መረጃዎች | 68ኛ የጨዋታ ቀን

በ17ኛው ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ዕለት የሚከናወኑ መርሐግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ

ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ከድል መልስ የሚገናኙ ቡድኖች የሚፋለሙበት ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነው።

ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ሲዳማ ቡናን በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ነጥባቸውን አስራ ስምንት አድርሰው 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ኤሌክትሪኮች ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ድል ከማድረጋቸውም በተጨማሪ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ችለዋል። በተለይም ቡድኑ ማግኘት ከሚገባው አስራ ስምንት ነጥብ ሦስቱን ብቻ ባሳካባቸው ስድስት ድል አልባ የጨዋታ ሳምንታት ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው የፊት መስመሩ በተጠቀሱት ስድስት ሳምንታት ያስቆጠራቸውን ድምር ግቦች በአንድ ጨዋታ ብቻ በማስቆጠር ቡድኑን ወደ ድል መንገድ መልሶታል። ሜዳ ላይ ከታየው ብቃት በተጨማሪ በተሻለ የማሸነፍ መንፈስ ጨዋታውን የከወነው ቡድኑ የመጀመሪያውን ዙር ከአደጋው ቀጠና ርቆ ለማጠናቀቅ ከወልዋሎ ጋር የሚያደርገው የነገው ጨምሮ ከአዳማ ከተማ እና አርባምንጭ ጋር በሚደረጉ ወሳኝ መርሐግብሮች ነጥቦችን መሰብሰብ ይኖርበታል። ይህ እንዲሆንም
በመጨረሻው ጨዋታ የታየው የአፈጻጸም እንዲሁም አጠቃላይ የቡድኑን መንፈስ ማስቀጠል ይኖርበታል።

ሳይጠበቁ ሀዲያ ሆሳዕናን በመርታት የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ድል ያስመዘገቡት ወልዋሎዎች የ13 ሳምንታት የድል ረሀባቸው በማስታገስ ነጥባቸውን አምስት ማድረስ ችለዋል።

ወልዋሎ አሁንም ከሊጉ ግርጌ መላቀቅ ባይችልም ወሳኝ ድል በማስመዝገብ ዘግይቶም ቢሆን ነፍስ ዘርቷል። ቢጫዎቹ በውድድር ዓመቱ ድንቅ የድል ግስጋሴ ያደረገው እና ለስምንት መርሐግብሮች ሽንፈት ያልቀመሰውን ሀዲያ ሆሳዕና ማሸነፋቸውን ተከትሎ በቀጣይ ጨዋታዎች ከቀደሙት ሳምንታት ዝቅተኛ ግምት የላቀ እንዲሰጣቸው ያስገድዳል። ወልዋሎዎች ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው እና ለቀጣይ ትልቅ የሞራል ስንቅ የሚሆኑ ውድ ሦስት ነጥቦች ማሳካት ቢችሉም ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ዘላቂ መሆናቸውን ለማረጋገጥ አሁንም ተደጋጋሚ ድሎችን ማስመዝገብ ያስፈልጋቸዋል።

ይህ እንዲሆን ደግሞ በመጨረሻው ጨዋታ የተቀናጀ አደረጃጀት የነበረው እና ስር ነቀል አወንታዊ ለውጥ ያሳየው የኋላ ክፍሉ በጥንካሬው መዝለቅ ይኖርበታል።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ቀዶ ጥገና ያደረገው አብዱላሂ አሊዩ እና የቁርጭምጭሚት ጉዳት የደረሰበት በፍቃዱ አስረሳኸኝ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም። በወልዋሎ በኩል ናትናኤል ዘለቀ፣ ሱልጣን በርሐ እና ዳዊት ገብሩ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም፤ የዮናስ ገረመው መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። እንዲሁም ኤፍሬም ኃይለማርያም በቅጣት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይሳተፍም።

ቡድኖቹ ሁለት ጊዜ (በ2010) ተገናኝተው አንደኛውን ወልዋሎ 3-1 ሲያሸንፍ ሌላኛውን 1-1 ተለያይተዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ መቻል

ከላይ እና ከታች ባለው ፉክክር የሚገኙትን የሊጉ አንጋፋ ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ በሁለቱም  ተጋጣሚዎች ባለው የውጤት አስፈላጊነት ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።

