የሊጉ የሁለተኛው ዙር ጨዋታዎች የትኛው ከተማ ይካሄድ ይሆን ?

አንደኛው ዙር ሊጠናቀቅ የሦስት ሳምንታት ጨዋታዎች የቀሩት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቀጣይ ሁለተኛው ዙር በየትኛው ከተማ እንደሚካሄድ ማጣራት አድርገናል።

የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን በተመረጡት ሁለት ከተሞች በድሬደዋ ከተማ እና በአዳማ ከተማ እየተከናወነ አሁን አስራ ስድስተኛው ሳምንት ላይ ደርሷል። የአንደኛው ዙር ቀሪ የሦስት ሳምንታት ጨዋታዎች በአዳማ ከተማ መካሄዳቸውን ከቀጠሉ በኋላ የካቲት ሦስት ቀን የመጀመርያው የውድድር ዘመን አጋማሽ የሚጠናቀቅ ይሆናል። ሊግ ካምፓኒው አስቀድሞ ባወጣው መርሐግብር መሠረት እስከ የካቲት አስራ ስድስት ድረስ ሊጉ ለዕረፍት የሚቋረጥ ሲሆን በቀጣይ ሁለተኛው ዙር ውድድሮች በየትኛው ከተማ ይካሄዳል የሚለው ተጠባቂ ጉዳይ ሆኗል።

ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራት ሁለተኛው ዙር እንዲካሄድባቸው ሁለት ከተሞች ማለትም አዲስ አበባ እና ሀዋሳ ከተማ እንደተመረጡ ለማወቅ ችለናል። ሁለቱ ከተሞች በዋናነት ሁለተኛው ዙር እንዲከናወንባቸው ይመረጡ እንጂ የአጋማሹ ጅማሮ ውድድር ወደ ሀዋሳ የመሄዱ ዕድል ሰፊ እንደሆነ ተሰምቷል። ግምቱን ዕውን ያደረገው ደግሞ በመዲናዋ ጨዋታዎችን ለማድረግ ሊግ ካምፓኒው አስቦ ቢንቀሳቀስም የሚሰምርለት አይመስልም። እንደ ምክንያት የሚቀርበው ደግሞ የከተማው የበላይ አካላት ፍቃደኛ የመሆን አዝማሚያው ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ ነገር አለመኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ የአዲስ አበባ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳው ሳር ብዙ ጉድለቶች እንዳሉበት እና ሳሩ መቀየር እንደሚገባው በተደጋጋሚ በማለሙያዎች ምክረ ሀሳብ መቅረቡን ተከትሎ በቅርቡ ያለውን ሳር በመንቀል አዲስ የሳር ተከላ ለማከናወን እንቅስቃሴ እየተደረገ በመሆኑና ስራው እስኪጠናቀቅ የሚወስደው ጊዜ ውድድሩን በአዲስ አበባ የማድረጉን ነገር የማይሆን አድርጎታል።

በዚህ መነሻነት ሁለተኛው ዙር በሀዋሳ ከተማ የመካሄዱ ዕድል ሰፊ ሲሆን የአወዳዳሪው አካል ገምጋሚ አካላትም ወደ ሀዋሳ በማቅናት እየተከናወኑ ያሉትን የልምምድ እና የመጫወቻ ሜዳዎችን ምልከታዎችን በማድረግ አንደኛው ዙር ከመጠናቀቁ አስቀድሞ ውድድሩ የሚካሄድበትን ቦታ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በተያየዘ ዜና የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ውድድሩ ከተጀመረ በኋላ 18 ቡድኖች መሆናቸውን ተከትሎ እንዲሁም ተስተካካይ ጨዋታችን ለማስቀረት የሁለተኛው ዙር አዲስ ዕጣ የማውጣት ስነ ስርዓት ዛሬ የሚከናወን ሲሆን በሌላ በኩል ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ የ2017 የውድድር ዘመን የመዝጊያ (የመጨረሻ ሳምንታት) ጨዋታዎች በአዳማ ከተማ እንደሚካሄድ አውቀናል።