በ18ኛው ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ዕለት የሚከናወኑ መርሐግብሮችን አስመልክተን ያዘጋጀናቸውን መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
መቐለ 70 እንደርታ ከ ወላይታ ድቻ
በመሃላቸው የሁለት ነጥቦች ልዩነት ያላቸው ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ለአሸናፊው የደረጃ መሻሻል የሚያስገኝ እንደመሆኑ ብርቱ ፍልሚያ ይደረግበታል ተብሎ ይታመናል።
በሃያ ሁለት ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች ከሁለት ተከታታይ ድል በኋላ ካስመዘገቡት የአቻ ውጤት መልስ ዳግም ድል አድርገው የመጀመሪያውን ዙር 25 ነጥቦች አስመዝግበው ለማጠናቀቅ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በአዳማ ከተማ ሽንፈት አልባ ጉዞ በማድረግ ላይ የሚገኙት ምዓም አናብስት በነገው ዕለት የመጀመርያውን ዙር የመጨረሻ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፤ በዙሩ አምስት ድል፣ ሰባት አቻ እና አራት ሽንፈት ያስመዘገበው ቡድኑ በተለይም ባለፉት ስድስት ሳምንታት ያሳየው ብቃት የመሻሻሉ ዋነኛ ማሳያ ነው። በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ስድስት ነጥቦችን ጥለው አስራ ሁለት ነጥቦችን ያሳኩት መቐለዎች በውድድር ዓመቱ ምርጥ አቋማቸው ላይ ይገኛሉ። ከሰንጠረዡ አጋማሽ ከፍ ለማለት እያደረጉት ያሉትን ጉዞ ለማሳመርም ነገ ሙሉ ነጥቦችን ማሳካት በእጅጉ አስፈላጊያቸው ይሆናል። የመጨረሻው ጨዋታ ከሌላው ጊዜ በተለየ በጥሩ የማጥቃት መንፈስ ጨዋታውን ቢከውኑም በዋነኝነት ለጥንቃቄ ከፍ ያለ ትኩረት የሚሰጡት ምዓም አናብስት በፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸው ፍጥነት ላይ የተመሰረተው መልሶ ማጥቃት ዋነኛው የግብ መፍጠሪያ መንገዳቸው መሆኑ ነገም የሚቀጥል ይመስላል።
በነገው ዕለት በመከላከሉ ረገድ ድክመት የሚታይበት እና በውድድር ዓመቱ ከፍተኛ የግብ መጠን ካስተናገዱ ክለቦች ተርታ የሚመደበውን ቡድን መግጠማቸውም እንደባለፈው ሳምንት ሁሉ በተሻለ የማጥቃት ድፍረት ወደ ሜዳ እንደሚገቡ መገመት ይቻላል።
በሃያ ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የጦና ንቦቹ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት አገግመው ደረጃቸውን ለማሻሻል ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ያስፈልጋቸዋል።
በአምስት ሳምንታት የአዳማ ቆይታቸው አንድ ድል ብቻ ያሳኩት ወላይቻ ድቻዎች ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በድምሩ ከአራት ነጥብ በላይ ማግኘት ተስኗቸው ደረጃቸው እንዲያሽቆለቁል ሆኗል።
እርግጥ ቡድኑ ከሰባት ሽንፈት አልባ ሳምንታት መልስ ሦስት ሽንፈቶች አስተናግዶ በመጠነኛ የውጤት መጥፋት ጎዳና እየተጓዘ ቢገኝም በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ግን ብዙም ለትችት የሚዳርገው ብቃት አያሳይም። ሆኖም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስተናገደው እና በውድድር ዓመቱ ሃያ ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀቱ ግን ከወዲሁ ስህተቱን ማረም ካልቻለ በቡድኑ ውጤት አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መቀጠሉ አይቀርም።
ምንም እንኳን ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠር ቢችልም በውድድር ዓመቱ ከፍተኛ የግብ መጠን ካስቆጠሩ አራት ክለቦች አንዱ የሆነው ቡድኑ ካለበት ወቅታዊ የግብ ማስቆጠር ችግር እና ከመቐለ የመከላከል ጥንካሬ አኳያ የተጋጣሚን የኋላ ክፍል መረበሽ መቻሉ ግን አጠራጣሪ ነው።
በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ሸሪፍ መሐመድ ከቅጣት ቢመለስም የአብሥራ ተስፋዬ፣ መናፍ ዐወል፣ አሸናፊ ሀፍቱ፣ አማኑኤል ልዑል፣ ክብሮም አፅብሐ እና ተመስገን በጅሮንድ ግን በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው። በወላይታ ዲቻ በኩል የቡድኑ ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂ ቢንያም ገነቱ በባለፉት ቀናት ልምምዶች ቢሳተፍም ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ነገ በአሰልጣኝ አባላቱ የሚወሰን ሲሆን ተከላካዩ ናትናኤል ናሲሮም በተመሳሳይ ለጨዋታው የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል። ሌሎቹ የጦና ንቦቹ የቡድን አባላት ለነገው ጨዋታ ተሟልተው እንደሚቀርቡ አውቀናል።
