ሐይቆቹ በዓሊ ሱሌይማን ግሩም የቅጣት ምት ጎል መቻልን 1ለ0 በመርታት ወሳኝ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።
መቻል ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው ከወጡበት ቋሚያቸው ሁለት ለውጦችን በማድረግ ግሩም ሀጎስን በዮሐንስ መንግስቱ እና አብዱ ሙታላቡን በዳዊት ማሞ ተክተው ሲጀምሩ ሀዋሳ ከተማዎች ከቅዱስ ጊዮርጊስ 1-1 ካጠናቀቁበት አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ቀርበዋል።
ሐይል በተቀላቀለ እንቅስቃሴ ጅማሮውን ባደረገው የምሽቱ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ኳሶችን ወደፊት በመጣል 3ኛ ደቂቃ ላይ በቆመ ኳስ ከግብ አግዳሚ ለትንሽ ከፍ ባለ የአቤኔዘር ዮሐንስ ሙከራ በኋላ በጥንቃቄ ቀጥሎ 8ኛው ደቂቃ ላይ መቻሎች በአቤል ነጋሽ አማካኝነት ዒላማውን ያልጠበቀ የግንባር ሙከራ ተደምሮበት እንቅሰቃሴያቸው ሁሉ ወደፊት ያደረጉበትን የመጀመሪያ 10 ደቂቃዎች አስመልክቶናል። መቻሎች ወደ ተጋጣሚ ቡድን በሚያደርጉት ፈጣን ሽግግር የቀጠለው ጨዋታ ደቂቃው 18ኛው ላይ ሲደርስ አብዱልከሪም ወርቁ እና አማኑኤል ዮሐንስ በጥሩ መግባባት ባደረጉት እርስ በርስ ቅብብል አማኑኤል ዮሐንስ ሳጥን ውስጥ በቀኝ መስመር ላይ ሆኖ ብቻውን ሳጥን ውስጥ ለነበረው አቤል ነጋሽ አሻግሮለት ሸርተት ብሎ ኳሷን ሳያገኝ የቀረው አስቆጪው አጋጣሚ ይጠቀሳል።
የመቻሎች የወደፊት የመሄድ እንቅስቃሴዎች በተበራከቱበት በአጋማሹ በአጫጭር የኳስ ቅብብል ብልጫ ወስደው ወደ ሦስተኛው ሜዳ ክፍል ሲደርሱ ቢስተዋሉም ጠንከር ያለ ሙከራ ለማድረግ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ጠንካራ ሆኖ ያመሸው የሀዋሳ ከተማዎች የኋላ ደጀን ኳሶቹን ሲያቋርጥባቸው ያስተዋልን ሲሆን 36ኛው ደቂቃ ላይ በቆመ ኳስ በፍሪምፖንግ ሜንሱ አማካኝነት አደገኛ ሙከራ አድርገው ሰዒድ ሀብታሙ እንዴትም ብሎ አድኖባቸዋል።
ዓሊ ሱሌይማንን ትኩረት ባደረጉ ረጃጅም ኳሶች እና በአማዛኙ ወደ አንደኛው ሜዳ ክፍል በማድላት መከላከሉ ላይ ትኩረት ያደረገው የሀዋሳ ከተማዎች አጨዋወት በመልሶ ማጥቃት ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ ያስተዋልን ሲሆን 40ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ ዓሊ ሱሌይማን ጨርፎ ወደ ግብ አሻግሮ አልዌንዚ ናፊያን እንዴትም ተንጠራርቶ የማዕዘን ምት ካደረገው ሙከራ ውጪ ሌላ የጠራ ሙከራ ሳያደርጉ አጋማሹ ተገባዷል።
ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ በቀጠለው በአጋማሹ ሁለቱም ቡድኖች አጨዋወታቸውን ሳይቀይሩ ገብተው ሐይቆቹ ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አክለዋል። 55ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ ብሩክ ኤልያስ ይዞ በሚገባበት ወቅት የመቻል ተከላካዮች በፈፀሙት ንክኪ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ቅጣት ምት ተሰጥቷቸው ዓሊ ሱሌይማን ቀጥታ ወደ ግብ በመምታት በግሩም ሁኔታ መረብ ላይ አሳርፎ መሪ አድርጓቸዋል።
ግቡ የረበሻቸው መቻሎች ለማጥቃት የተሻለ ፍላጎት ያሳዩ ሲሆን ጠንካራ ጥቃት እየሰነዘሩ ቢቀጥሉም ደቂቃዎች እየገፋ በመጡ ቁጥር ወደ ራሳቸው ግብ ክልል ወረድ ብለው መጫወት የመረጡትን የሐይቆቹን የተከላካይ ክፍል ሰብረው ገብተው ጠንከር ያለ ሙከራ ማድረግ ተስኗቸዋል። ሐይቆቹ በበኩላቸው የናፈቃቸውን ድል ለመጎናፀፍ ወደ ኋላ አፈግፍገው በቀሪ ደቂቃዎች ውጤቱን ማስጠበቅ ላይ ትኩረት አድርገው በመጫወት አልፈው አልፈው በመልሶ ማጥቃት ጥቃት ለመሰንዘር ያስቡ እንጂ ሀሳብ ብቻ ሆኖ ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች አቅንቷል።
ጫናዎችን አጠናክረው ቀጥለው የሀዋሳ ከተማዎችን ተከላካዮች መፈተን የቀጠሉት መቻሎች 84ኛው ደቂቃ ላይ አደገኛ ሙከራ አድርገዋል፤ አስቻለው ታመነ ከመሃል ሜዳ ኳስ እየገፋ ይዞ ሄዶ ተቀይሮ ለገባው ጳውሎስ መርጊያ አቃብሎት በግራ መስመር ከሳጥኑ ቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ የመታውን ኳስ ሰይድ ሀብታሙ እንዴትም አምክኖባቸዋል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ጭማሪ ደቂቃዎች ላይ መቻሎች ቢያንስ አንድ ነጥብ ለማግኘት ሙሉ ኃይላቸውን ተጠቅመው ለማጥቃት ቢሞክሩም እጃቸው የገባውን 3 ነጥብ ይዞ ለመውጣት ሲታገሉ የነበሩትን የሐይቆቹን ተጫዋቾች አልፈው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል። ጨዋታውም በዓሊ ሱሌይማን ግሩም ቅጣት ምት ብቸኛ ግብ ሐይቆቹን ከ12 ጨዋታ ሳምንታት ጥበቃ በኋላ ወደ ድል በመመለስ ተቋጭቷል።