በእስካሁኑ የሊጉ ቆይታቸው ደካማ ጉዞ በማድረግ ላይ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች በአስራ ሁለት ነጥቦች በወራጅ ቀጠናው ላይ ይገኛሉ።

በሊጉ ከወልዋሎ እና አዳማ በመቀጠል በርከት ያሉ ሽንፈቶች በማስተናገድ በሁለተኛ ደረጃነት የተቀመጠው ቡድኑ ድል ካደረገ አስራ አንድ የጨዋታ ሳምንታት አስቆጥሯል። ቡድኑ ከሁለት ሽንፈቶች በኋላ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቶ ከመውጣቱ በተጨማሪ ከአስራ አንድ መርሐግብሮች በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በተከታታይ ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት ችሏል። ቡድኑ ለተከታታይ ሳምንታት ከድል ጋር ቢራራቅም በደረጃ ሰንጠረዡ ባለው መቀራረብ ተከታታይ ድሎች ማስመዝገብ ከቻለ ደረጃውን የማሻሻል ዕድል አለው። ይህ እንዲሆን ግን ከተከታታይ የአቻ  ውጤቶች በኋላ ከመሪነቱ ፉክክር እንዳይርቅ የሚረዳውን ድል ለማግኘት ወደ ሜዳ ከሚገባው መቻል እና ከስጋት ቀጠናው ፈቀቅ ካለው ንግድ ባንክ ጋር ከሚደረጉ ቀሪ ሁለት መርሐግብሮች ነጥቦችን መሰብሰብ ይኖርበታል።

በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ከሊጉ አናት ወደ 3ኛ ደረጃነት የወረደው መቻል 27 ነጥቦች ሰብስቧል።

መቻሎች ተከታታይ ድሎች እያስመዘገቡ በዘለቁበት የዘንድሮው ውድድር በጊዜ ርቀው የመሄድ ምልክት ቢያሳዩም ባልተጠበቁ ጨዋታዎች ነጥቦችን መጣላቸው ተፎካካሪዎቻቸው እንዲጠጓቸው እንዲሁም መሪነታቸው እንዲያስረክቡ አድርጓቸዋል። ጦሩ ከውጤታማው የድሬ ቆይታ በኋላ በአዳማ ከተማ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሦስት አቻ፣ አንድ ሽንፈት እና አንድ ድል ማስመዝገቡን ተከትሎ የእስካሁኑ የአዳማ አፈጻጸሙ ጥሩ ነው ማለት አይቻልም። በውድድር ዓመቱ ሃያ ሦስት ግቦችን ያስቆጠረ ጠንካራ የፊት መስመር ያለው ቡድኑ በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል፤ ከቀደመው ጥንካሬው አንጻር ደከም ብሎ መታየቱም ኮስታራ ተፎካካሪ መሆኑን የሚያሳይ ድል ማስመዝገብም ይኖርበታል።

በሀዋሳ ከተማ በኩል በረከት ሳሙኤል ከቅጣት እስራኤል እሸቱ ደግሞ ከጉዳት ተመልሰዋል። የዮሴፍ ታረቀኝ ጉዳይ አሁንም ባለበት ሲቀጥል ቡድኑ ለነገው ጨዋታ ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነውን ስብስቡን ይዞ ይቀርባል። በመቻል በኩል የመስመር ተከላካዩ ግሩም ሀጎስ በአምስት ቢጫ ካርዶች ምክንያት በቅጣት የነገው ጨዋታ ያልፈዋል።

ሁለቱ ቡድኖች 34 ጊዜ ተገናኝተዋል። ሀዋሳ ከተማ 14 በማሸነፍ ቅድሚያውን ሲይዝ መቻል 10 ጨዋታ አሸንፏል። ቀሪዎቹ 10 ጨዋታዎች አቻ የተለያዩባቸው ግንኙነቶች ናቸው። በጎሎች የታጀበ ታሪክ ያለው ይህ ግንኙነት 80 ጎሎች የተቆጠሩበት ሲሆን ሀዋሳ 43 መቻል በበኩሉ 37 ጎሎችን አስቆጥረዋል።