁ አይደለም፤ በተመሳሳይ ሁለተኛው ግብጠባቂ አብነት ይስሀቅ ሙሉ ለሙሉ ከጉዳቱ ባለማገገሙ ነገ በሚኖረው ጨዋታ ወጣቱ ግብጠባቂ አብነት ሀብቴ የሚሰለፍ ይሆናል። ከዚህ ውጭ በጉዳትም ሆነ በቅጣት ከነገው ስብስብ ውጭ የሆነ ተጫዋች በወላይታ ድቻ በኩል የለም።

ከዚህ ቀደም ሁለቱ ቡድኖች 14 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ዘጠኙ ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ሲፈፅሙ ወላይታ ድቻዎች አራት እንዲሁም አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ አንድ ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ስሑል ሽረ

የነገው ሁለተኛ ጨዋታ በወራጅ ቀጠናው ውስጥ በሦስት ነጥቦች ልዩነት ተከታትለው የተቀመጡት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ስሑል ሽረን ያገናኛል።
ጨዋታው ሙሉ ነጥብ ይዞ ለሚወጣ ቡድን ከወራጅ ቀጠናው የማውጣት ወይም የተሻለ ተስፋ ሰንቆ ለቀጣይ መርሀ-ግብር የመሻገር ዕድል የሚሰጥ እንደመሆኑ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።

በውድድር ዓመቱ ሳይጠበቁ በታችኛው የሰንጠረዡ ክፍል በሚደረግ ፉክክር የሚገኙት ሻምፕዮኖቹ ንግድ ባንኮች በሀድያ ሆሳዕና ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም ከተከታታይ አራት ሽንፈቶች ለመውጣት ወደ ሜዳ ከሚገባው ስሑል ሽረ ይፋለማሉ።

በነብሮቹ ሽንፈት በገጠማቸው የመጨረሻ ጨዋታ ጨምሮ በአመዛኙ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ይዘው በመጫወት ላይ የሚገኙት ንግድ ባንኮች በሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦች አስቆጥረው ዓመቱን ቢጀምሩም ውጤታማነታቸው በተቀሩት መርሀ-ግብሮች መቀጠል አልቻለም። ቡድኑ ከተጠቀሱት ሁለት ጨዋታዎች በኋላ በተከናወኑ አስራ አንድ መርሀ-ግብሮች ስድስት ግቦች ብቻ ማስቆጠሩም በግብ ማስቆጠሩ ረገድ የነበረው መልካም አጀማመር ምን ያህል እንዳሽቆለቆለ ማሳያ ነው።

አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ቡድናቸው ከመልካም እንቅስቃሴው በዘለለ ወደ ውጤታማነት የማሸጋገር የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል። በተለይም ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት ጥምረት መሻሻል የሚገባው ክፍል ነው። የሽረ የኋላ መስመር በቅርብ ጨዋታዎች ተዳክሞ ከመታየቱ አንፃር በነገው ዕለት ከባለፉት ተጋጣሚዎች ቀለል ያለ ፍልምያ ይጠብቃቸዋል ተብሎ ስለሚታሰብም በውጤትም ይሁን በግብ ማስቆጠሩ የተሻለ ነገር እንዲጠበቅ ያደርገዋል።

ተከታታይ አራት ሽንፈቶች ያስተናገዱት ስሑል ሽረዎች ከመጥፎው ወቅታዊ አቋማቸው ለማገገም በሦስት ነጥቦች ልቆ በአንድ ደረጃ ከፍ ብሎ ከሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ይፋለማሉ።

በአዳማ ከተማ ቆይታቸው ነጥብ ማስመዝገብ ያልቻሉት ስሑል ሽረዎች ከገጠማቸው ተከታታይ ሽንፈት በተጨማሪ ዘለግ ላሉ ሳምንታት የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ ሆኖ መዝለቅ ችሎ የነበረው የመከላከል አደረጃጀት ብርታት አጥተዋል። በመጨረሻዎቹ አራት መርሀ-ግብሮች ሰባት ግቦች ያስተናገደው ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ከወልዋሎ እና አዳማ ከተማ በመቀጠል ከወላይታ ድቻ ጋር በጣምራ በርከት ያሉ ግቦች ያስተናገደ ክለብ ሆኗል።

አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ተጋላጭ እየሆነ ያለው የኋላ መስመራቸው ክፍተት ለመድፈን የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት መዋቅር ማስተካከል ቀዳሚ ስራቸው ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ በመጀመርያዎቹ ሁለት ሳምንታት አዳማ እና ሀዋሳ ላይ አራት ግቦች ካስቆጠረ ወዲህ በተከናወኑ አስራ ሁለት መርሀ-ግብሮች አምስት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወታቸው ወደ ቀደመ ጥንካሬው የመመለስ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ፉአድ ፈረጃ እና ሱሌማን ሀሚድ ከጉዳታቸው ለማገገም ረጅም ወራት የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ በጨዋታው የማይኖሩ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት ሳይጠበቅ ከጨዋታ ውጭ የነበረው ተከላካይ ካሌብ አማንክዋህ ግን ልምምድ በመመለሱ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑ ሲታወቅ የተቀሩት የቡድኑ አባላት ለወሳኙ ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠናል። በስሑል ሽረ በኩል ፋሲል አስማማው ከጉዳት ቢመለስም የአላዛር አድማሱ መሰለፍ ግን አጠራጣሪ ነው። ሰለሞን ገብረክርስቶስም በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች ነገ በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል።