“በዚህ ዓመት ከመቼውም ዓመት ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ሽልማት ይኖራል” አቶ ክፍሌ ሰይፈ

የሊጉ ሁለተኛ ዙር የዕጣ ማውጣት መርሐ-ግብር ላይ የሊጉ አክሲዮን ማህበር ስለ ሽልማት ምን ተናገሩ።

የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች አስራ ስምንት መሆናቸውን ተከትሎ በሁለተኛው ዙር አዲስ ፕሮግራም እየወጣ ይገኛል። በዚህ ስነ ስርዓት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአክሲዮን ማህበሩ ስራ አስኪያጅ በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ከሽልማት ጋር የተያያዘው ሲሆን “ በዚህ ዓመት ከመቼውም ዓመት በተለየ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ሽልማት ይኖራል። አሸናፊው ቡድን ከፍተኛ ገንዘብ የሚያገኝ ሲሆን በእያንዳንዱ ደረጃ በእራሱ የሚኖረው ልዩነት ከአምስት ሚሊየን ብር በላይ ሊሆን ይችላል” ብለዋል። ከፍተኛ ሽልማት እንዲኖር ያስቻለው ምክንያትም የዶላር ምንዛሪ መጨመር እንደሆነ አክለው ተናግረዋል።

አቶ ክፍሌ አያይዘው “ዲኤስ ቲቪ በኢትዮጵያ ገብያ አትራፊ አይደለም በማለት ውሉን አቋርጦ ለመውጣት አስቦ ነበር። ሆኖም ግን ወደ ክስ እናመራለን ስንለው ጨዋታውን ወደ ማስተላለፍ ተመልሷል” ሲሉ ተናግረዋል።

ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ የሊጉ አንደኛ ሆኖ የሚጠናቅቅ ቡድን ከ25 ሚሊየን ብር በላይ ሊያገኝ እንደሚችል ሲነገር ዲኤስ ቲቪ 18ኛውን እና 19ኛውን ሳምንት ጨዋታ ካስተላለፈ በኋላ በቀጣይ ወደ ቀጥታ ስርጭት የሚመለሰው የመዝጊያውን አራት ሳምንት ጨዋታዎች ብቻ እንደሚሆን ሰምተናል።