ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ከአራት ጨዋታዎች በኋላ አሸንፏል

33 ደቂቃዎችን ብቻ ሜዳ ላይ የቆየው መስፍን ታፈሰ ባስቆጠራት ጎል ሲዳማዎች ስሑል ሽረን 1ለ0 አሸንፈዋል።

በ17ኛው ሳምንት በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2ለ0 የተሸነፉት ሲዳማዎች መስፍን ሙዜ ፣ ደግፌ ዓለሙ ፣ ብርሃኑ ቦጋለ እና አበባየሁ ሀጂሶን አሳርፈው ቶማስ ኢካራ ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ ፣ በዛብህ መለዮ እና ሐብታሙ ታደሰን ሲያስገቡ በ17ኛው ሳምንት አራፊ የነበሩት ስሑል ሽረዎች በአንጻሩ በ16ኛ ሳምንት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር 1ለ1 ከተለያዩበት አሰላለፍ ሞይስ ፖየቲ ፣ ክፍሎም ገብረሕይወት እና ብርሃኑ አዳሙን አስወጥተው ፋሲል ገብረሚካኤል ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ፋሲል አስማማውን አስገብተዋል።

ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ የመሩት ጨዋታ አጀማመሩ ቀዝቀዝ ያለ ነበር። በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ውስጥም 12ኛ እና 14ኛ ደቂቃ ላይ የሽረው ግብ ጠባቂ ፋሲል ገብረሚካኤል በሠራቸው ስህተቶች ሲዳማዎች ሁለት የግብ ዕድሎችን አግኝተው ነበር። የመጀመሪያውን ሳሙኤል ሳሊሶ ሲመታው ያገኘው ይገዙ ቦጋለ ያስቆጠረውን ጎል አንደኛ ረዳት ዳኛው ወጋየሁ አየለ በአወዛጋቢ ሁኔታ ከጨዋታ ውጪ ብለው ሲሽሩት በሁለተኛው አጋጣሚም ይገዙ ቦጋለ ያደረገውን ሙከራም በቅርብ ርቀት ላይ የነበረው ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል አግዶበታል።

ሲዳማዎች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መድረስ ቢችሉም 31ኛው ደቂቃ ላይ ሬድዋን ናስር በድንቅ ሁኔታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ሀብታሙ ታደሰ ከሳጥን አጠገብ አክርሮ መትቶት በግቡ የቀኝ ቋሚ ከወጣበት ኳስ ውጪ የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ተደራጅቶ ለመግባት የከበዳቸው ስሑል ሽረዎች በአንጻሩ 42ኛ ደቂቃ ላይ በአጋማሹ ባደረጉት የመጀመሪያ ሙከራ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው መሐመድ ሱሌይማን በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ኃይል የለሽ ሙከራ ግብ ጠባቂው ቶማስ ኢካራ በቀላሉ ይዞበታል።

ከዕረፍት መልስ ሳሙኤል ሳሊሶን አስወጥተው መስፍን ታፈሰን ያስገቡት አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ለውጣቸው ፍሬ ያፈራው 50ኛ ደቂቃ ላይ ነበር። ስሑል ሽረዎች ከራሳቸው የግብ ክልል ኳስ ለመመስረት ሲሞክሩ ይገዙ ቦጋለ ከመሐመድ ሱሌይማን ላይ ጥፋት በመሥራት ጭምር የነጠቀውን ኳስ ሐብታሙ ታደሰ ወደ ውስጥ ሲያመቻቸው ተቀይሮ የገባው መስፍን ታፈሰ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ጥረት ያደረጉት ሽረዎች በጨዋታው የተሻለውን ሙከራቸውን 52ኛ ደቂቃ ላይ አድርገው ሀብታሙ ገዛኸኝ ከርቀት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቶማስ ኢካራ መልሶበታል።

በተጋጣሚ የመከላከል አደረጃጀት ክፍተት ተጠቅመው በተደጋጋሚ ሳጥን ውስጥ ኳስ ማግኘት የቻሉት ሲዳማዎች 60ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን ከይገዙ ቦጋለ በተቀበለው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል ሲያግድበት በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ በዛብህ መለዮ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ከፍ ብሎ ወጥቶበታል።

የጋለ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ ሲዳማዎች 72ኛ ደቂቃ ላይም እጅግ ያለቀለት የግብ ዕድል አግኝተው ሬድዋን ናስር ያሻገረው ኳስ የደረሰው መስፍን ታፈሰ እጅግ ደካማ በሆነ አጨራረስ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ሲያባክነው አጥቂው ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በጉዳት ምክንያት ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል። ስሑል ሽረዎች በአንጻሩ 78ኛ ደቂቃ ላይ በጃዕፈር ሙደሲር አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ጠንካራ ሙከራ አድርገው በግብ ጠባቂው ቶማስ ኢካራ ተመልሶባቸዋል።


ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የስሑል ሽረው አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት በሰጡት አስተያየት በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም በተከላካይ እና ግብ ጠባቂ በተሠሩ ተደጋጋሚ ስህተቶች ዋጋ መክፈላቸውን ተናግረው ስህተቶቻቸውን አርመው ከወራጅ ቀጠናው የመውጣት አቅም እንዳላቸው ሲጠቁሙ የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ቢጫወቱም በሁለተኛው አጋማሽ ግን ጎሉን ካስቆጠሩ በኋላ በተጋጣሚ ቡድን ጫና እንደተፈጠረባቸው ተናግረው በዛሬው ጨዋታ ጎል ማስቆጠራቸው ለቀጣይ ጨዋታዎች መነሳሻ እንደሚሆናቸው ሀሳብ ሰጥተዋል።