ሪፖርት | የፈረሰኞቹ የአሸናፊነት ጉዞ በሀይቆቹ ተገቷል

ፈረሰኞቹን በወራጅ ቀጠናው እየዳከሩ ከሚገኙት ሀይቆቹ ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ15ኛው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ከረቱበት ቋሚ አሰላለፋቸው ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ሲገቡ ሀዋሳ ከተማ በአንፃሩ በ15ኛው ሳምንት ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ቋሚ ስብስባቸው አራት ለውጦችን በማድረግ በረከት ሳሙኤልን በሰለሞን ወዴሳ ፣ፍቃደስላሴ ደሳለኝን በፀጋአብ ዩሐንስ፣ ታፈሰ ሰለሞንን በአቤኔዘር ዩሐንስ እና አማኑኤል ጎበናን በብሩክ ኤልያስ ተክተው ገብተዋል።


ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ በጀመረው ጨዋታ ቡድኖቹ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች መረጋጋት ተስኗቸው ያስተዋልንበት ነበር።

ጨዋታው ሀያ ደቂቃን ሲሻገር ወደ ጨዋታ የመግባት ፍንጭን ማሳየት የጀመሩት ፈረሰኞቹ በአጫጭር ቅብብሎች ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አስተውለናል ፤ ሆኖም ግን የሀይቆቹን ተከላካይ መስመር የፈተኑ ኳሶችን ወደሳጥን ይዘው ሲገቡ ሳንመለከት ደቂቃዎች ገፍተዋል።

እምብዛም የግብ ማግባት ሙከራዎች ባላስመለከተው በአጋማሹ ሁለቱም ቡድኖች ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የተጫወቱበት ነበር ፤ የኋላ ኋላ ግን ግለቱ እየጨመረ በመጣው በአጋማሹ በ41ኛው ደቂቃ ላይ ፈረሰኞቹ መሪ መሆን የቻሉበትን ኳስ መረብ ላይ አሳርፈዋል።

ከመሃል ሜዳ አካባቢ በረከት ወልዴ ለፍፁም ጥላሁን መሬት ለመሬት ሲያሻግርለት ኳስ ተከላካዮችን ቀንሶ በሳጥኑ ቀኝ ጠርዝ ላይ ብቻውን ለነበረው ቢኒያም ፍቅሩ ያቀበለውን ኳስ ቢኒያም ፍቅሩ ኳሷን መሬት ለመሬት ወደግብ በመምታት ከመረብ አሳርፏል።

ግብ አስተናግደው ቶሎ ወደ ጨዋታው የተመለሱት ሐይቆቹ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጫን ብለው ወደፊት በመሄድ አራት ደቂቃ ብቻ ጠብቀው 45ኛው ደቂቃ ላይ በአቤኔዘር ዩሐንስ ግሩም ግብ አቻ መሆን ችለዋል።

በግራ መስመር በኩል በቅብብል የተገኘውን ኳስ ብሩክ ኤልያስ ከሳጥኑ ቅርብ ርቀት ላይ ክፍት ለነበረው አበኔዘር ዩሐንስ አሻግሮለት አክርሮ ወደ ግብ በመምታት ከመረብ ጋር ያገናኛት ኳስ አጋማሹ በአቻ እንዲገባደድ አስገድዳለች።

ከዕረፍት መልስ በ52ኛው ደቂቃ ላይ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ የፈረሰኞቹ የፊት መስመር ተጫዋች ቢኒያም ፍቅሩ በፍጥነት ደርሶ ሳጥን ውስጥ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ወደግብ ለመምታት ጥረት አድርጎ ኳሷን ሳያገኘው የቀረው አስቆጪው አጋጣሚ የአጋማሹ ቀዳሚ ሙከራ ነበረች።

በጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ወደፊት በመሄድ ረገድ ደካማ የነበሩ ሲሆን ይልቁንስ በፈጣኝ ሽግግሮች ቶሎ ቶሎ ወደግብ የመድረስ ሂደት ተደጋግሞ ታይቷል።

በ70ኛው ደቂቃ ላይ ከተጠባባቂ ወንበር የተነሳው አማኑኤል ኤርቦ ሳጥን ውስጥ ሆኖ መሬት ለመሬት ወደግብ ያሻገረውን ኳስ ሰይድ ሀብታሙ እንዴትም ብሎ ጨርፎ ወደ ውጪ ያወጣበት አጋጣሚ ፈረሰኞቹን ዳግም ወደ መሪነት ለመመለስ የቀረበች ሙከራ ነበረች።

በሂደት ቡድኖቹ ይበልጥ ተጠናክረው በፈጣን ሽግግር ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚዎቻቸው ግብ ክልል በደረሱበት በመጨረሻዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች በመልሶ ማጥቃት በረጃጅም ኳሶች ወደ ተጋጣሚያቸው ግብ ሲደርሱ ቢስተዋሉም በጥንቃቄ የኋላ መስመራቸውን በማጠናከራቸው አልፈው ግብ ለማስቆጠር ተቸግረዋል ጨዋታው በአቻ ውጤት ተገባዷል።