ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን በአስደናቂ ግስጋሴው ቀጥሏል

የአቡበከር ሳኒ የ84ኛ ደቂቃ ግብ ኢትዮጵያ መድንን አምስተኛ ተከታታይ ድላቸውን አስጨብጣለች።

ኢትዮጵያ መድን በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት ባህር ዳር ከተማን የረታውን ስብስብ ሙሉ ለሙሉ ሳይቀይሩ ለዛሬው ጨዋታ የተጠቀሙ ሲሆን በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጨረሻ ጨዋታቸው ፋሲል ከነማን ሲረቱ ከተጠቀሙበት የመጀመሪያ አስራ አንዳቸው ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ኪሩቤል ደሳለኝን በኤርምያስ ሹምበዛ ብቻ ተክተው ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።


በኢትዮጵያ ቡናዎች አንፃራዊ የበላይነት በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቡናማዎቹ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ምንም እንኳን የጠሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ባይችሉም በኳስ ቁጥጥር ሆነ የተሻለ ወደፊት ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ አስተውለናል።

በ17ኛው ደቂቃ በግሩም የቅብብል ሂደት ኦካይ ጁል ከተከላካይ ጀርባ ያደረሰውን ኳስ በፍቃዱ ዓለማየሁ ሞክሮ አቡበከር ኑራ በቀላሉ የያዘበት ኳስ በቡናማዎቹ በኩል እጅግ አስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።

በሂደት ተመጣጣኝ መልክን ይዞ በቀጠለው ጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን ለመውሰድ ሙከራ ሲያደርጉ የተመለከትን ሲሆን በሙከራ ረገድ እጅግ ቀዝቃዛ በነበረው አጋማሽ ምናልባት በ36ኛው ደቂቃ ወገኔ ገዛኸኝ ከዳዊት ተፈራ የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ከሳጥን ጠርዝ በቀጥታ ያደረጋት እና ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት ኳስ ሌላኛዋ የአጋማሹ ሙከራ ነበረች።

ከዕረፍት መልስ አጋማሹን በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የጀመሩት ኢትዮጵያ መድኖች በ50ኛው ደቂቃ ከይታገሱ ታሪኩ በተነጠቀ ኳስ በጀመረ የማጥቃት ሂደት ዳዊት ተፈራ ባደረገውን እና ዳንልድ ኢብራሂም ባመከነበት ሙከራ በጀመረው አጋማሹ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ እምብዛም በሙከራዎች የታጀበ አልነበረም።

በአቻ የሚጠናቀቅ ይመስል በነበረው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኖች በ84ኛው ደቂቃ በድንገት እጅግ ወሳኙን ሦስት ነጥብ ያሳኩበትን ግብ አግኝተው ፤ ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስን ከግብ ጠባቂያቸው ለማስጀመር ባደረጉት ጥረት የሰሩትን ስህተት ተከትሎ አቡበከር ሳኒ ያገኘውን ኳስ ከግብ ክልሉ ጠርዝ በቀጥታ በመምታት ያስቆጠራት ኳስ መድንን ወሳኝ ሦስት ነጥብ አስጨብጣለች።


በ86ኛው ደቂቃ አንተነህ ተፈራ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር በመግጨት ያደረጋት ሙከራ ለጥቂት ዒላማዋን ሳትጠብቅ ቀረች እንጂ ኢትዮጵያ ቡናን አቻ ለማድረግ የቀረበች ሙከራ የነበረች ሲሆን በተጨማሪ ደቂቃ መሀመድ አበራም የቡድኑን መሪነት ማሳደግ የምትችል ሙከራ ቢያደርግም ዳናልድ ኢብራሂም አድኖበት ጨዋታው በኢትዮጵያ መድኖች የ1-0 የበላይነት መቋጨቱን ተከትሎ መድኖች በ29 ነጥቦችን ሊጉን መምራታቸውን ቀጥለዋል።