የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለብዙዎቹ ሴት ተጫዋቾች ተምሳሌት የሆነችውን ብርቱካን ገብረክርስቶስን በክብር እንደሚሸኛት አውቀናል።
በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ስማቸው በጉልህ ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች አንዷ የሆነችው ብርቱካን ገብረክርስቶስ ራስዋን ከብሔራዊ ቡድን ማግለሏን እና ስለነበራት ቆይታ የሰጠችውን አጭር ቃለመጠይቅ ከሰዓታት በፊት ማስነበባችን ይታወቃል። አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ባሕሩ ጥላሁን በብርቱካን ገብረክርስቶስ ሽኝት ዙርያ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተውናል።
“ብርቱካን እጅግ ድንቅ ተጫዋች ለብዙዎች ሴት ተጫዋቾች ተምሳሌት የሆነች ጠንካራ ሴት ናት። ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ ተደርጎላት እንኳን አክብራ ነው መጥታ ለፌዴሬሽኑ ያሳወቀችው ይህ ያላትን መልካም ስብዕና ያሳያል። ስለዚህ ይሄን ያህል ዓመት አቋሟ ሳይዋዥቅ ረጅም ዓመት መቆየት መቻል ለሙያ መታመንን ያሳያል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በቀጣይ ከዩጋንዳ አቻው ጋር በሚኖረው ጨዋታ ብርቱካንን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በክብር ይሸኛታል ብለውናል”።