መረጃዎች | 70ኛ የጨዋታ ቀን

በታላቁ የሸገር ደርቢ የሚከፈተው የ18ኛው ሳምንት ነገ ይጀምራል፤ በዕለቱ የሚከናወኑ ጨዋታዎችን አስመልክተን ያዘጋጀናቸውን መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ፈረሰኞቹ እና ቡናማዎቹን የሚያገናኘው ተጠባቂው የሸገር ደርቢ የጨዋታ ሳምንቱ ቀዳሚ መርሐግብር ነው።

በሃያ ስምንት ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፈው ሳምንት ከተጎናጸፈው ድል በኋላ ለዚህ ጨዋታ ደርሷል።

ሃያ ስምንት ነጥቦችን የሰበሰቡት እና ከመሪው በሁለት ነጥቦች ርቀት ላይ የሚገኙት ፈረሰኞቹ ከተከታታይ አራት ድሎች በኋላ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ  ቢጋሩም በመጨረሻው መርሐግብር ወላይታ ድቻን አሸንፈው ለወሳኙ ጨዋታ ይቀርባሉ።

ከመቻል እና ፋሲል ከነማ በጣምራ ጥቂት ሽንፈቶች በማስተናገድ በሁለተኛ ደረጃነት የተቀመጡት ጊዮርጊሶች በቅርብ ሳምንታት እጅግ የተሻሻለ እና ውጤታማ የፊት መስመር ገንብተዋል። በሊጉ ከመቻል ቀጥሎ በርከት ያሉ ግቦች ያስቆጠረው ቡድኑ ከድሬዳዋ የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ ኳስና መረብ ሳያገናኝ ቢወጣም በአዳማ ቆይታው በስድስት ጨዋታዎች አስር ግቦችን በማስቆጠር በጥሩ የአፈፃፀም ብቃት ላይ ይገኛል።

ከብዙዎች ግምት ውጭ በሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል የሚፎካከር ጠንካራ ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ዘለግ ላሉ ሳምንታት እንቅስቃሴ ከውጤት ጋር ለማጣጣም ቢቸገሩም አሁን ግን ቡድናቸው ሁለንተናዊ ለውጥ አምጥቶ
በሚፈለገው የውህደት ደረጃ ላይ መድረስ ችሏል።

በሃያ ሁለት ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጨረሻው ሳምንት ከተጎናፀፉት ጣፋጭ ድል መልስ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፈው ደረጃቸውን ለማሻሻል እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

አስራ አንድ ጨዋታዎችን ባከናወኑበት የድሬዳዋ ከተማ ቆይታቸው አራት ድል፣ አራት ሽንፈት እና ሦስት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡት ቡናማዎች በውጤት ረገድ ወጣ ገባ ከነበረው የድሬ ቆይታቸው በብዙ ረገድ ተሻሽለዋል። ጠንካራ ቡድኖችን በገጠሙባቸው ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ያስመዘገቧቸው ሁለት ድሎች እና ያሳዩት እንቅስቃሴም የዚህ ማሳያ ነው። ቡናማዎቹ ከኳስ ውጭ ያለው የቡድናቸው እንቅስቃሴ ዋነኛ የጥንካርያቸው መገለጫ ነው፤ በማያቋርጥ እንቅስቃሴ ጫና ፈጥሮ የመጫወት ጥረት የሚያደርገው ቡድኑ የተጠቀሰው አወንታዊ ጎኑ  በሊጉ ጥቂት ግቦች ካስተናገዱ ተርታ እንዲመደብ አስችሎታል። ከላይ እንደገለፅነው የቡና ዋነኛ ጠንካራ ጎን ከኳስ ውጭ ያለው ታታሪነት እና ጫና ፈጥሮ የመጫወት ክህሎት ሲሆን የተሻለ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የሚያስችል ተከታታይ ጫናን መፍጠር የነገ የቤት ሥራው ይመስላል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ባለፈው ጨዋታ ሳይታሰብ በጉዳት ከስብስቡ ውጭ የነበሩት ሻይዱ ሙስጠፋ እና ፍሪምፖንግ ክዋሜ ለነገው ጨዋታ ሲደርሱ ያለፉትን ጨዋታዎች ቡድኑን ያላገለገለው አማኑኤል ተርፉ ወደ ልምምድ ሲመለስ የመጫወቱ ነገር ነገ የሚወሰን ይሆናል። ከዚህ ውጭ የአጥቂው ዳግማዊ አርዓያ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ሲሆን የተቀሩት የቡድኑ አባላት ለነገው የደርቢ ጨዋታ በተሟላ ሁኔታ ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ከመላኩ አየለ ውጪ ሁሉም የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ 48 ጊዜ ተገናኝተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶች ፈረሰኞቹ 21 ጊዜ ድል ሲቀናቸው ቡናማዎቹ 8 ጊዜ አሸንፈዋል፤ 19 ጊዜያት ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በ48ቱ የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት በድምሩ 95 ጎሎች መረብ ላይ አርፈዋል። 63 ግቦች በማስቆጠር ፈረሰኞቹ ቀዳሚ ሲሆኑ ቡናማዎቹ ደግሞ 32 ኳሶችን ከመረብ አዋህደዋል።

