ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ አቻ ተለያይተዋል

ፍቃዱ ዓለሙ እና ዳዋ ሆቴሳ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ጎላቸውን ባስቆጠሩበት ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ነጥብ ተጋርተዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ16ኛው ሳምንት ሲዳማ ቡናን በማሸነፍ ወደ ድል ሲመለሱ ከተቀሙበት ቋሚ አሰላለፍ አንድ ለውጥ አድርገው ሚኪያስ ካሣሁንን በጌታሁን ባፋ ተክተው ሲገቡ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሀዲያ ሆሳዕናን አሸንፈው የውድድር አመቱን የመጀመሪያ ድል ካሳኩበት ቋሚ ስብስባቸው አንድ ለውጥ አድርገው፤ ናትናኤል ዘለቀን በሚራጅ ሰፋ ተክተው ቀርበዋል።

በወልዋሎች አንፃራዊ ወደፊት የመሄድ የበላይነት በጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያ 10 ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራ ባይደረግም በአንፃራዊነት ቢጫዎቹ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ለመሄድ ሲጥሩ ታይተዋል። ምንም እንኳን በኳስ ንክኪ ብልጫ ቢወሰድባቸውም ለግብ የቀረበ አጋጣሚ በመፍጠር ረገድ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ቀዳሚ ነበሩ ፤ በ12ኛው ደቂቃ ላይ ኢዮብ ገብረማርያም ከመሃል ሜዳ አካባቢ በረጅሙ የጣለውን ኳስ ሽመክት ጉግሳ ደርሶ ሳጥን ውስጥ ብቻውን ለነበረው ሐብታሙ ሸዋለም አሻግሮለት ሐብታሙ ሳይጠቀምበት የቀረው አስቆጪ አጋጣሚ ይታወሳል።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል ምንም የጠራ የግብ ማግባት ሙከራዎች ሳያስመለክት በቀጠለው አጋማሽ ምንም እንኳን በሙከራ መድመቅ ባይችልም በእንቅስቃሴ አኳያ ጨዋታው አሰልቺ የሚባል አልነበረም። ወልዋሎዎች ጨዋታው ገና 20ኛው ላይ ሲደርስ ዮናስ ገረመውን አስወጥተው ሰለሞን ገመቹን ቀይረው ያስገቡበት ክስተት ሲታወስ በአጫጭር ቅብብል ቶሎ ወደ ተጋጣሚ ቡድን ግብ ክልል እየደረሱ በተደጋጋሚ የቆመ ኳስ በብዛት ሲያገኙ የነበሩ ቢሆንም እንደ አጋጣሚዎቹ አጠቃቀማቸው የተዳከመ ነበር።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩላቸው በረጃጅም ኳሶች አለፍ ሲልም በአንድ ለአንድ ቅብብል በማጥቃት ሂደት ወደፊት ረጃጅም ኳሶችን እየጣሉ ሙከራ ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም በአጋማሹ እንደ እቅዳቸው ሳይሆን ቀርቶ በረጅሙ የሚጣሉ ኳሶች ቀጥታ ወደ በረከት አማረ እጅ እየገቡ ሲቸገሩ አስተውለናል። አጋማሹም ግብ ሳያስመለክተን ተገባዷል።

ጨዋታው በሁለተኛ አጋማሽ ሲቀጥል ገና ጨዋታው ከመጀመሩ ቢጫዎቹ ጠንከር ያለ ሙከራ በማድረግ ጀምረዋል ፤ 46ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ርቀት ላይ ሆኖ አክርሮ የመታውን ኳስ ኢድሪሱ አብዱላኢ መልሶባቸዋል። ግለቱን ጨምሮ በተመለሰው በአጋማሹ ሁለቱም ቡድኖች በፈጣን ሽግግር ወደ ሦስተኛው ሜዳ ክፍል ሲደርሱ ያስተዋልን ሲሆን ቢጫዎቹ ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ ሆነዋል ፤ 53ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ለአንድ ቅብብል ኳሷን ዳዋ ሆቴሳ ሳጥን ውስጥ ይዞ ሲገባ ዲንክ ኪያር በሰራው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ዳዋ ሆቴሳ እራሱ መትቶ ወደ ግብነት ቀይሮ መሪ አድርጓቸዋል።

ግብ ካስተናገዱ በኋላ የተነቃቃቱ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ጫን ብለው የአቻነት ግብ ፍለጋ ወደፊት ሲሄዱ የተስተዋሉ ሲሆን አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የፊት መስመራቸውን ለማጠናከር የተጫዋች ቅያሪ አድርገው ኢዮብ ገብረማርያምን በፍቃዱ ዓለሙ ቀይረው ሜዳ እንዳስገቡ በሴከንዶች ልዩነት የአቻነት ግብ መረብ ላይ አክለዋል። 68ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በግራ መስመር በኩል ኳስ እየገፋ ይዞ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ ተቀይሮ ሜዳ የገባው ፍቃዱ ዓለሙ በመጀመሪያ ሁለት ንክኪዎቹ ወደ ግብነት ቀይሮ አቻ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

ከግቦቹ መቆጠር በኋላ ጨዋታው ዘለግ ላለ ደቂቃ ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራዎችን ሳያመለክት ቀጥሎ ወደመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ላይ ሲደርስ ሁለቱም ቡድኖች ጫን ብለው የማሸነፊያ ግብ ለማስቆጠር ሙከራዎች አድርገዋል። 80ኛው ደቂቃ ላይ የቆመ ኳስ ዳዋ ሆቴሳ አሻምቶ ሚራጅ ሰፋ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ ቋሚ ብረት ለትንሽ ርቃ ያለፈበት አጋጣሚ ሲታወስ ምናልባትም ቢጫ ለባሾቹን ከአንድ ነጥብ ወደ ሦስት ነጥብ ከፍ ለማድረግ የቀረበ ሙከራ ነበር። ኢትዮ ኤሌክትሪክም በረጃጅም ኳሶች ወደ  ተጋጣሚያቸው ግብ ክልል ሲደርሱ ብንመለከትም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክት 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።