ሪፖርት | ተጠባቂው ጨዋታ ያለአሸናፊ ተጠናቋል

መቻልን ከባህርዳር ከተማ ያገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ መርሃግብር 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ያለአሸናፊ ተጠናቋል።

መቻል በ15ኛው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ ተጋርተው ከወጡበት ቋሚያቸው አራት ለውጦችን ሲያደርጉ ዳዊት ማሞን በዓለምብርሃን ይግዛው ፣ምንይሉ ወንድሙን በአማኑኤል ዩሐንስ፣ ዳንኤል ዳርጌን በአቤል ነጋሽ እና ሽመልስ በቀለን በአብዱ ሙታለብ ተክተው ሲገቡ ባህርዳር ከተማ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከኢትዮጵያ መድን ሽንፈት ከቀመስቡት ስብስባቸው ሶስት ለውጥ በማድረግ ፍፁም ፍትዓለሙን በወንድሜነህ ደረጀ፣ ወንደሰን በለጠን በሆኖክ ጥጋቡ እና ጄሮም ፈሊፕን በቸርነት ጉግሳ ቀይረው ቀርበዋል።

ከጅምሩ አንስቶ በሙከራዎች የታጀበው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በሚያደርጉት ፈጣኝ ሽግግር ጥሩ ፉክክር አስመልክቷል ፤ በ3ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅበብል ያገኘውን ኳስ በረከት ደስታ በደካማ እግሩ ከፍ አድርጎ ካመከነው ሙከራ በኋላ በድጋሚ በ8ኛው ደቂቃ ላይ ከበረከት ደስታ የተሻገረለትን ኳስ በሀይሉ ግርማ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አክርሮ የመታው ኳስ ከግብ አግዳሚ ለትንሽ ከፍ ያለበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ነበሩ።

ባህርዳር ከተማዎች በአንፃሩ በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ምንም እንኳን ወደፊት ቢሄዱም ፈታኝ የሚባል ሙከራ በማድረግ ብልጫ ተወስዶባቸዋል ፤ በ10ኛው ደቂቃ ላይ በመቻል ተከላካዮች ስህተት መነሻ የተገኘውን ኳስ መሳይ አገኘሁ ከመሃል ሜዳ ቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ ያደረገው ሙከራንም የግብ አግዳሚ መልሶበታል።

ጫን ብለው ግብ ማነፍነፋቸውን የቀጠሉት መቻሎች ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ አግኝተዋል። 16ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ እና አቤል ነጋሽ በአንድ ሁለት ንክኪ ካደረጉ በኋላ አቤል ነጋሽ ኳስን እየገፋ ወደ ሳጥን ተጠግቶ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አክርሮ በመምታት ግሩም ግብ መረብ ላይ አሳርፏል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ወደፊት የገሰገሱት የጣናው ሞገዶች አከታትለው ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን በተለይም 19ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም በግንባሩ ገጭቶ ከግብ ቋሚ አናት ያለፈችበት ሙከራ አቻ ለመሆን ያቀረባቸው ነበር።

በተመጣጣኝ ፉክክር በቀጠለው በአጋማሹ ሁለቱም ቡድኖች ኳስን በሚገባ ተቆጣጥረው  ተረጋግተው በመጫወት ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል በመሄድ በሚያደርጉት ግብ ማግባት እንቅስቃሴዎች ጨዋታው ሳቢ እንዲሆን አድርጎታል።

የአቻነት ግብ ፍለጋ ጫን ብለው በፈጣን ሽግግር የጦሩን ግብ ክልል ሲጎበኙ የነበሩት የጣናው ሞገዶች እስከ ሰላሳዎቹ ደቂቃ መዳረሻ ድረስ መጠበቅ ግድ ሆኖባቸዋል። ጨዋታው 39ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ በቸርነት ጉግሳ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ በመታት ኳስ አቻ መሆን ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ተመልሶ ቡድኖቹ በኳስ ቁጥጥር እየተፈራረቁ ብልጫ በመውሰድ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚዎቻቸው ግብ ክልል ቢደርሱም ጠንከር ያለ አደገኛ የሚባል ሙከራ ሳያስመለክቱ ጨዋታው እስከ ስልሳኛው ደቂቃ ድረስ ዘልቋል።

65ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ ኳስ እየገፋ ይዞ ገብቶ ሳጥን ውስጥ ተመቻችቶ ሲጠባበቅ ለነበረው ሙጂብ ቃሲም በሁለት ተከላካዮች መካከል አሻግሮለት ያለቀ ኳስ አግኝቶ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ለግብ ጠባቂው ያሳቀፈው አስቆጪው የባርህዳር ከተማዎች ሙከራ ይጠቀሳል።

እንደመጀመሪያው አጋማሽ በግብ ማግባት ሙከራዎች መታጀብ ባልቻለው በአጋማሹ ቡድኖቹ የፊት መስመራቸውን ለማጠናከር የተጫዋቾች ቅያሪ ቢያደርጉም እንቅስቃሴዎቹ እንዳሰቡት ሳይሆን ቀርቶ ግብ ለማስቆጠር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እየተቆራረጠባቸው ሲቸገሩ አስተውለናል።

ወደፊት በመሄዱ ረገድ ብልጫ የነበራቸው ባህርዳር ከተማዎች 82ኛው ደቂቃ ላይ በርከት ብለው ገብተው በአንድ ሁለት ቅብብል የተገኘውን ሙከራ በሄኖክ ይበልጣል አማካኝነት አድርገው አልዌንዚ ናፊያን እንዴትም ብሎ መልሶባቸዋል።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ጭማሪ በታየው ላይ ባህርዳር ከተማዎች አከታትለው ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችን የፈጠሩ ቢሆንም ወደግብነት ሳይቀይሩ ቀርተው ተጠባቂው ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት ያለአሸናፊ ተጠናቋል።