ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከታታይ ድል አስመዝግቧል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ሀዋሳ ከተማን 2ለ0 በመርታት ደረጃቸውን ማሻሻል ችለዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ17ኛው ጨዋታ ሳምንት አዳማ ከተማ 2ለ0 ሲያሸንፋ ይዘው ከገቡት ቋሚ ስብስባቸው አንድ ለውጥ በማድረግ ዳዊት ዮሐንስን አስወጥተው በዮናስ ለገሰ ተክተው ሲገቡ ሀዋሳ ከተማዎች በ17ኛው ሳምንት መቻልን 1ለዐ ካሸነፉበት ቋሚ አሰላለፍ ሁለት ለውጦችን አድርገው፤ ፀጋአብ ዮሐንስን በበረከት ሳሙኤል ፣ ተባረክ ሄፋሞን በአማኑኤል ጎበና ተክተው ገብተዋል።

ሁለት ተቀራራቢ ውጤት ይዘው ከወራጅ ቀጠና ፈቀቅ ለማለት ጥረት የሚያደርጉ ቡድኖችን ያገናኘው የእለቱ ቀዳሚ ጨዋታ አጀማመሩ ጥንቃቄ የሰፈነበት ሲሆን የመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ቡድኖቹ የግብ ማግባት ፍላጎት በማሳየት ወደፊት ለመሄድ ይጣሩ እንጂ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉበት ነበር።

እምብዛም ግልፅ የግብ ማግባት እንቅስቃሴ ሳያስመለክት በቀጠለው በአጋማሹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ቶሎ ቶሎ ወደ ተቀራኒ ቡድን ሜዳ በመድረስ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። ሀዋሳ ከተማዎቹ በአንፃሩ ወደፊት በመሄድ ረገድ ፍፁም የተዳከመ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ያስተዋልን ሲሆን በ17ኛው ደቂቃ ሰይድ ሀብታሙ በመልስ ምት ከተካካይ ጀርባ ያሻገረውን ኳስ አሊ ሱሌይማን በፍጥነት ለመድረስ ጥረት አድርጎ ፓላክ ቾል የቀደመበት አጋጣሚ ሐይቆቹን ቀደሚ ለማድረግ ቀርቦ የነበር ክስተት ነበር።

በአጋማሹ አካፋይ ላይ ንግድ ባንኮች የቆመ ኳስ ተሻምቶ በባሲሩ ኡመር አማካኝነት መረብ ላይ ቢያሳርፉም ረዳት ዳኛው ከጨዋታ ውጪ ብለው የተሻረባቸው አጋጣሚ ሲጠቀስ የቀዳሚነት ጎል ፍለጋ ጫን ብለው ወደ ተጋጣሚያቸው ግብ ክልል መግባት አጠናክረው ቀጥለው የመጀመሪያ ጎል መሆን የቻለውን አጋጣሚ በፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ወደ ግብነት ቀይረውታል ፤ አዲስ ግደይ እና ሳይመን ፒተር በጥሩ ቅብብል ኳስ ይዘው ሳጥን ውስጥ ሲገቡ የሐይቆቹ ተከላካይ እንየው ካሣሁን አዲስ ግደይ ላይ በፈፀመው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቷቸው ፤ አዲስ ግደይ በመምታት መረብ ላይ አክሎ መሪ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

የአጋማሹ መገባደጃ ላይ ሁለቱም ቡድኖች በፈጣን ሽግግር ግብ ለማስቆጠር ወደፊት ለመሄድ ጥረት ያድርጉ እንጂ ኳሶቹ ቶሎ ቶሎ እየተቋረጡባቸው ሲቸገሩ አስተውለናል። ንግድ ባንኮች ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን 41ኛው ደቂቃ ላይ ኪቲካ ጅማ ርቀት ላይ ሆኖ ጠንከር ያለ ሙከራ አድርጎ ለትንሽ ከፍ ያለበት ሲታወስ የሐይቆቹ አቤነዘር ዮሐንስ በቆመ ኳስ ያደረገው ጠንከር ያለ ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ የቀረው አጋጣሚ በአጋማሹ የተገኙ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ሆነው አጋማሹ ሊገባደድ ተገዷል።

