የ18ኛ ሳምንት መገባደጃ የሆኑ መርሐግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ !
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሀዋሳ ከተማ
ከአቻ መልስ እጅግ አስፈላጊ ድል አስመዝግበው ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርቡ እና በደረጃ ሰንጠረዡ ተከታትለው የተቀመጡት ሀምራዊዎቹን እና ሐይቆቹን የሚያገናኘው ጨዋታ ብርቱ ፍልሚያ ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።
ሊጉ በአዳማ መደረግ ከጀመረ በኋላ የተሻሻለ የሚመስለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለበርካታ ጊዜያት ከነበረበት የአደጋው ቀጠና ለመራቅ እና ከወራጅ ቀጠናው ያለበት የሦስት ነጥቦች ብልጫ
ለማሳደግ ባሳለፍነው ሳምንት አዳማ ከተማ ላይ ያሳካውን ድል ለመድገም ወደ ሜዳ ይገባል።
በመጨረሻው ጨዋታ አዳማ ከተማን ከጥሩ ብቃት ጋር ያሸነፈው ቡድኑ አንድ ጨዋታ በእጁ ይዞ ከነገው ተጋጣሚው በሦስት ነጥቦች ርቀት ላይ ይገኛል፤ ነጥቡንም 18 ማድረስ ሲችል ነገ አሸንፎ ከፍ ባለው የሰንጠረዡ ክፍል ላለው ፉክክር ለመጠጋት ይፈልጋል። ንግድ ባንክ አዳማ ከተማን በረታበት ጨዋታ በአቀራረቡ ውስጥ ጎሎች ለማግኘት የነበረውን ቀመር ያገኘ ይመስላል።
ሁለት ግብ ካስቆጠረበት የወልዋሎ ጨዋታ በኋላ በ90 ደቂቃ ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ከብዶት የነበረው ቡድኑ ከዘጠኝ የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ግቦች ማስቆጠር ችሏል። ይህንን የተሻሻለው ጠንካራ ጎን ማስቀጠልም ከነገው ጨዋታ አንዳች ነገር ይዞ እንዲወጣ ይረዳዋል ተብሎ ይታመናል።
ለበርካታ ሳምንታት በደረጃ ሰንጠረዡ የታችኛው ክፍል ተቀምጦ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ አስራ አንድ የጨዋታ ሳምንታትን መጠበቅ ግድ ብሎት የነበረው ሀዋሳ ከተማ ያለፉትን አራት ጨዋታዎች በእንቅስቃሴም ሆነ በውጤት ደረጃ መሻሻል እያሳየ ይገኛል። ለወትሮ በአብዛኞቹ የሜዳ ክፍሎች ያለመቀናጀት ችግር የነበረበት ቡድኑ ከቅርብ ሳምንታት በኋላ ጥንካሬውን ያገኘ ይመስላል፤ በዚህ የውድድር ዓመት ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ከሚገኙት መቻል እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረጋቸው ሁለት መርሐግብሮች ያገኛቸው አራት ነጥቦች እንዲሁም የቡድኑ አጠቃላይ እንቅስቃሴ እና መንፈስም ያለበትን አሁናዊ መነሳሳት ያሳየ ነው።
ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ወሳኝ ድል ማስመዝገብ የሚጠበቅበት ቡድኑ በተከታታይ ሳምንታት በአቀራረብ ረገድ ተመሳሳይነት ያላቸው ቡድኖች እንደመግጠሙ የጨዋታ ዕቅዱ ላይ ለውጦች ያደርጋል ተብሎ አይጠበቅም፤ በዚህም ቀጥተኝነትን ሊያዘወትር እንደሚችል ይገመታል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ጉዳት ላይ ያሉት ፉዓድ ፈረጃ እና ሱሌይማን ሀሚድ ባለማገገማቸው በነገው ጨዋታም አይሰለፉም፤ የተቀሩት ተጫዋቾች ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በሀዋሳ ከተማ በኩል የፊት መስመር ተጫዋቹ ተባረክ ሂፋሞ በ5 ቢጫ በቅጣት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆኑን አውቀናል።
በሊጉ በሰላሳ ሰባት ጨዋታዎች የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በአስራ ሶስት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ሲፈፅሙ ንግድ ባንክ በአስራ አራት እንዲሁም ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በአስር ጨዋታዎች ድል ማድረግ ችለዋል። በጨዋታዎቹ ንግድ ባንኮች አርባ እንዲሁም ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ ሰላሳ ሰባት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።
