ሪፖርት | ተጠባቂው የደርቢ ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል

በደማቅ የደጋፊዎች ድባብ ታጅቦ የተደረገው እጅግ ተጠባቂው የደርቢ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጨረሻ የሊጉ መርሃግብራቸው ወላይታ ድቻን ሲረቱ ከተጠቀሙት የመጀመሪያ 11 ስብስብ ባደረጓቸው ሦስት ለውጦች ቶሎሳ ንጉሴ ፣ አሸናፊ ጌታቸው እና ቢኒያም ፍቅሬን አስወጥተው በምትካቸው ሻሂዱ ሙስጠፋ ፣ ፍሪምፖንግ ክዋሜ እና ተገኑ ተሾመን በመጀመሪያ ተሰላፊነት ሲያስጀምሩ በአንፃሩ በመጨረሻ የሊግ ጨዋታቸው ባህር ዳር ከተማን ረተው የመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ አማኑኤል አድማሱን በአንተነህ ተፈራ ብቻ ተክተው ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።

ከጨዋታው ጅማሮ አስቀድሞ ኢትዮጵያ ቡናዎች በቅርቡ ህይወቱ ላለፈው የክለቡ የልብ ደጋፊ ለነበረው ካሊድ አህመድ መታሰቢያ በማድረግ በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ፍፁም ደካማ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን የተመለከትንበት ነበር።

የሚቆራረጡ የኳስ ሂደቶች በርክተው በተስተዋሉበት አጋማሹ ከተደጋጋሚ ጥፋቶች በዘለለ በጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በኩል በቂ ነገር መመልከት የቻልንበት አልነበረም ፤ ምናልባት በአጋማሹ የተሻለ የሚባለው ሙከራ በ15ኛ ደቂቃ ፍፁም ጥላሁን በግራ መስመር በኩል ረጀም ሚፍታህን አልፎ ወደ ውስጥ ያሻገራት ኳስ በድንገት ሳትጠበቅ አቅጣጫዋን ቀይራ ዳንላድ ኢብራሂም ያዳናት ኳስ ተጠቃሽ ነበረች።

እጅግ ደካማ በነበረው አጋማሽ በኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል በ41ኛው ደቂቃ በፍቃዱ ዓለማየሁ በሜዳው የላይኛው ክፍል ላይ ከነጠቀው ኳስ በተነሳ የማጥቃት ሂደት ዲቫይን ዋቹኩዋ ከግራ ወደ ውስጥ ያሳለፈለትን ኳስ ኮንኮኒ ሃፍዝ ወደ ግብ ያደረጋት ሙከራ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ርብርብ ስትመለስ በፍቃዱ ዳግም ሞክሮ ባህሩ ነጋሽ ያዳነበት ሙከራ ተጠቃሽ አጋጣሚ ነበረች።

በአጋማሹ መገባደጃ በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል   በአስገዳጅ ሁኔታ የትከሻ ጉዳት ያስተናገደው በረከት ወልዴን በአፍወርቅ ኋይሉ ለመተካት ተገደዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ሚኪያስ ፀጋዬ እና ኪሩቤል ደሳለኝን በመቀየር የጀመሩት ቡናማዎለ በሰከንዶች ልዮነት ተቀይሮ የገባው ኪሩቤል ደሳለኝ ባስጀመረው የማጥቃቅ ሂደት በዲቫይን ዋቹኩዋ አማካኝነት ከሳጥን ጠርዝ ሞክረው ባህሩ ነጋሽ አድኖባቸዋል።

ይበልጥ ተነቃቆት በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በ48ኛው ደቂቃ ይታገሱ ታሪኩ ከሳጥን ውጭ ያደረጋት እና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችብ እንዲሁም በ53ኛው ደቂቃ ኪሩቤል ደሳለኝ ከሳጥን ውስጥ ሆኖ የሞከራት እና ባህሩ ነጋሽ የያዘበት ሙከራ ሲታወሱ በጊዮርጊሶች በኩል በ51ኛው ደቂቃ ፍፁም ጥላሁን ከቆመ ኳስ ያደረገውን ሙከራ ዳንላድ ኢብራሂም አድኖበታል።

በሁለተኛው አጋማሽ በአውንታዊነት የተሻሉ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በ61ኛው ደቂቃ ዲቫይን ዋቹኩዋ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ከቀኝ መስመር ያሻገራትን ኳስ አንተነህ ተፈራ ገጭቶ አስቆራት ተብሎ ሲጠበቅ ያመከናት ኳስ ከሙከራዎች ሁሉ የላቀችው ነበረች።

ከዕረፍት መልስ በተደረጉት ለውጦች ታግዘው ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ቡናማዎቹ በ68ኛው ደቂቃ ላይ ኪሩቤል ደሳለኝ ያቀበለውን ኳስ ከሳጥን ውጭ ነፃ ሆኖ ያገኘው ሚኪያስ ፀጋዬ በግራ እግሩ በግሩም ሁኔታ ያደረጋት ሙከራ የግቡን ቋሚ ለትማ ተመልሳበታለች።

በሂደት እየተቀዛቀዘ በመጣው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጨረሻዎች ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጨዋታውን አሸንፈው ሊወጡባቸው የሚችሉባቸውን ሙከራዎችን በአማኑኤል ኤርቦ ፣ አብዲ ሳሚዮ እና መሀመድ ኮኔ ቢያደርጉም የኢትዮጵያ ቡናው የግብ ዘብ ዳንላድ ኢብራሂም በአስደናቂ ብቃት ሙከራዎችን ማምከኑን ተከትሎ ጨዋታው ያለ ግብ ሊጠናቀቅ ችሏል።