ሪፖርት | ኤሌክትሪክ ከ540 ደቂቃዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሰበትን ውጤት ከሲዳማ ቡና አግኝቷል

በ162 ሰከንዶች ልዩነት የተቆጠሩት የናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ሁለት ግቦች ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል መልሰዋል።

ሲዳማዎች በ15ኛ ሳምንት ከወላይታ ድቻ ጋር 0ለ0 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ጉዳት አስተናግደው ወጥተው የነበሩትን ፍራኦል መንግሥቱ እና ሐብታሙ ታደሰ አሳርፈው ደግፌ ዓለሙ እና ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃንን ሲያስገቡ ኤሌክትሪኮች በአንጻሩ በመቐለ 70 እንደርታ 1ለ0 ከተሸነፉበት አሰላለፍ በጋሻው ክንዴ ፣ ፍቃዱ ዓለሙ እና ሄኖክ ገብረሕይወትን አስወጥተው አብዱላዚዝ አማን ፣ አበባየሁ ዮሐንስ እና ኢዮብ ገብረማርያምን አስገብተዋል።

በጨዋታው የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራ ባይደረግም ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአንፃራዊነት በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመሄድ ሲጥር ታይቷል። በተቃራኒው ሲዳማ ቡና ወደ መስመር አጥቂዎቹ የሚደርሱ ረጃጅም ኳሶችን በማዘውተር የጨዋታውን ሚዛን ወደ ዳር ለማድረግ ቢጥርም የኤሌክትሪክን የመጨረሻ ሜዳ ሰብሮ መግባት ቀላል አልሆነለትም። ጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ አካፋይ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግብ ማስቆጠር ጀምሯል። በዚህም ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በ22ኛው እና በ24ኛው ደቂቃ አከታትሎ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ተደላደለ መሪነት ተሸጋግሯል። ተጫዋቹም በቅድሚያ ከቀኝ መስመር የተሰጠውን ኳስ በተከላካዮች መሀል ተገኝቶ የመጀመሪያ ግብ ሲያስቆጥር ከሁለት 60 ሰከንዶች በኋላም በፈጣን ሩጫ ከተከላካዮች ጀርባ በመሮጥ ከእዮብ ገብረማርያም የደረሰውን ኳስ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል።

ሁለቱ ተከታታይ ግቦች የረበሻቸው ሲዳማዎች አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ቢያመነቱም የኤልፓን የግብ ክልል ለመፈተን 37 ደቂቃዎችን መጠበቅ ግድ ብሏቸዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ሬድዋን ናስር በአንድ ሁለት ቅብብል ያገኘውን ኳስ መሬት ለመሬት ወደ ግብ ልኮት የግብ ዘቡ ኢድሪሱ አብዱላኢ አምክኖታል። አጋማሹም በኢትዮ ኤሌክትሪክ መሪነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለት ፈጣን የተጫዋች ቅያሪ አድርገው የገቡት ሲዳማ ቡናዎች ለማጥቃት የተሻለ ፍላጎት ቢታይባቸውም የሰላ ጥቃት ግን መሰንዘር አልቻሉም። በተቃራኒው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ወረድ ብለው መጫወትን መርጠው የመጀመሪያዎቹን ደቂቃዎች ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል። ደቂቃዎች እየገፉ በመጡ ቁጥር ግን የመልሶ ማጥቃትን እንደ ሁነኛ የግብ ምንጭ በመጠቀም ሲዳማ ለማጥቃት ከፍቶ የሚወጣውን ቦታ በፈጣን ሽግግር በማጥቃት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም ሀሳባቸው በጎል እና ሙከራዎች የታጀበ መሆን አልቻለም።

ጨዋታው 71ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ በጊዜያዊ አሰልጣኝ የሚመሩት ሲዳማዎች ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። በዚህም በአጋማሹ ተቀይሮ የገባው ዮሴፍ ዮሐንስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ ለግብነት የተቃረበ ቢሆንም የግብ ዘቡ ኢድሩሱ አድኖታል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ቢያንስ አንድ ነጥብ ለማግኘት ሙሉ ኃይላቸውን ተጠቅመው ለማጥቃት የሞከሩት ሲዳማዎች የኤሌክትሪክን የኋላ መስመር ሰብሮ መግባት ተስኗቸው ተጨማሪ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ደግሞ እጃቸው የገባውን 3 ነጥብ ይዞ ለመውጣት ታግለው በመጫወት ጨዋታውን በድል ፈፅመዋል።