ከፍተኛ ሊግ | ደደቢት አዲስ አሰልጣኝ ቀጥሯል

የቀድሞ ተጫዋቾቹን ወደ አሰልጣኝ ቡድኑ ያካተተው ደደቢት አዲስ ዋና አሰልጣኝ ሲሾም ስድስት ተጫዋቾችም አስፈርሟል።

በከፍተኛ ሊጉ በምድብ “ሀ” ተደልድሎ ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች 12 ነጥቦችን በመሰብሰብ 8ኛ ደረጃን ይዞ የመጀመሪያውን ዙር ያጠናቀቀው ደደቢት አዲስ አሰልጣኝ መሾሙን እና የስድስት ተጫዋቾችን ዝውውር ማጠናቀቁን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ቡድኑን የተረከበው አሰልጣኝ አዲስ ዶይሶ (ወይዲዴ) ነው። በተጫዋችነት ለደቡብ ፖሊስ ፣ ኒያላ እና ኦሜድላ ከተጫወተ በኋላ በ2004 ወደ አሰልጣኝነት የገባው አሰልጣኙ ከፋ ቡና ፣ ቡሌ ሆራ ፣ ሀድያ ሌሞ ፣ እንጅባራ ከተማ እና ዱራሜ ከተማን አሰልጥኗል። በዚህም በ2013 እንጅባራን በ2016 ደግሞ ዱራሜን ወደ ከፍተኛ ሊግ ያሳደገው አሰልጣኝ ባለፈው ዓመት በነበረበት ዱራሜ ከተማ ውሉን አራዝሞ እስከ ዘንድሮ ግማሽ ዓመት በከፍተኛ ሊጉ ማሰልጠን የቻለ ሲሆን አሁን ደግሞ ደደቢትን ለማሰልጠን ፊርማውን አስቀምጧል።

ደደቢት አሰልጣኙ በመጀመሪያው ዙር ካሳለጠነው ክለብ ዱራሜ ግብ ጠባቂውን ቅዱስ ዳኜ ፣ የመሃል ተከላካዩን ሚሊዮን ተፈራ ፣ አማካዩን ወንድማገኝ ኢያሱን እና የፊት አጥቂውን ተመስገን ገብረጻድቅን ሲያስፈርም የጅማ አባ ቡናውን የቀኝ መስመር ተከላካይ ሚኪያስ ታምራት እንዲሁም የደብረብርሃኑን የመስመር አጥቂ ማሞ አየለም ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።