ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ስሑል ሽረ ነጥብ ተጋርተዋል

ሁለቱንም ከሽንፈት የተመለሱ ቡድኖችን ያገናኘው የምሽቱ ጨዋታ ያለ አሸናፊ ተጠናቋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በ15ኛው ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ሽንፈት ከቀመሱበት ቋሚያቸው አምስት ለውጦችን በማድረግ እንዳለ ዩሐንስን በተስፋዬ ታምራት ፣ ተመስገን ተስፋዬን በካሌብ አማንክዋህ፣ ቢኒያም ካሣሁንን በብሩክ እንዳለ፣ አዲስ ግደይን በዳዊት ዩሐንስ፣ ሃይከር ደዋሙን በዮናስ ለገሰ ተክተው ሲቀርቡ ስሑል ሽረ በ15ኛው ሳምንት በአርባምንጭ ከተማ ከተሸነፉበት ቋሚ ስብስባቸው አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ ፋሲል ገ/ሚካኤልን በሞይስ ፖዎቲ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፈጣን ሽግግር የጀመረው ጨዋታው በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ቶሎ ቶሎ ተጋጣሚዎቻቸው ግብ ክልል ደርሰው የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ፈጥረው ፍፁም ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችን በማምከን ቀጥሏል። ከእነዚህ አጋጣሚዎች መካከል በአንደኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ታምራት ሳጥን ውስጥ ሆኖ ለኪቲካ ጅማ አሻግሮለት ከግቡ ቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ ከፍ አድርጎ ያመከነው አጋጣሚ ቀዳሚ የነበረ ሲሆን እንዲሁ ካሌብ አማንክዋህ በረጅሙ ከተከለካይ ጀርባ የጣለውን ኳስ ዳዊት ዩሐንስ በፍጥነት ደርሶ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ወደግብ መጥቷት ሞይስ ፖዊቲ የመለሰበት ሌላኛዋ ለግብ የቀረበች አጋጣሚ ትታወሳለች። በአጋማሹ ስሑል ሾረዎች ኳስ እያንሸራሸሩ ወደፊት እየሄዱ ከተቃራኒው ቡድን ተቀራራብ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም የግብ እድል በመፍጠር ረገድ ደካማ ነበሩ።  39ኛው ደቂቃ ላይ ብርሃኑ አዳሙ ያመከነው ወርቃማ አጋጣሚ ሲታወስ በአንድ ለአንድ ቅብብል ይዘው የገቡትን ኳስ አግኝቶ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ጠንከር ያለ ኳስ መጥቶ የንግድ ባንኩ ግብ ጠባቂ ፓላክ ቸል ሸፍኖ የመለሰባቸው አጋጣሚ ይታወሳል።

አጋጣሚዎችን በመፍጠር ብልጫ የወሰዱት ንግድ ባንኮች አልፈው አልፈው ግብ ሚሆኑ እድሎችን ለመፍጠር ወደ ግብ ክልል መድረስ የቻሉ ቢሆንም እላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያስመለክቱ ጨዋታው እንዲህ እያለ ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ እያስመለከተ ቀጥሎ 31ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዳዊት ዩሐንስ ኳስና መረብ ቢያገናኝም ከጨዋታው ውጪ ተብሎባቸዋል። እንዲሁም 44ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር በኩል የተሻማውን ኳስ ባስሩ ኡመር በግንባሩ ገጭቶ ሙከራ ቢያደርግም ኳሷ ለጥቂት ከግብ አግዳሚ ከፍ ብላ አልፋበታለች። በዚህም አጋማሹ ግብ ሳያስመለክት ተገባዶ ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ጨዋታው ከእረፍት ተመልሶ ሲቀጥል ጠንከር ብለው የተመለሱት ንግድ ባንኮች የግብ እድሎችን ለመፍጠር ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል ቶሎ ቶሎ እየደረሱ ጫና እያሳደሩ ጨዋታው 52ኛው ደቂቃ ላይ ሲድርስ ለግብ የቀረበ አደገኛ ሙከራ አድርገዋል። በአንድ ለአንድ ቅብብል የተገኘውን ኳስ ኪቲካ ጅማ አግኝቶ ዞሮ ወደ ግብ መጥቶ ግብ ጠባቂው መልሶበታል። በተደጋጋሚ የግብ መግባት ጥረት ሲያድርጉ የነበሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ መሪ መሆን የቻሉበትን ኳስ መረብ ላይ አሳርፈዋል። በ60ኛው ደቂቃ ላይ ባስሩ ኡመር ከመሃል ሜዳ ቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ ከፍ አድርጎ ያሻገረውን ኳስ ኪቲካ ጅማ ቶሎ ወደ ውስጥ በምግባት ደርሶ ዘሎ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብነት ቀይሮታል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ወደ ጨዋታ ተመልሰው ወደ ፊት መሄድ ላይ ያተኮሩት ስሑል ሽረዎች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር አምስት ደቂቃ  ጠብቀው በ65ኛው ደቂቃ ላይ በመሐመድ ሱሌይማን አማካኝነት ግብ አስቆጥረዋል። ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ የተከላካይ መስመር ተጫዋች የሆነው መሐመድ ሱሌማን በግንባሩ ገጭቶ መረብ ላይ አሳርፏል።

ጨዋታው አቻ ከሆነ በኋላ ንግድ ባንኮች ገፍተው ወደ ሶስተኛው ሜዳ በመድረሱም ሆነ በእንቅስቃሴ ጥሩ ብልጫ የወሰዱ ሲሆን እላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ተስኗቸው ጨዋታው ወደመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎት ሲደርስ 82ኛው ደቂቃ ላይ በዳዊት ዩሐንስ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው አዲስ ግደይ ላይ በተሰራ ጥፋት ቅጣት ምት አግኝተው አዲስ ግደይ ከሚታወቅበት ቦታ ላይ ወደ ግብ መጥቶ ግብ ጠባቂው የተቆጣጠረባቸው አጋጣሚ ይታወሳል። ስሑል ሽረዎችም በበኩላቸው አልፈው አልፈው በመልሶ ማጥቃት ወደፊት ለመሄድ ጥረት ቢያደርጉም ተፅዕኖ ሳያሳድሩ ቀርተው ይልቁንስ ወደኋላ አፈግፍገው ኳሶቹን ሲያቋርጡ ተመልክተናል።

መደበኛው የጨዋታ ክፍልጊዜ ተጠናቆ ጭማሪ በታየው ላይ ሁለቱም ቡድኖች ከአንድ ነጥብ ይልቅ ሶስት ነጥብ ይዘው መውጣት የሚያስችላቸውን ተጨማሪ ግብ ፍለጋ የተጋጣሚዎቻቸውን ግብ ክልል ብረግጡም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክት ነጥብ በማጋራት ተጠናቋል።