በትናንትናው ዕለት በሸገር ደርቢ ጨዋታ ከቡናማዎቹ ጋር ያለ ጎል የተለያዩት ፈረሰኞቹ በዳኝነት ላይ ያላቸውን ቅሬታ ለፌዴሬሽኑ በደብዳቤ አቅርበዋል።
በ18ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታ በትናንትናው ዕለት 9 ሰዓት ላይ በአሳቴዩ ስታዲየም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ተጫውተው 0ለ0 የተለያዩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጨዋታው ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ አመራር ላይ የነበራቸውን ቅሬታ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አመልክተዋል።
“በየዘመኑ ተደጋጋሚ የሆኑ የዳኝነት በደሎች ቢፈፀሙብንም በሂደት ይስተካከላሉ በሚል እምነት በትዕግስት አሳልፈናል፡፡” ያሉት ጊዮርጊሶች “አሁን አሁን በስታዲየም የሚፈፀሙ ግልጽና አድሏዊ የሆኑ የዳኝነት በደሎች ተጫዋቾች እና የቡድን አባላት እንዲሁም ተመልካቹ ህዝብ የሥነ ምግባር ጥሰት ውስጥ እንዲገባ የሚገፋፉ ሆነው ታይተዋል፡፡” በማለት ጠቁመው “ትናንት በሸገር ደርቢ ጨዋታ በመሐል ዳኝነት የመሩት ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ሦስት የፍፁም ቅጣት ምቶችን የከለከሉበት ሁኔታ አግራሞት የፈጠረ ቢሆንም ጉዳዩ መመርመር የሚያስፈልገው እና የማያዳግም እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ፣ ለእግር ኳሱ እድገት ፀር የሆነ አካሄድ ነው፡፡ ሦስቱንም የቪዲዮ ምስሎች በአጽንዖት እንድትመለከቱት አያይዘን አቅርበናል፡፡” በማለት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እርምጃ እንዲወሰድ የሚያሳስብ ደብዳቤ ማስገባታቸው ታውቋል።