የጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ ፍልምያ ጨምሮ በ16ኛው ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ዕለት የሚከናወኑ መርሀ-ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
መቻል ከ ባህርዳር ከተማ
በደረጃ ሰንጠረዡ የላይኛው ፉክክር የሚገኙት መቻል እና ባህርዳር ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ የሳምንቱ ተጠባቂ መርሀ-ግብር ነው።
ሀያ ስድስት ነጥቦችን ይዘው በሁለተኛ ደረጃነት የተቀመጡት መቻሎች በመጨረሻዎቹ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተው መውጣታቸው ተከትሎ መሪነታቸውን ለማስረከብ ተገደዋል።
በድሬዳዋ ከተማ እስከ አስረኛው ሳምንት የነበረው ግስጋሴ እየራቀው የሚገኘው ቡድኑ በመጀመርያዎቹ አስር ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው ሰላሣ ነጥብ ሀያ አንዱን ማሳካት ቢችልም በቅርብ ሳምንታት ግን ተቀዛቅዟል። ቡድኑ ሊጉ በአዳማ ከተማ መደረግ ከጀመረ ወዲህ ካከናወናቸው አራት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ሁለት ነጥብ ሰባቱን ጥሎ አምስት ነጥቦች መሰብሰቡም በነጥብ ረገድ መቀዛቀዝ እንዳሳየ ማሳያ ነው። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎቻቸው በተከታታይ ነጥብ የተጋራው ቡድኑ በነገው ዕለት ወደ ድል መንገድ መመለስ ካልቻለ ከፉክክር አንድ እርምጃ ወደ ኃላ የሚቀርበት ዕድል ሰፊ ስለሆነ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ከሚጠበቀው መርሀ-ግብር ሙሉ ነጥብ ማሳካት ግድ ይለዋል።
በሀያ ሁለት ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የጣና ሞገዶቹ በመጨረሻው ሳምንት በኢትዮጵያ መድን ከገጠማቸው ሽንፈት ለመገገም እና9 ደረጃቸውን ለመሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በአርባምንጭ ከተማ ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላ ለስምንት የጨዋታ ሳምንታት ከሽንፈት ርቀው የቆዩት ባህርዳር ከተማዎች በቅርብ ሳምንታት መጠነኛ መንገራገጭ ተስተውሎባቸዋል። ከመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ሁለት አቻ፣ አንድ ድል እና አንድ ሽንፈት ያስተነገደው ቡድኑ በተጠቀሱት መርሀ-ግብሮች ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ቡድኖች ጋር መጫወቱ ለመቀዛቀዙ እንደ ምክንያትነት ሊጠቀስ የሚችል ነጥብ ቢሆንም በተከታታይ ነጥብ መጣል ከፉክክሩ እንዲርቅ ልያደርገው ስለሚችል በብዙ መንገድ ተሻሽሎ መቅረብ ይኖርበታል። ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ ያለው ጥንካሬ ማስቀጠም ቢችልም በማጥቃት ሂደት ውስጥ ያለበትን ክፍተት ቀርፎ መቅረብ በእጅጉ ያስፈልገዋል።
በባህር ዳር ከተማ በኩል ሁሉም የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በመቻል በኩል ዮዳሄ ዳዊት ከጉዳት ተመልሶ ልምምድ ቢጀምርም ለነገው ጨዋታ የማይደርስ ሲሆን በባለፈው ጨዋታ ላይ ጉዳት አስተናግዶ የወጣው ሽመልስ በቀለ ልምምድ መሥራት ቢጀምርም በጨዋታው ላይ የመሰለፉ ነገር ነገ የሕክምና ባለሙያዎች በሚሰጡት ውሳኔ የሚታወቅ ይሆናል። ሌሎቹ የቡድን አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራም ከነገ ጀምሮ ቡድናቸው የሚመሩ ይሆናል።
ሁለቱ ቡድኖች 8 ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱ በእኩሌታ ሦስት ጨዋታዎች ስያሸንፉ ሁለቱ አቻ ተጠናቋል። ጦሩ 11፣ ሞገዱ 10 አስቆጥረዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሀዋሳ ከተማ
ወደ መሪዎቹ ይበልጥ ለመጠጋት የሚያልመው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ወሳኝ ድል ከሚያስፈልገው ሀዋሳ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሀ-ግብር ነው።
ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ከመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎቻቸው ምንም ነጥብ ያልጣሉት ፈረሰኞቹ ወደ ዋንጫ ፉክክሩ በትክክል መምጣታቸውን ለማረጋገጥ ከነገው ጨዋታ ይዘው የሚወጡት ውጤት እጅግ ወሳኝ ይሆናል።
በአዳማ እጅግ ውጤታማ ጊዜ በማሳለፍ ላይ የሚገኙት እና ከሦስት ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ተከታታት ድሎች ማስመዝገብ የቻሉት ፈረሰኞቹ በድሬዳዋ ከተማ የመጨረሻ ሳምንታት በጎል ፊት የነበራቸው አባካኝነት መቅረፋቸው በውጤት ጎዳና እንዲጎማለሉ አድርጓቸዋል። በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወታቸውም በዋነኛነት የሚጠቀስ ጠንካራ ጎናቸው ነው። ጊዮርጊሶች በነገው ዕለት ከመሪው መድን ያላቸው የአምስት ነጥብ ልዩነት ለማጥበብ የሚረዳቸውን ድል ለማግኘት ነው ወደ ሜዳ የሚገቡት። ከተከታታይ አራት ድሎች በኋላ መምጣታቸው ደግሞ በጥሩ የአዕምሮ ደረጃ ላይ እንዲገኙ እንደሚረዳቸው ይታመናል።
በወራጅ ቀጠናው የሚገኘው ሀዋሳ የመጨረሻ ድሉን ሀድያ ሆሳዕና ላይ ካስመዘገበ ድፍን አስር የጨዋታ ሳምንታት አልፈዋል። ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ በሁለት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት መጠነኛ እፎይታ አግኝቶ የነበረው ሀዋሳ ከተማ በመጨረሻው ጨዋታ በአርባምንጭ ከተማ ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ በወራጅ ቀጠናው ለመርጋት ተገዷል።
የቡድኑ ዋነኛ ችግር የጎል ማስቆጠር ድክመት ነው። ምንም እንኳን ከአምስት ሳምንታት የግብ ድርቅ በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ ግብ ማስቆጠር ቢችልም አሁንም ከባድ ስራ እንደሚቀራቸው እሙን ነው። ስብስብ ደረጃ የተሻሉ ተጨዋቾችን የያዘው ቡድኑ ከፍተኛ የአፈፃፀም ችግር ይስተዋልበታል። ቡድኑ በተለይም በቅርብ ሳምንታት የግብ አጋጣሚዎችን በመፍጠር የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችልም በተጋጣሚ የመከላከል ወረዳ በሚፈጠሩ የውሳኔ እና የአፈፃፀም ስህተቶች ግቦችን ለማስቆጠር ሲቸገር ተስተውሏል። በነገው ጨዋታም በጥሩ ወቅታዊ አቋም ያለና ውጤታማ የፊት መስመር ያለው ቡድን እንደመግጠማቸው ጨዋታውን ሊያከብድባቸው እንደሚችል ይገመታል።
በፈረሰኞቹ በኩል ባለፈው ሳምንት በቅጣት ምክንያት አንድ ጨዋታ ያመለጠው አጥቂው አማኑኤል ኤርቦ ወደ ጨዋታ ይመለሳል። ተከላካዮ አማኑኤል ተርፉም ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ልምምድ ቢመለስም ለነገው ጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ነው እንዲሁም አጥቂው ዳግማዊ አርአያ ጉዳት ላይ በመሆኑ ከነገው ጨዋታ ውጭ ነው። ከዚህ ውጭ የአዳማ ቆይታቸውን በድል ጎዳና እየተጓዙ ያሉት ፈረሰኞቹ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በሀዋሳ ከተማ በኩል በረከት ሳሙኤል ቡድኑ ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ ላይ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ መውጣቱን ተከትሎ በቅጣት የነገው ጨዋታ ሲያመልጠው እንዲሁም በጨዋታው ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ የወጣው እስራኤል እሸቱ በጉዳት የነገው ጨዋታ ያመልጠዋል። ከዚህ በተጨማሪ የፊት መስመር ተጫዋቹ ዮሴፍ ታረቀኝ እስከአሁን ወደ ቡድኑ እንዳልተቀላቀለ ሰምተናል።
ሁለቱ ቡድኖች 49 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 29 ጊዜ ባለድል ሲሆኑ ሀዋሳ ከተማ 8ጊዜ አሸንፈዋል። ቀሪዎቹ 12 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። ፈረሰኞቹ 85፣ ሀይቆቹ 37 ግቦች አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት አልተካተተም)