የ16ኛው ሳምንት ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይገባደዳል፤ የጨዋታ ሳምንቱ መቋጯ የሆኑ መርሀ-ግብሮች አስመልክተን ያዘጋጀናቸው መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ ሀድያ ሆሳዕና
የተለያየ መልክ ያለው የውድድር ዓመት በማሳለፍ የሚገኙት ቢጫዎቹ እና ነብሮቹ የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሀ-ግብር ነው።
በደረጃ ሰንጠረዡ በሊጉ ግርጌ የሚገኙት ወልዋሎዎች ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ነጥብ ካስመዘገቡበት ጨዋታ መልስ ከነብሮቹ ጋር ይፋለማሉ።
አስከፊ የውድድር ዓመቱን መቀልበስ የተሳነው ወልዋሎ የመጀመሪያ ድሉን ለማሳካት የሚያደርገውን ጥረት ጠንካራው ሀድያ ሆሳዕና ላይ ለማሳካት የነገውን ጨዋታ ይጠብቃል። ነገም የተስፋ ጭላንጭልን ፍለጋ ወደ ሜዳ የሚገባው ቡድኑ በውድድር ዓመቱ በጨዋታ በአማካይ 1.3 ግቦችን ያስተናገደ መሆኑ እንዲሁም በሊጉ ሦስት ግቦች ብቻ ማስቆጠሩ ስለመከላከል እና የማጥቃት አደረጃጀቱ ሁሉንም ነገር የሚጠቁሙ ነጥቦች ናቸው። በነገው ዕለትም በኋላ ክፍሉ ላይ የሚታይበት ዘርፈ ብዙ ችግር አብሮት የሚኖር ከሆነ ከፍ ያለ ተነሳሽነት በሚታይባቸው የነብሮቹ አጥቂዎች ዳግም መቀጣቱ የሚቀር አይመስልም።
አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ከተጋጣሚያቸው ጥንካሬ አንፃር ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀታቸው ማስተካከል ቀዳሚ ስራቸው መሆን ይገባዋል።
በሀያ ስድስት ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ነብሮቹ ከመሪው ጋር በነጥብ እንዲስተካከሉ የሚያስችላቸውን ድል ፍለጋ ለማግኘት ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ስድስት ተከታታይ ድሎች ካስመዘገቡ በኋላ ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ ተጋርተው መሪነታቸውን ለማስረከብ የተገደዱት ነብሮቹ በመጨረሻው ሳምንት ንግድ ባንክን በማሸነፍ ዳግም ወደ ድል ተመልሰዋል። በነገው ዕለትም በአንፃራዊነት ቀለል ያለ ተጋጣሚ በሚያገኙበት ጨዋታ ድል ማድረግ ከመሪው ጋር በነጥብ እንዲደላደሉ ያስችላቸዋል።
ሀድያ ሆሳዕናዎች በድሬዳዋ ከተማ የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ማስቆጠር ቢችሉም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ያስቆጠሯቸው ግቦች ግን ሦስት ናቸው። ቡድኑ ከተጋጣሚው አሁናዊ ሁኔታ አኳያ በአዳማ በተከናወኑ ሦስት ጨዋታዎች ካሳየው የበዛ ጥንቃቄ የተሞላበት አቀራረብ ነገ ይበልጥ በተጋጣሚው ሜዳ ላይ የመቆየት ድፍረትን ተላብሶ እንደሚቀርብ ይጠበቃል።
በሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል የሚፎካከር ጠንካራ ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በነገው ዕለትም በተመሳሳይ ለመስመር ተጫዋቾቹ ከፍ ያለ የማጥቃት ኃላፊነት ሰጥቶ እንደሚገባ ይገመታል።
በወልዋሎ በኩል ዳዊት ገብሩ፣ ሱልጣን በርሐ እና ታዬ ጋሻው በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ ናትናኤል ዘለቀ ከጉዳት ተመልሷል። በሀድያ ሆሳዕና በኩል ተመስገን ብርሀኑ እና ጫላ ተሺታ ከጉዳታቸው አገግመው ወደ ልምምድ ቢመለሱም ነገ ጨዋታ የመድረሳቸው ነገር አጠራጣሪ ነው። ዳግም ንጉሴ ፣ በረከት ወንድሙ እና መለሰ ሚሻሞ ገና ከጉዳታቸው ሙሉ ለሙሉ ያላገገሙ በመሆኑ ከነገ ጨዋታ ውጭ መሆናቸው እርግጥ ሆኗል። የተቀሩት የነብሮቹ የቡድን ስብስብ ግን ለነገው ወሳኝ ፍልሚያ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠናል።
