መረጃዎች | 63ኛ የጨዋታ ቀን

በ16ኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት የሚከናወኑ መርሐብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

መቐለ 70 እንደርታ ከ አዳማ ከተማ

በሁለት ደረጃዎች እና በሦስት ነጥቦች ልዩነት የተቀመጡትን ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነው።

በመጨረሻው መርሐግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክን በማሸነፍ ነጥባቸው አስራ ስምንት በማድረስ 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ምዓም አናብስት አዳማ ከተማ ተመችቷቸዋል።  በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስቴድየም ሽንፈት እንዲሁም ግብ ሳያስተናግድ የዘለቀው ቡድኑ በነገው ዕለት ሙሉ ነጥብ ማስመዝገብ ከአደጋው ክልል ይበልጥ እንዲርቅ ያስችለዋል።

በስሑል ሽረ እና ደደቢት የሚታወቁበትን የ3-5-2 አደራደር መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ በመከላከል አደረጃጀታቸው የሚታይ ለውጥ ያመጡት አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ውሳኔያቸው ውጤታማ እያደረጋቸው ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዱም የኃላ ክፍሉ ላመጣው አወንታዊ ለውጥ ማሳያ ነው። መቐለ ምንም እንኳ ውጤታማ የመከላከል አደረጃጀት መገንባት ቢችልም በማጥቃቱ ረገድ ያለው ጥንካሬ ግን ደረት አያስነፋም።  ቡድኑ በነገው ዕለት በሊጉ ከፍተኛ የግብ መጠን በማስተናገድ በሁለተኛ ደረጃነት የተቀመጠው ቡድን እንደመግጠሙ ከባድ ፍልሚያ ይጠብቀዋል ተብሎ ባይገመትም በጨዋታዎች የሚፈጥራቸው የግብ ዕድሎች በጥራትም ሆነ በቁጥር ከፍ የማድረግ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል።

ወልዋሎን በማሸነፍ የከተማቸውን ቆይታ አሀዱ ብለው የጀመሩት አዳማ ከተማዎች ከዛ በኋላ በተከናወኑ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግደው ወደ ነገው ጨዋታ ይቀርባሉ።

ተከታታይ ሽንፈቶች ማስተናገዱን ተከትሎ በወራጅ ቀጠናው አፋፍ ለመቀመጥ የተገደደው ቡድኑ ከአደጋው ክልል ለመራቅ ከወዲሁ ወደ ድል መንገድ መመለስ ግድ ይለዋል።  አዳማ ከተማ ወረጃ ቀጠና ውስጥ ከሚገኙ ቡድኖች አንፃር ሲታይ በርከት ያሉ ግቦች ማስቆጠር ቢችልም በመከላከሉ ረገድ ደካማ ቁጥሮች አስመዝግቧል። ሃያ ግቦች በማስተናገድ ከፍተኛ የግብ መጠን ካስተናገደው ወልዋሎ በመቀጠል በውድድር ዓመቱ አስራ ስምንት ግቦች ያስተናገደው የቡድኑ መከላከል መዋቅርም መሻሻል የሚገባው የቡድኑ ክፍል ነው። ቡድኑ ከአደጋው ክልል ለመራቅ እና በከተማው ሁለተኛ ድሉን ለማሳካት በነገው ጨዋታ በሙሉ ኃይሉ በማጥቃት ላይ ተመስርቶ ወደ ሜዳ እንደሚገባም ይጠበቃል።

መቐለ 70 እንደርታ አምበሉ ያሬድ ከበደን በአምስት ቢጫ በቅጣት አያሰልፍም ከዚ በተጨማሪ የአብሥራ ተስፋዬ፣ መናፍ ዐወል፣ አሸናፊ ሀፍቱ፣ አማኑኤል ልዑል እና የረዥም ጊዜ ጉዳት የገጠመው ክብሮም አፅብሐ በነገው ጨዋታ የማይሳተፉ ተጫዋቾች ናቸው። በአዳማ ከተማ በኩል አድናን ረሻድ ፣ ቢኒያም ዐይተን እና ዳግም ተፈራ በጉዳት ምክንያት የማይኖሩ ሲሆን የሬድዋን ሸሪፍ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።

ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም አራት ጊዜ ተገናኝተው መቐለ 70 እንደርታ ሁለቱን ሲያሸንፍ አዳማ ከተማ አንዱን አሸንፎ በቀሪው አቻ ተለያይተዋል። መቐለ 6፣ አዳማ 5 ግቦች አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 ጨዋታ አልተካተተም)

ኢትዮጵያ መድን ከ ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ መድን መሪነቱን ለማጠናከር ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ከሰንጠረዡ አጋማሽ ከፍ ለማለት የሚያደርጉት ፍልሚያ በጨዋታ ሳምንቱ ከሚደረጉ ተጠባቂ ጨዋታዎች አንዱ ነው።

አራት ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው የሊጉን መሪነት የተረከቡት ኢትዮጵያ መድኖች በአዳማ ከተማ ያላቸውን ውጤታማ ጉዞ በማስቀጠል እንዲሁም መሪነታቸውን ለማጠናከር ኢትዮጵያ ቡናን ይገጥማሉ።

ተጠባቂ በነበረው የመጨረሻ ሳምንቱ የባህር ዳር ከተማው ጨዋታ ወሳኝ ድል ተቀዳጅተው በጥሩ የማሸነፍ መንፈስ የሚገኙት መድኖች በመጨረሻዎቹ አራት መርሐግብሮች በጨዋታ በአማካይ ሁለት ግቦች ግቦች ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወታቸው የወቅቱ ዋነኛ ጠንካራ ጎናቸው ሆኗል። ሆኖም በነገው ዕለት ያለፉትን አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች መረቡን ባለማስደፈር ጥሩ የመከላከል አወቃቀር የገነባውን ኢትዮጵያ ቡና እንደመግጠማቸው ቀላል ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ አይገመትም።

በውድድር ዓመቱ አንድ ሽንፈት ብቻ የቀመሰው ብቸኛው የሊጉ ክለብ የሆነው መድን ሽንፈት አልባ ጉዞ ባደረገባቸው ያለፉት አስር ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው ሰላሣ ነጥብ ሀያ አራቱን ማሳካቱም ቡድኑ ያለበትን የውጤት ከፍታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

አስራ ዘጠኝ ነጥቦች በመሰብሰብ በ9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከሰንጠረዡ አጋማሽ ከፍ የሚያደርጋቸውን ውጤትን ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

በሀድያ ሆሳዕናና አዳማ ከተማ ከገጠሟቸው ሽንፈቶች በኋላ በሁሉም ረገድ የሚታይ ለውጥ ያመጡት ቡናማዎች ከተጠቀሱት መርሐግብሮች በኋላ በተካሄዱ አምስት ጨዋታዎች ከሽንፈት ከመራቃቸው በዘለለ ሦስት ድሎች በማስመዝገብ በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ ይገኛሉ። ቡድኑ ከውጤቱም  በዘለለ በመከላከሉ ረገድ ጉልህ መሻሻሎች አሳይቷል። መረቡን ካስደፈረ አምስት የጨዋታ ሳምንታት ማስቆጠሩም የመከላከል አደረጃጀቱ ያለበትን አሁናዊ ብቃት ማሳያ ነው።

የቡናማዎቹ የኋላ ክፍል ካለበት ወቅታዊ አቋም አንፃር በቀላሉ እጅ ይሰጣል ተብሎ ባይገመትም ቡድኑ ከሽንፈት በራቀባቸው አምስት መርሐግብሮች አራት ግቦች ያስቆጠረው የፊት መስመር በሊጉ ጠንካራ የመከላከል ጥምረት ለገነባው መድን በሚመጥን አቅራረብ ወደ ጨዋታው መቅረብ ግድ ይለዋል።

በኢትዮጵያ መድን በኩል አጥቂው አብዲሳ ጀማል ከጉዳቱ አገግሞ ልምምድ ቢጀምርም ለነገው ጨዋታ የማይደርስ ሲሆን ተከላካዩ ዮሀንስ ሴጌቦም በተመሳሳይ ከነገው ጨዋታ ውጭ ይሆናል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ሁሉም የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 29 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 13 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መድን 7 ጊዜ አሸንፏል ፤ 9 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ ቡና 48 ጎሎች ሲያስቆጥር ኢትዮጵያ መድን 32 ጎሎች አስቆጥሯል።