ቡድኖቹ በሊጉ ለአራት ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን መቐለ 3 በማሸነፍ የበላይነት አለው። ቀሪዋን ደግሞ ድቻ አሸንፏል። መቐለ 4 ሲያስቆጥር ድቻ አንድ አስቆጥሯል።
አርባምንጭ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና
በሦስት ነጥቦች እና በሁለት ደረጃዎች ልዩነት የተቀመጡትን ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።
በሦስት መርሐግብሮች ተከታታት ድሎች ካስመዘገቡ ወዲህ በመጨረሻው ጨዋታ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ነጥብ ተጋርተው በመውጣት ነጥባቸውን ሃያ ሦስት ያደረሱት አዞዎቹ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች መልስ ወደ ሜዳ ከሚገቡት ነብሮቹ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ። አዞዎቹ ከዚህ ቀደም ዋነኛ ችግራቸው የነበረው የወጥነት ችግር ቀርፈዋል፤ ቡድኑ የአዳማ ቆይታውን በሽንፈት ቢጀምርም ከዛ በኋላ በተከናወኑ አራት መርሐግብሮች ሽንፈት አልቀመሰም። በተጠቀሱት የመጨረሻ አራት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ሁለት ነጥብ አስሩን በእጁ ያስገባው ቡድኑ ከውጤቱም ባሻገር የሚታይ ለውጥ አምጥቷል። በተለይም ለሳምንታት ውጤታማነቱ ቀንሶ የነበረው እና በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ሰባት ግቦችን ያስቆጠረው የማጥቃት ክፍሉ ለቡድኑ ውጤት ማማር የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል። በነገው ጨዋታ ግን ወሳኝ ተሰላፊዎቹን ማጣቱ ተከትሎ በቀደመው ብቃቱ ለመገኘት እንደሚቸግረው መገመት ይቻላል።
ለስምንት የጨዋታ ሳምንታት ካሳየው ድንቅ ብቃት በኋላ መጠነኛ መንገራገጭ የገጠመው ሀዲያ ሆሳዕና መሪዎቹን እግር በእግር ለመከታተል በመደዳ ከገጠሙት ሁለት ሽንፈት መልስ ድል ማድረግ አስፈላጊው ነው።
በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ተከታታይ ሽንፈት የገጠመው የነብሮቹ ስብስብ ከዚህ ቀደም የነበረው የማጥቃት ክፍል ጥንካሬ በመጠኑ ያጣ ይመስላል። ሽንፈት በቀመሰባቸው የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት ያልቻለው ቡድኑ በድሬ የመጨረሻ አምስት ሳምንታት ስምንት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም በአዳማ የአምስት ሳምንታት ቆይታው ማስቆጠር የቻለው የግብ መጠን ሦስት ብቻ መሆኑ ሲታይ የማጥቃት አጨዋወቱ መቀዛቀዙ ማሳያ ነው። በፈጣን የመስመር ተጫዋቾቻቸው ላይ የተንጠለጠለ የማጥቃት አማራጭን ተግባራዊ የሚያደርጉት ነብሮቹ በነገው ዕለት ይበልጥ በሰንጠረዡ አናት ተፅዕኖ ለመፍጠር ማጥቃታቸው ተለዋዋጭ ማድረግ እና ወደ ውጤታማነቱ መመለስ ይጠበቅባቸዋል።
በአርባምንጭ ከተማ በኩል ጉዳት ላይ ከነበሩት ሳሙኤል አስፈሪ ፣አበበ ጥላሁን እና አሸናፊ ተገኝ በተጨማሪ አህመድ ሁሴን እና ካሌብ በየነ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል። በተጨማሪም በህመም ምክንያት ባሳለፍነው ሳምንት ጨዋታ ላይ መሰለፍ ያልቻለው በፍቅር ግዛው አገግሞ ልምምድ ቢጀምርም የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው። በሀዲያ ሆሳዕና በኩል መለሰ ሚሻሞ እና በረከት ወንድሙ አሁንም ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው ከስብስቡ ውጭ ሲሆኑ የመስመር ተከላካዩ በረከት ወልደዮሐንስም በቅጣት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ነው። ተከላካዩ ዳግም ንጉሤ ምንም እንኳን ከህመሙ አገግሞ ወደ ልምምድ ቢመለስም ለነገ ጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ነው። ከዚህ ውጭ የነብሮች ስብስብ ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።
ቡድኖቹ በሊጉ ከተገናኙባቸው ስድስት ጨዋታዎች አራቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ሁለቱም አንድ አንድ ጊዜ ድል አድርገዋል። በጨዋታዎቹ ነብሮቹ ስምንት አዞዎቹ ደግሞ ሰባት ግቦችን አስቆጥረዋል።