መረጃዎች | 71ኛ የጨዋታ ቀን

መረጃዎች | 71ኛ የጨዋታ ቀን

18ኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት የሚከናወኑ መርሀ-ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

አዳማ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ከተከታታይ ሽንፈት ለማገገም ወደ ሜዳ የሚገባው አዳማ ከተማ እና ደረጃው ለማሻሻል የሚያልመው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሀ-ግብር ነው።

በአስራ አምስት ነጥቦች በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው እና በከተማው ውጤታማ ጊዜ ማሳለፍ የተሳነው አዳማ ከተማ ከአደጋው ቀጠና ፈቀቅ ለማለት በነገው ጨዋታ ሙሉ ውጤት ያስፈልገዋል።

በአሠልጣኝ ዓብዲ ቡሊ የሚመራው አዳማ ከተማ
ሽንፈት በገጠሙበት ተከታታይ አራት መርሀ ግብሮች ያሳየው እንቅስቃሴዎች በውድድር ዓመቱ በደካማነት ከሚያዙት ድል አልባ ጉዞዎች መካከል አንዱ እንደሚሆን ብዙዎች ይስማማሉ። በተለይም በአራት ተከታታይ መርሀ-ግብሮች ስምንት ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀታቸው የቡድኑ ዋነኛ ድክመት ነው። በሊጉ በጨዋታ በአማካይ 1.4 ግቦች ያስተናገደው ቡድኑ በውድድር ዓመቱ ከፍተኛ የግብ መጠን በማስተናገድም ቀዳሚ ሆኗል።

ምንም እንኳን እንደ ቡድኑ ውጤት ወጥነት ባይኖረውም ከበታቹ ካሉት ቡድኖች በተሻለ አስራ አምስት ግቦች ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወታቸውም ከዚ ቀደም በነበረው የፈጠራ እና የግብ ማስቆጠር ብቃት ላይ አይገኝም። አሰልጣኝ አብዲ ቡሊ በነገው ዕለት ከወትሮው በተለየ ሁኔታ አፍሳሽ የሆነው የኋላ ክፍላቸው በተጨማሪ ኳስና መረብ ካገናኘ 270′ ደቁቃዎችን ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወታቸው ማስተካከል ይኖርባቸዋል።

ደረጃው እንዲያሽቆለቁል ምክንያት ከሆኑ
ተከታታይ ሦስት ሽንፈቶች አገግሞ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች መሰብሰብ የቻለው ኤሌክትሪክ ከወራጅ ቀጠናው ይበልጥ ለመራቅ እና
ቀጣዩን ዙር በምቾት ለመጀመር ማሸነፍ ያስፈልገዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በውጤት ረገድ ካሳየው መጠነኛ መሻሻል በተጨማሪ በቅርብ ሳምንታት በግብ ማስቆጠሩ ረገድ የነበረው ድክመት አሻሽሏል። ቡድኑ በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ካስቆጠረባቸው መርሀ-ግብሮች በኋላ በተከናወኑ ሁለት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ማስቆጠሩም የመሻሻሉ አንድ ማሳያ ነው። ሆኖም ተስፋ ያለው እንቅስቃሴ ቀጣይነት እንዲኖረው በጨዋታዎች የሚፈጥሯቸው የግብ ዕድሎች በቁጥርም ይሁን በጥራት ከዚህም በላይ ከፍ የማድረግ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል። ቡድኑ በነገው ዕለት በሊጉ ከፍተኛ የግብ መጠን ያስተናገደው ( 22 ) አዳማ እንደመግጠሙ ፈታኝ ፍልምያ ይጠብቀዋል ተብሎ ባይገመትም በቀጣይ ግን አስተማማኝ የሆና የግብ ምንጭ ማበጀት የሚያሳስበው ጉዳይ ነው።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ጉዳት ላይ ከሚገኙት ከአብዱላሂ አላዮ እና በፍቃዱ አስረሳህኝ ውጭ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው፤ በአዳማ ከተማ በኩል የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ነገ ለ38 ጊዜ ይገናኛሉ። እስካሁን 52 ግቦች ያስቆጠረው አዳማ ከተማ 20 ድሎችን ሲያሳካ አስር ጊዜ መርታት የቻለው ኤሌክትሪክ ደግሞ 44 ጎሎች አሉት።

ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ ድሬዳዋ ከተማ

በጥሩ መነቃቃት የሚገኙት ቢጫዎቹ እና በተከታታይ ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻሉት ብርቱካናማዎቹ የሚያደርጉት ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች ባለው የድል ረሀብ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኘው ወልዋሎ ከእጅግ መጥፎው ጊዜ ተላቆ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ነጥብ በማስመዝገብ መጠነኛ እፎይታ አግኝቷል።

