ቡልቻ ሹራ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ቢጫዎቹ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ሀዲያ ሆሳዕና ላይ ተቀዳጅተዋል።
ወልዋሎዎች በ15ኛው ሳምንት ከሀዋሳ ጋር 1ለ1 የተለያዩበትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ሲቀርቡ ሀዲያዎች በአንጻሩ ግብ ጠባቂ ላይ ያሬድ በቀለን አሳርፈው ሳሚኪ ሚኬልን ሲያስገቡ ፀጋአብ ግዛውንም በሄኖክ አርፊጮ ተክተው አስገብተዋል።
9 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ተፈሪ አለባቸው መሪነት የተጀመረው ጨዋታ በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል መቀዛቀዞች የታየበት ነበር። የመጀመሪያው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራም 13ኛው ደቂቃ ላይ ተደርጎ ጋዲሳ መብራቴ ከቅጣት ምት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኪ መልሶበታል። ያንኑ ኳስ በፍጥነት አስጀምረው የወሰዱት ነብሮቹም በሴኮንዶች ልዩነት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ኢዮብ ዓለማየሁ ከቀኝ መስመር የመታውን ኳስ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል።
በሀዲያ በኩል 21ኛው ደቂቃ ላይ ኢዮብ ዓለማየሁ ከማዕዘን አሻምቶት አስጨናቂ ጸጋዬ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ እና በአንድ ደቂቃ ልዩነት የወልዋሎው ዳዋ ሆቴሳ ከረጅም ርቀት ካደረገው ኃይል የለሽ ሙከራ ውጪ ረዘም ላሉ ደቂቃዎች ተቀዛቅዞ ሲቀጥል 39ኛው ደቂቃ ላይ ግን ነብሮቹ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበት ዕድል አግኝተው ሳሙኤል ዮሐንስ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ለመግጨት ምቹ ቦታ ላይ ሆኖ ያገኘው ብሩክ በየነ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተመጣጣኝ ሆኖ ሲቀጥል ወልዋሎዎች በግሩም መግባባት 58ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል። ጋዲሳ መብራቴ ከቅጣት ምት ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ቡልቻ ሹራ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ኳሱን በመምታት ከጠባብ አንግል በድንቅ አጨራረስ ጎል በማስቆጠር ቢጫዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል።
ሀዲያዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ተጭነው መጫወታቸውን ቢቀጥሉም በተሻለ የራስ መተማመን ላይ የነበሩትን ወልዋሎዎች አልፈው የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ሆኖም 90+2ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎው ኤፍሬም ኃይለማርያም ከዳኛ ጋር በፈጠረው ሰጣ እገባ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወገድ በአንድ ደቂቃ ልዩነት ነብሮቹ በፀጋአብ ግዛው አማካኝነት ያለቀለት የግብ ዕድል ፈጥረው አስቆጪ በሆነ ሁኔታ ሳይጠቀሙበት ቀርተው ጨዋታው በወልዋሎ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱም ቢጫዎቹ በ14ኛ ጨዋታቸው በውድድሩ ያሳኩት የመጀመሪያ ድል ሆኖ ተመዝግቧል።