ኢትዮ ኤሌክትሪኮች አዳማ ከተማን 3-0 በሆነ ሰፊ ግብ ልዩነት በማሸነፍ ደረጃቸውን ያሻሻሉበትን ድል አስመዝግበዋል።
አዳማ ከተማዎች ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽንፈት ሲያስተናግዱ ይዘው ከገቡት ቋሚ ስብስባቸው ሁለት ለውጦችን አድርገው ፍቅሩ ዓለማየሁ እና ሳዲቅ ዳሪን አሳርፈው ኃይለሚካኤል አደፍረስ እና ጋዲሳ ዋዶን ተክተው ሲገቡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ17ኛው ሳምንት ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ቋሚ አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ገብተዋል።
በፌዴራል ዋና ዳኛ አብርሃም ኮይራ አስጀማሪነት የጀመረው የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ቀዳሚ ለመሆኑ በፈጣን ሽግግር ኳሶችን ይዘው ወደ ሦስተኛው ሜዳ ክፍል ይዘው ሲገቡ ቢስተዋሉም የጠራ የግብ ማግባት አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም። በ25ኛው ደቂቃ ላይ አዳማ ከተማዎች በቆመ ኳስ በሱራፌል አዎል አማካኝነት ሙከራ አድርገው ኳሱ ለትንሽ ከፍ ካለበት አጋጣሚ ውጪ ሌላ ለግብ የቀረበ ሙከራ መመለከት ሳንችል ቀርተናል።
ጨዋታው በግብ ማግባት እንቅስቃሴ እየተቀዛቀዘ የሄደ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች በአመዛኙ መሃል ሜዳ ላይ ባደላ አጨዋወት እየተጫወቱ ደቂቃው ወደ ሀያዎቹ መጨረሻ ሲደርስ አዳማ ከተማዎች አደገኛ ሙከራ አድርገዋል። ኃይለሚካኤል አደፍረስ በግራ መስመር በኩል ኳስ ይዞ ገብቶ ከሳጥኑ ቅርብ ርቀት ላይ አክርሮ የመታውን ኳስ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ኢድሪሱ አብዱላሂ አግዶ ወደ ውጪ አውጥቶበት በማዕዘን ምት ድጋሚ ሬድዋን ሸሪፍ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ይቅር እንጂ የአዳማ ከተማዎችን የግብ ማግባት ጥረት ያሳየ አጋጣሚ ነበር።
ሁለቱም ቡድኖች ግብ ለማስቆጠር ወደፊት ለመሄድ ጥረት ያድርጉ እንጂ በአጨራረስ ላይ ደካማ እንቅስቃሴ እያደረጉ ሲቸገሩ አስተውለናል። ሆኖም ግን ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ37ኛው ደቂቃ ላይ ሳይጠበቅ ልዩነት መፍጠር የቻሉበትን ጎል መረብ ላይ አክለዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ አበባየሁ ዩሐንስ ርቀት ላይ ሆኖ አክርሮ የመታውን ኳስ የአዳማ ከተማ ተከለካዮች አግደውበት ተጨራርፋ ሳጥን ውስጥ ለነበረው አቤል ሀብታሙ ጋር ደርሳ በግንባሩ ገጭቶ አሻግሮት ብቻውን የነበረው ኢዮብ ገብረማርያም በግንባሩ ገጭቶ ወደግብነት ቀይሮ ኢትዮ ኤሌክትሪኮችን መሪ አድርጓቸዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በአጋማሹ መገባደጃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረው በእፎይታ ወደ እረፍት ለማምራት በርከት ብለው ጥቃት መሰንዘራቸው ቀጥለው በ45ኛው ደቂቃ ላይ በንክኪ የተገኘውን ኳስ ሽመክት ጉግሳ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ ጠንከር ያለ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው በንቃት ሲመልስባቸው አዳማ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት ሙሴ ከበላ 47ኛው ደቂቃ ላይ ጠንከር ያለ ሙከራ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አድርጎ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ አድኖበት በኢትዮ ኤሌክሪክ መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ አዳማ ከተማዎች የሦስት ተጫዋቾች ቅያሪ አድርገው በመግባት ጠንከር ብለው የአቻነት ግብ ፍለጋ በጫና ግብ ለማግባት ቢጥሩም ተጨማሪ ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል። በ57ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ በቀኝ መሰመር በኩል ኳስ እየገፋ ይዞ ገብቶ ያሻማውን ኳስ አቤል ሀብታሙ በግንባሩ ጨርፎ አሻግሮት ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ወደ ግብ መትቶ በግብ ጠባቂው ተመልሶ በድጋሚ አቤል ሀብታሙ አግኝቶ ከመረብ ጋር አገናኝቶ መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።
ጫናዎችን አጠናክረው የቀጠሉት አዳማ ከተማዎች በርከት ያሉ የግብ ማግባት ሙከራዎችን አድርገው በ73ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጪ የሚባል አጋጣሚ ፈጥረው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል፤ ቢንያም ዐይተን እና ነቢል ኑሪ በቅብብል ገብተው ያደረጉትን ሙከራ ግብ ጠባቂው መልሶባቸው በድጋሚ ቢኒያም አይተን ብቻውን ሆኖ አግኝቶ ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ያመከነበት ወርቃማ አጋጣሚ ሲታወስ ምናልባትም ጎል ቢቆጠር ኖሮ ወደ ጨዋታው እንዲመለሱ ሊረዳቸው የሚችል አጋጣሚ ቢሆንም ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። እንዲሁም 80ኛው ደቂቃ ላይ የቆመ ኳስ ተሻምቶ አብዱልፈታ ሰፋ በግንባሩ ገጭቶ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው በቀላሉ ተቆጣጥሮበታል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ ውጤቱን ለማስጠበቅ ሙሉ ለሙሉ ከራሳቸው ሜዳ ወረድ ብለው መከላከሉ ላይ አተኩረው ሲጫወቱ የተመለከትን ቢሆንም 90ኛ ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል፤ ያሬድ የማነ በመስመር በኩል ኳስ ይዞ ገብቶ ያሻማውን ኳስ ተቀይሮ ወደሜዳ የገባው አሸናፊ ጥሩነህ በግንባሩ ገጭቶ መረብ ላይ አሳርፎ ጨዋታው 3-0 በሆነ ውጤት እንዲጠናቀቅ ሆኗል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ለሱፐር ስፖርት የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ያጋሩ ሲሆን አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ከእዚህም በላይ ማግባት ነበረብን አሁንም መስራት ያለብን ነገር አለ፤ እኛ ሥራ እና ሥራችን ላይ ብቻ ነው የምናተኩረው የሚል አስተያየት ሲሰጡ አሰልጣኝ አብዲ ቡሊ በበኩላቸው በስሜት የመጓዝ ነገር አለ ያን ካላስተካክለን አሁንም አስቸጋሪ ነው ፤ የተሻለ ነገር ለማድረግ ብዙ እጅግ ብዙ መሥራት ያለብን ነገር አለ የሚል አስተያየት አጋርተዋል።