ኢትዮጵያ መድን ከ ፋሲል ከነማ
ከድል መልስ የሚገናኙ ቡድኖች የሚያደርጉት እና ከፍተኛ ፍልሚያ ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቀው ጨዋታ የሳምንቱ መቋጫ መርሐግብር ነው።
በአሁኑ ሰዓት እንደ አሰልጣኝ ገብረመድኅን እንዲሁም ኢትዮጵያ መድን አስደናቂ ጊዜ በማሳለፍ ላይ የሚገኝ አለ ለማለት አያስደፍርም። በተከታታይ ስድስት የጨዋታ ሳምንታት ድል በማድረግ በሰላሣ ሁለት ነጥቦች በሊጉ መሪነት የተሰየሙት መድኖች መሪነታቸው ለማደላደል ዐፄዎቹን ይገጥማሉ።
ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ የአንድ ለባዶ ድል ማስመዝገብ ቢችልም ከገጠማቸው ጠንካራ ተጋጣሚዎች አንፃር ያሳየው ወጥነት ያለው ብቃት የዋንጫ ተፎካካሪዎች ባህሪ አላብሶት ታይቷል። ቡድኑ በየጨዋታዎች ላይ ከፍ ያለ ፍልሚያ ከተጋጣሚዎቹ ቢመጣም እስከጨዋታው ፍፃሜ በሚያደርገው ተጋድሎ ውጤት ይዞ የመውጣት ባህሪው አሁንም ቀጥሏል። ይህ ቡድናዊ ባህሪ ከበድ ያለ ፍልሚያ ለሚስተናገድባቸው ለእንደነገ ዓይነት ጨዋታዎች እጅግ አስፈላጊ መሆኑ እሙን ነው። የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ በአመዛኙ ከሽግግሮች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የሚሞክረው መድን የፊት መስመር የሦስትዮሽ አስፈሪነቱን ጠብቆ መቀጠሉ ሌላው የስብስቡ በጎ ጎን ሆኖ ይነሳል።
ድሬዳዋ ከተማን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ በአዳማ ከተማ የመጀመርያ ድሉን ያገኘው ፋሲል ከነማ በሃያ ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በሁለት ተከታታይ ድሎች ድሬን የተሰናበቱት ዐፄዎቹ በአዳማ ቆይታቸው በአራት ጨዋታዎች ድል ሳያደርጉ ቢቆዩም ድሬዳዋን በማሸነፍ ደረጃቸውን አሻሽለዋል። በእንቅስቃሴ ደረጃ ለክፉ የሚሰጥ ነገር በአምስቱ ጨዋታዎች ያላሳየው ፋሲል በንፁህ የግብ ዕድሎች ፈጠራ ረገድ ያለበትን ክፍተት ዋጋ እያስከፈለው ይመስላል። በተለይም በተጋጣሚ ሳጥን አቅራቢያ የሚደረጉ ቅብብሎቹ ጥራት በሚፈለገው ልክ አለመሆን ባለፉት ጨዋታዎች እንደልቡ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር እንዲቸገር ሲያደርገው ዐይተናል።
ቡድኑ ምንም እንኳን በሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ካስቆጠረባቸው መርሐግብሮች መልስ ድሬዳዋ ከተማ እና መቻል ላይ ሦስት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም በነገው ዕለት ዝቅተኛ የግብ መጠን ያስተናገደ እና እምብዛም ለጥቃት የማይጋለጥ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድን እንደመግጠሙ የማጥቃት አጨዋወቱን ጥራት ከፍ ማድረግ ይኖርበታል።
በነገው ዕለት በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ድል ለማድረግ እያለሙ ወደ ሜዳ የሚገቡት ዐፄዎቹ ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማስመዝገብ ከቻሉ እስከ አራት ደረጃዎች የማሻሻል ዕድል አላቸው። ይህን ተከትሎ ከውጤት አስፈላጊነቱ እና ከተጋጣሚው ክብደት አንፃር ከሌላው ጊዜ በተለየ ዝግጁነት ወደ ጨዋታው ይቀርባል ተብሎ ይገመታል።
ቡድኖቹ በሊጉ 5 ጊዜ ተገናኝተው አንድ አንድ ጨዋታ በእኩሌታ ሲያሸንፉ ሦስቱ ጨዋታዎች አቻ ተጠናቀዋል። መድን ሁለት ጎል ሲያስቆጥር ፋሲል ሦስት ጎል ማስቆጠር ችሏል።