ሲዳማ ቡና ከ ስሑል ሽረ

በአደጋው ቀጠና የሚገኘው ሲዳማ እና በወራጅ ቀጠናው የሚገኘው ስሑል ሽረን የሚያገናኘው
የነገው ጨዋታ ለሲዳማዎች ከወራጅ ቀጠናው በአንፃራዊነት በጥሩ ሁኔታ ለመሸሽ ለስሑል ሽረ ደግሞ ከተከታታይ ድል አልባ ጨዋታ መጠነኛ እፎይታ ለማግኘት ስለሚረዳ ቡድኖቹ ከፍተኛ ትግል ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ሲዳማ ቡና በደረጃ ሰንጠረዡ የወራጅ ቀጠና ባይገኝም ከስጋት ግን ብዙም አልራቀም። ቡድኑ ከወራጅ ቀጠናው በአራት ነጥብ እና በአንድ ደረጃ ፈቀቅ ብሎ በ13ኛ ደረጃ ላይ እንደመገኘቱም በነገው ዕለት ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል መመለስ ግድ ይለዋል። ኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮጵያ መድን ላይ ካስመዘገቧቸው ተከታታይ ድሎች በኋላ ባልተጠበቀ መልኩ በጥቅሉ ደካማ ጊዜያትን ያሳለፉት ሲዳማዎች በሁሉም ረገድ የነበራቸው አፈፃፀም ቡድኑ ላለው የስብስብ እና የጥልቀት ጥራት የሚመጥን አይደለም። ከተጠቀሱት ተከታታይ ድሎች በኋላ በተከናወኑ አስር ጨዋታዎች አምስት ሽንፈት፣ አራት አቻ እና አንድ ድል ብቻ ያስመዘገበው ቡድኑ ምንም እንኳን በአዳማ ቆይታው ከተከታታይ ሽንፈቶች ቢርቅም ከአደጋው ቀጠና ለመሸሽ ወደ ድል የመመለስ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል።

ሲዳማ ቡናዎች በድሬ የመጨረሻ ጨዋታዎች
እጅግ አሳሳቢ የነበረው የመከላከል ድክመታቸው ማረማቸው በጥሩነት የሚነሳላቸው ነጥብ መሆኑ ባይካድም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ኳስ እና መረብ ማገናኘት የተሳነው የፊት መስመራቸው ግን ስር ነቀል ለውጥ የሚፈልግ ደካማው ጎናቸው ነው።

በአስራ ሁለት ነጥቦች 17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት
ስሑል ሽረዎች የአዳማ ከተማ መጥፎ አጀማመራቸውን የሚቀለብስ ወሳኝ ድል ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

በውጤት ረገድ በአዳማ ከተማ ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ያልቻሉት ስሑል ሽረዎች ከባለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሳካት የቻሉት አንድ ነጥብ ብቻ ነው። ከነጥቡ ባለፈ በአምስቱ ጨዋታዎች ቡድኑ ስምንት ግቦችን ያስተናገደ ሲሆን በተቃራኒው ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠረው ጎል ሦስት ብቻ ነው።ይህ ቁጥር ቡድኑ ምን ያህል በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ እየተቸገረ እንደሆነም ይጠቁማል። ቡድኑ ካለበት ወራጅ ቀጠና ዕድገት ለማምጣት የነገው ጨዋታ ወሳኝ ስለሆነም በብዙ ረገድ ተሻሽሎ መቅረብ ይኖርበታል። ቡድኑ በመጨረሻው ጨዋታ ከተከታታይ አራት ሽንፈቶች መልስ አንድ ነጥብ ማስመዝገብ ቢችልም በነገው ዕለት ከሲዳማ ቡና ጋር ያለበት ጨዋታ ጨምሮ ከወልዋሎ ጋር የሚያደርገው የመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ አወንታዊ ነጥብ ይዞ ለመውጣት በመከላከሉ እና በማጥቃት ረገድ ያሉበትን ክፍተቶች በቶሎ መድፈን ይጠበቅበታል።

በሲዳማ ቡና በኩል ጉዳት ላይ የነበሩት መስፍን ታፈሰ እና ሀብታሙ ታደሰ ሲመለሱ ፍራኦል መንግሥቱ እና አበባየሁ ሀጂሶ መጠነኛ ጉዳት አስተናግደው ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆናቸውን አረጋግጠናል። በስሑል ሽረ በኩል ብርሃኑ አዳሙ፣ ዋልታ ዓንደይ እና ሄኖክ ተወልደ በቅጣት ኬቨን አርጉዲ ደግሞ በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይሰለፉም።ቡድኖቹ በሊጉ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ አንዱን ሲያሸንፍ በአንዱ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ሲዳማ አራት ሲያስቆጥር ሽረ ደግሞ ሦስት ማስቆጠር ችሏል (የተሰረዙትን የ2012 ሁለት ጨዋታዎች አያካትትም)።