አንድ ነጥብ ብቻ በማስመዝገብ ድሬን የተሰናበተው ወልዋሎ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥብ አምስቱን በማሳካት ቀና ብሏል፤  ከነጥቡም ባሻገር በእንቅስቃሴ ረገድ  ያሳየው መሻሻል እንዲሁም የቡድኑ መንፈስ መነቃቃት ማሳየቱም ቀላል ግምት እንዳይሰጠው ያደርጋል። በ17ኛ ደረጃ ካለው ስሑል ሽረ በስድስት ነጥቦች ርቀት ላይ የሚገኘው ቡድኑ ከነበረበት አዘቅት በብዙ ረገድ መሻሻል ማሳየቱ አይካድም፤ ለዚህ ደግሞ ቡድኑ እንዲነቃቃና ነጥብ ማስመዝገብ እንዲጀምር የረዱት ዋና አሰልጣኙ ፀጋዬ ኪዳነማርያም እና ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ቡድኑን የመራው ወጣቱ  ምክትል አሰልጣኙ አታኽልቲ በርሐ የበኩላቸው ድርሻ ተወጥተዋል። ሆኖም በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ኳስና መረብ ያገናኘው የማጥቃት አጨዋወት የጥራት ደረጃው ከፍ ማድረግ እንዲሁም በውድድር ዓመቱ ሀያ አንድ ግቦች ያስተናገደው እና ባለፉት ሳምንታት በመጠኑ ጥሩ እድገት ካሳየ በኋላ  በኢትዮ ኤሌክትሪክ የተፈተነው የኋላ ክፍል የማስተካከል የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።

በጥቅሉ ሲታይ ግን ቡድኑ ከነበረበት የከፋ ውጤት ማጣት ተላቆ ነጥብ መሰብሰብ መጀመሩ ለከርሞ በተሻለ ተነሳሽነት እንዲጫወት እንደሚያደርገው ይታመናል።

በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ከገጠማቸው ሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርቡት ድሬዳዋ ከተማዎች ከነበራቸው መልካም አጀማመር ተንሸራተው ቀስ በቀስ ከሊጉ መሪዎች እየራቁ በመምጣት ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች ድል ማድረግ አልቻሉም። ከሳምንታት በፊት በሊጉ በርከት ያሉ ግቦች ካስቆጠሩ ክለቦች ተርታ የነበሩት ብርቱካናማዎቹ ከወሳኙ አጥቂ መሐመድኑር ናስር ጉዳት በኋላ የፊት መስመራቸው ብቃት በጥሩ ሁኔታ እየሄደላቸው አይደለም። በመጀመርያዎቹ አምስት ጨዋታዎች አስር ግቦች በማስቆጠር በአስደናዊ ብቃት ዓመቱን የጀመረው ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ግን በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ በማስቆጠር ጉልህ የጎል ማስቆጠር ችግር ውስጥ ገብቷል።

በመቀመጫ ከተማቸው ከተሰናበቱ ወዲህ ከድል ጋር የተራራቁት ድሬዎች ከድል አልባው የሳምንታት ጉዞ ለማገገም በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ያለባቸው ክፍተት መድፈን ቀዳሚ ስራቸው መሆን ይገባዋል።ከመጨረሻው ጨዋታ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው የድህረ ጨዋታ ቆይታ የሜዳው ምቹ አለመሆን በአጨዋወታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ የገለፁት አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በተለመደው አቀራረባቸው ይቀጥላሉ ወይስ የሜዳውን ጥራት ከግምት ያስገባ ሌላ አጨዋወት ያበጃሉ የሚለው ጉዳይም ተጠባቂ ነው።

በወልዋሎ በኩል ዳዋ ሆቴሳ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ዳዊት ገብሩ በጉዳት ኤፍሬም ኃይለማርያም ደግሞ በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው፤ ዋና አሰልጣኙ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ግን ከቅጣት መልስ ቡድናቸውን እየመሩ ወደ ሜዳ ይገባሉ።  በድሬዳዋ ከተማ በኩል መሐመድኑር ናስር በጉዳት አላዛር መርኔ ደግሞ በቅጣት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይሰለፉም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ ሦስቱን በማሸነፍ የበላይ ሲሆን አንዱን አቻ ተለያይተው ወልዋሎ እስካሁን ድል ማሳካት አልቻለም። በአራቱ ግንኙነቶች ድሬዳዋ 6፣ ወልዋሎ 1 ጎል አስቆጥረዋል።