ሪፖርት | አዞዎቹ ከመመራት ተነስተው ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል

አዞዎቹ በአህመድ ሁሴን ሁለተኛ አጋማሽ ሁለት ግቦች ታጅበው ወላይታ ድቻን ከመመራት ተነስተው በማሸነፍ ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን አሳክተዋል።

አርባምንጭ ከተማ በ15ኛው ሳምንት ስሑል ሽረን ካሸነፉበት ቋሚያቸው ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ሲቀርቡ ወላይታ ድቻ በ15ኛው ሳምንት ከሲዳማ ቡና ነጥብ ተጋርተው ከወጡበት ቋሚ ስብስባቸው ሁለቱ ለውጥ በማድረግ ተስፋዬ መላኩን በፍፁም ግርማ ካርሎስ ዳምጠውን በባዬ ገዛኸኝ ተክተው ገብተዋል።

በርከት ያሉ ደጋፊዎች የታደሙበት የ16ኛ ሳምንት መክፈቻ ጨዋታ ከጅምሩ ጀምሮ አዞዎቹ ወደ ግብ የሚያደርጉትን ግስጋሴ በማስመለከት የጀመረ ሲሆን ገና ከአንደኛው ደቂቃ ጀምረው አደገኛ ሙከራ ለተመልካች አስመልክተዋል። ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ በአጋማሹ መረጋጋት ተስኗቸው በጨዋታም ሆነ በግብ አጋጣሚዎችን በመፍጠር ረገድ ተበልጠው የመጀመራዎቹ አስር ደቂቃዎች ተቆጥረዋል። በአንፃራዊነት በአጋማሹ አዞዎቹ በተደጋጋሚ የጦና ንቦችን ግብ ክልል እየጎበኙ ተከላካዮቻቸውን የፈተኑ ሙከራዎችን አድርገዋል።

ከአዞዎቹ ሙከራዎች መካከል 1ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማው ኳስ ተጨራርፎ አህቡዋ ብሪያን ጋር ደርሶ ወደግብ መጥቶ የግብ ቋሚ ብረት የመለሰበት ፣ 8ኛው ደቂቃ ላይ ቡታቃ ሸመና ርቀት ላይ ሆኖ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂ ያዳነበት፣ በ14ኛው ደቂቃ አህመድ ሁሴን ከፍፁም ቅጣት ምት መምቻ ሳጥን ለትንሽ ርቆ ያደረገው ሙከራ በግብ አግዳሚ ተጨራርፋ ወደ ውጪ የወጣበት እንዲሁም በ35ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን ኳስ አግኝቶ ይዞ ገብቶ ወደ ግብ መጥቶ ለትንሽ ከግብ ቋሚ ብረት በኩል ያለፈበት ሙከራዎች ተጠቃሾቹ ነበሩ።

በኳስ ቁጥጥር እና በግብ ማግባት ሙከራ ደካማ እንቅሰቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት የጦና ንቦች አልፈው አልፈው ወደፊት ለመሄድ የሚያደርጉት አንቅስቃሴ እየተቋረጠባቸው ሲቸገሩ ለማየት ችለናል። ምንም እንኳን ብልጫ ቢወሰድባቸውም ግብ በማስቆጠር ረገድ ቀዳሚ መሆን ችለዋል። በ16ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ውጪ የወጣውን ኳስ ግብ ጠባቂው አብነት ሀብቴ በመልስ ምት ረጅም ኳስ ከተከላካይ ጀርባ ሲጥል ያሬድ ዳርዛ ፍጥነቱንና ጉልበቱን በመጠቀም ደርሶ የአዞዎቹ ግብ ጠባቂ መውጣቱን አይቶ በብልሃት ኳሷን ከፍ አድርጎ በእጆቹ መሃል በማሳለፍ ከመረብ ጋር አገናኝቶ መሪ አድርጓቸዋል። በዚህም አጋማሹ በጦና ንቦች መሪነት ተገባዶ ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሲቀጥል ሁለቱም ቡድኖች ወደፊት በመሄድ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እያደረጉ ጨዋታው 60ኛው ደቂቃ ላይ ደርሶ አዞዎቹ አቻ መሆን የቻሉበት ግብ በአህመድ ሁሴን አማካኝነት አስቆጥረዋል። በረጅሙ የተጣለውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ አሻግሮለት ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ በቀላሉ ከፍ አድርጎ በመምታት ግሩም ግብ መረብ ላይ አክሏል። ከአቻነት ግብ መቆጠር በኋላ የተነቃቁ ሚመስሉት አዞዎቹ አከታታትለው ወደፊት ሄደው ጫና ለማሳደር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ወላይታ ድቻዎችም በበኩላቸው ወደ ሦስተኛው ሜዳ ክፍል በረጃጅም ኳሶች ቢደርሱም ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ፈታኝ የሚባል ሙከራ ሳያደርጉ ደቂቃዎቹ ወደ ሰባዎቹ መዳረሻ ደርሰዋል።


ቡድኖቹ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች የግብ ማግባት ሙከራ ሳያስመለክቱ ደቂቃዎች እየገፉ ወደ መገባደጃ የቀረቡ ሲሆን አዞዎቹ በርከት ብለው ወደ ግብ ክልል በመግባት ጫና ሲያደሳድሩ የጦና ንቦች ደግሞ ነጥብ ተጋርተው መውጣት ያሰቡ በሚመስል መልኩ ወደኋላ አፈግፍገው ሲጫወቱ መመለከት ችለናል።

ጨዋታውም በአቻ ውጤት የሚጠናቀቅ ቢመስልም በተደጋጋሚ ኳስ ይዞ በመግባት የወላይታ ድቻዎችን ተከላካዮች ሲያስጨንቅ የነበረው ቁመታሙ የፊት መስመር ተጫዋች አህመድ ሁሴን መደበኛው ደቂቃ ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀሩት የማሸነፊያ ግብ መረብ ላይ አክሏል። 89ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር በኩል የተሻገረውን ኳስ በደረቱ አቁሞ በግሩም ሁኔታ ዞሮ ጠንከር ያለ ኳስ በመምታት ከመረብ ጋር አገናኝቶ አዞዎቹ ከመመራት ተነስተው ወላይታ ድቻን 2-1 በማሸነፍ ሶስት ነጥብ ይዘው እንዲወጡ አድርጓል።