የነገው ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ የሚያደርጉት የመጀመርያ ግንኙነት ነው ( የተሰረዘው እና በሀድያ ሆሳዕና አንድ ለባዶ አሸናፊነት የተጠናቀቀው የ2012 ውድድር ዓመት ጨዋታ አያካትትም)።
ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
በአራት ነጥቦች እና በአንድ ደረጃ ልዩነት የተቀመጡት ቡድኖች የሚያገነኘው ጨዋታ የሳምንቱ መገባደጃ መርሀ-ግብር ነው።
በአስራ ዘጠኝ ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች መልስ ድል አድርገው ደረጃቸው ለማሻሻል ኢትዮ ኤሌክትሪክን ይገጥማሉ።
ጥሩ አጀማመር ካደረጉ ቡድኖች ውስጥ የሚጠቀሰው ሲዳማ ቡና በድሬዳዋ ከተማ ካደረጋቸው የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ይዞ መውጣቱ ተሰጥቶት የነበረውን ግምት እንዲሸረሸር አድርጓል። እርግጥ ቡድኑ በተከታታይ ሳምንታት ካሳየው መጥፎ ውጤት አገግሞ በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ከሽንፈት ቢርቅም ከሦስት መርሀ-ግብሮች በፊት አርባምንጭ ላይ ያሳካው ወሳኝ ድል ለመድገም በብዙ ረገድ መሻሻል ይገባዋል። በመደዳ ሦስት ሦስት ግቦች አስተናግዶ ድሬዳዋን የተሰናበተው ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት በመከላከሉ ረገድ ያሳየው ለውጥ በአወንታነቱ የሚነሳለት ትልቁ ነጥብ ነው፤ ቡድኑ በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ በማስተናገድ የቀደመው ደካማ የመከላከል ብቃቱ ማስተካከል ቢችልም በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ያለው ውጤታማነት ከፍ ማድረግ የሚገባው ጉዳይ ነው።
በሊጉ የመጀመርያ መርሀ-ግብር ሽንፈት ካስተናገዱ ወዲህ ለዘጠኝ የጨዋታ ሳምንታት ሽንፈት አልባ ጉዞ ማድረግ ችለው የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከገጠማቸው ሦስት ተከታታይ ሽንፈት ለማገገም ሲዳማ ቡናን ይገጥማሉ።
ኤሌክትሪኮች በአስራ አምስት ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ በወራጅ ቀጠናው አፋፍ ይገኛሉ።
ድል ካደረገ ስድስት ጨዋታዎች ያስቆጠረው ቡድኑ በድሬ ካሳየው ብቃት አንፃር በአዳማ ቆይታው በብዙ መመዘኛዎች ተዳክሞ ተከታታይ ጨዋታዎች ለመሸነፍ ተገዷል። ከወልዋሎ እና ሀዋሳ ከተማ በመቀጠል ከስሑል ሽረ ጋር በእኩሌታ ጥቂት ግቦች በማስቆጠር 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኤሌክትሪክ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በአንድ አጋጣሚ ብቻ ኳስና መረብ ማገናኘቱ የፊት መስመሩ ያለበት አሁናዊ ሁኔታ ማሳያ ነው።
በነገው ጨዋታም ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የኋላ ክፍላቸውን በማስተካከል ባለፉት አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገዱት ሲዳማ ቡናዎች እንደመግጠማቸው የፊት መስመራቸውን ማስተካከል ይኖርባቸዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ አብዱላሂ አላዩ እና በፍቃዱ አስረሳህኝ አሁንም ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆናቸው ሲታወቅ አብዱላዚዝ አማን ከጉዳት መልስ ለነገው ጨዋታ ሲደርስ የተቀሩት የቡድኑ አባላት ዝግጁ መሆናቸውን አውቀናል። የሲዳማ ቡና የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ቡድኖቹ እስካሁን 20 ጊዜ ተገናኝተው ኤሌክትሪክ 7 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ሲዳማ ቡና 5 አሸንፎ በ 8 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ኤሌክትሪክ 17 ሲዳማም በተመሳሳይ 17 ጎሎችን አስቆጥረዋል።