ምዓም አናብስቶች በሁለቱም አጋማሽ ባስቆጠሩት ሁለት ግቦች አዳማ ከተማን በመርታት ተከታታይ ድል ተጎናፅፈዋል።
መቐለ 70 እንደርታ በ15ኛው ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከረቱበት ቋም ስብስባቸው አንድ ለውጥ በማድረግ ያሬድ ከበደን በኬኔዲ ገ/ብረፃዲቅ ተክተው ሲቀርቡ አዳማ ከተማ በ14ኛው ሳምንት በአርባምንጭ ከተማ ሁለት ለምንም ሲሸነፉ ከተጠቀሙበት ቋሚ አሰላለፋቸው አራት ለውጥ በማድረግ ናትናኤል ተፈራን በዳንኤል ተሾመ፣ መላኩ ኤልያስን በኋይለሚካኤል አደፍረስ፣ ሬድዋን ሸረፋን በሙሴ ከበላ እና ዳንኤል ደምሴን በአሜ መሐመድ ተክተው ገብተዋል።
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ከፍ ያለ ጫና አሳድረው መጫወት የጀመሩት መቐለ 70 እንደርታዎች ገና በሶስተኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። መሃል ሜዳ አከባቢ ተጨራርፋ የተገኘችውን ኳስ ያሬድ ብርሃኑ እየገፋ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ከመረብ ጋር አገናኝቶ መሪ አድርጓቸዋል። አዳማ ከተማዎች ምንም እንኳን ግብ ቢያስተናግዱም በንክኪ እና ወደ ፊት በሚያደርጉት እንቅሰቃሴ የተሻሉ ነበሩ። በአመዛኙ ተከላካይ መስመር ላይ ያመዘነው የምዓም አናብስቶቹ አጨዋወት በአጋማሹ በሙከራዎች ረገድ ፍፁም የተዳከመ ነበር።
ምንም እንኳን ቅድሚያ ቢወስድባቸውም አሁንም አውንታዊነታቸውን ያስቀጠሉት አዳማ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል በመድረስ ብልጫው በነሱ ቁጥጥር ስር ሆኖ የግብ ማግባት ሙከራዎችን በማድረግ ሲቀጥሉ በ24ኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ ኤልያስ በቀኝ መስመር በኩል ኳስ እየገፋ ሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ አክርሮ በመምታት ያደረገውን ሙከራ ሶፎንያስ ሰይፈ ተቆጣጥሮባቸዋል።
ጨዋታው 31ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ አዳማ ከተማዎች ከሳጥኑ ለትንሽ ርቆ አደገኛ የሚባል ቦታ ላይ ቅጣት ምት አግኝተው ነቢል ኑሪ ወደግብ መጥቶ ከግብ አግዳሚ ለትንሽ ከፍ ያለበት ሙከራ አቻ ሊያደርጋቸው የቀረበ ነበር። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት አዳማ ከተማዎች ጫን ብለው ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን በ40ኛው ደቂቃ ላይ ነብል ኑሪ በግራ መስመር በኩል ተከለካዮችን አታሎ በማለፍ ግብ ጠባቂው ጋር ደርሶ ያልጠነከረ ኳስ መጥቶ ግብ ጠባቂው ሲመልስበት በ41ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ በንክኪ የተገኘውን ኳስ ሙሴ ከበላ አሻግሮለት ሙሴ ኪሮስ ጠንከር ያለ ኳስ ወደግብ መጥቶ ሶፎንያስ ሰይፈ ሸፍኖ መልሶባቸው አጋማሹ በምዓም አናብስቶች 1-0 መሪነት ተገባዷል።
ከመልበሻ ክፍል መልስ አዳማዎች ወደፊት ለመሄድ ጥረት ሲያደርጉ በመልሶ ማጥቃት ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል የደረሱት ምዓም አናብስቶች ተጨማሪ ግብ ሁለተኛ አጋማሽ ከመጀመሩ ገና በማለዳው አግኝተዋል። በ47ኛው ደቂቃ ላይ የቆመ ኳስ ሄኖክ አዱኛ ወደ ግብ አሻምቶ ቤንጃሚን ኮቴ በግንባሩ ገጭቶ መረብ ላይ አክሎ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። የአዳማ ከተማዎችን ብልጫን ያስተዋልንበት አጋማሹ ቶሎ ቶሎ ወደ ሳጥን የሚደርሱ የሽግግር አጨዋወቶችን ያየንበት ሲሆን በርከት ብለው በመግባት የምዓም አናብስቶችን የተከላካይ መስመር በመፈተን ሙከራዎችን ያደረጉበት ነበር። በ52ኛው ደቂቃ ላይ አዳማ ከተማዎች የቆመ ኳስ አማካኝነት አድርገው ሶፎንያስ ሰይፈ አውጥቶባቸዋል።
በሁሉተኛው አጋማሽ ረጃጅም የሆኑ ኳሶች ወደተቀራኒ ቡድን ተከላካይ መስመር በመጣል ያገኟቸው የነበሩ ኳሶች ደግሞ ወደግብ ሲመቱ የነበሩት ምዓም አናብስቶች በመልሶ ማጥቃት አደጋ ለመፍጠር ቢሞክሩም የአዳማ ከተማዎችን ተከላካዮች የፈተኑ አልነበሩም። ሆኖም ግን ጨዋታው 73ኛው ደቂቃ ላይ ስደርስ ቦና አሊ በፈጣኝ ሽግግር ኳስ ይዞ ገብቶ ከሳጥን ውጪ ሆኖ የመታውን ኳስ ዳንኤል ተሾመ ጨርፎ ወደ ውጪ ያወጣባቸው አጋጣሚ በአጋማሹ ለምዓም አናብስቶች ሶስተኛውን ግብ ለማስገኘት የቀረበ ሙከራ ነበር።
ጨዋታው ወደመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ሲያመራ የአዳማ ከተማዎች ጫና በርቶት ተጨማሪ ሙከራዎችን አድርገው አስቆጪ የሚባል አጋጣሚ የፈጠሩ ሲሆን 93ኛው ደቂቃ ላይ አሜ መሐመድ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ አግኝቶ ያደረገውን ሙከራ ሶፎንያስ ሰይፈ መልሶባቸው ጨዋታው በምዓም አናብስቶች 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።