 

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ሐይቆቹ ፈጣን እንቅሰቃሴ አድርገው የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። በጥሩ ሂደት የተገኘውን ኳስ አዲስ ግደይ በግራ መስመር በኩል ሆኖ ወደ ግብ አሻምቶ ሳይመን ፒተር  በግንባሩ ገጭቶ መረብ ላይ አክሎ መሪነቻውን ማጠናከር ችሏል።

ንግድ ባንኮች ኳስ ተቆጣጥረው በመጫወት በተደጋጋሚ የሐይቆቹን ተከላካይ መስመር የፈተኑ አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ አስተውለናል። ሐይቆቹም በአንፃራዊነት በንቃት በመልሶ ማጥቃት ረጃጅም ኳሶችን ተጠቅመው ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል። ሆኖም ግን ይሄ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ሳይፈጥሩ ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ ሀያ ደቂቃዎች አምርቷል። ጨዋታው 75ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ንግድ ባንኮች ርቀት ላይ የቆመ ኳስ አግኝተው አዲስ ግደይ ጠንከር ያለ ኳስ ቀጥታ ወደ ግብ መጥቶ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት አጋጣሚ ዒላማውን የጠበቀ ሌላኛዋን ግብ ሊያስገኛቸው የቀረበ ሙከራ ነበር።

በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ሀዋሳ ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ኳስ መስርተው ከራሳቸው ሜዳ ጀምረው ሶስተኛውን የሜዳ ክፍል መርገጣቸውን ያጠናከሩ ቢሆንም የግብ ልዩነታቸውን አስፍተው በጥሩ ጥምረት አጫጭር የኳስ ንክኪ እያደረጉ በአማዛኙ በእራሳቸው ሜዳ ላይ ጨዋታ ምርጫቸውን ያደረጉትን የንግድ ባንኮችን ተከላካዮች አልፈው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል። 83ኛው ደቂቃ ላይ በንግድ ባንኩ ግብ ጠባቂ ስህተት መነሻነት የተገኘችውን ኳስ ተቀይሮ ሜዳ የገባው ያሬድ ብሩክ ግልፅ ግብ መሆን የሚችል አጋጣሚ አግኝቶ አምክኖታል።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጨናቆ ጭማሪ በታየው ላይ ሀዋሳ ከተማዎች ሙሉ ለሙሉ ወደፊት ሄደው ወደጨዋታ ሊመልሳቸው የሚችል ኳስ መረብ ለማሳረፍ ጥረት ሲያደርጉ ቢስተዋሉም ንግድ ባንኮች እጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ እና ሁለት ንፁህ ጎል አሳልፈው ላለመስጠት የሚቀመሱ ሊሆኑላቸው አልቻሉም። ጨዋታው ተጨማሪ ግብ የሚያስተናግድ ቢመስልም ግብ ሳይቆጠር 2ለ0 በሆነ ውጤት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱም ቡድን አስልጣኞች አስተያየተቸውን አጋርተዋል ፤ ጊዜያዊ የሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ ”ከፍተኛ ዝግጅት አድርገን ነበር ግን ጨዋታ ከጠበቅነው በላይ ሆኖብናል ፤ በአጥቂ መስመር ላይ ተጫዋቾች ተጎድተውብናል የእነሱ አለመኖር ላይ የተጋጣሚያችን ጥንካሬ ተደምሮ ይሄን ውጤት አስመዝግበናል፤ ብዙ ነገሮች መቀየር አለባቸው” የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ በበኩላቸው ” ውጤት በሚያስፈልገን ሰዓት ሶስት ነጥብ ማስመዝገባችን ለቀጣይ ጨዋታ ተነሳሽነትን ይፈጥራል፤ ሁልጊዜ ሜዳ ስንገባ የተሻለ ቦታ ላይ እራሳችን ለማድረስ ነው ምንገባው። ተከታታይ ጨዋታ ብታሸነፍ ወደ ላይ ትመጣለህ እሱ አንዱ ሊጉ ላይ ያለ አድቫንቴጅ ነው” የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።