ሪፖርት | ዐፄዎቹ ጣፋጭ ድል ተጎናጽፈዋል

የአንዋር ሙራድ ድንቅ ግብ ዐፄዎቹን አሸናፊ ስታደርግ መድንም ከተከታታይ ስድስት ድሎች በኋላ ሽንፈት ገጥሞታል።

ኢትዮጵያ መድኖች ሀዲያ ሆሳዕናን ካሸነፈው ቋሚ አሰላለፍ ረመዳን የሱፍን በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በቋሚ አሰላለፍ በተካተተው ሐቢብ ከማል ሲተኩ ዐፄዎቹ ድሬዳዋ ከተማን ከረታው ቋሚ አሚር ሙደሲር እና ማርቲን ኪዛን አሳርፈው በኤፍሬም ኃይሉ እና ቢንያም ላንቃሞ ተክተው ገብተዋል።

በዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ መሪነት ተጀምሮ እንደተጠበቀው ጠንካራ ፉክክር ያስመለከተን የመጀመርያው አጋማሽ አትዮጵያ መድኖች ከተጋጣሚያቸው የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳዩበት ነበር። ጨዋታው ምንም እንኳን ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ቢሆንም ጥቂት በሙከራዎች የታጀበ አልነበረም። ወገኔ ገዛኸኝ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ሆኖ መቷት ዮሐንስ ደርሶ ከጨርፋት በኋላ ሀቢብ ከማል የሞከራት ኳስ በኢትዮጵያ መድን፤ በመከላከሉ ረገድ ውጤታማ አርባ አምስት ደቂቃዎች ባሳለፉት ፋሲል ከነማዎች በኩል ደግሞ ጌታነህ ከበደ ከርቀት ያደረጋት ሙከራ በአጋማሹ የተደረጉ ሙከራዎ ነበሩ።

በእንቅስቃሴ ደረጃ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የነበረው ሁለተኛው አጋማሽ ፋሲል ከነማዎች ተሻሽለው የቀረቡበት ነበር። በአጋማሹ የመጀመርያ ደቂቃዎች እንዋር ሙራድ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ባደረገው ሙከራ እና ጌታነህ ከበደ በመቀስ ባደረገው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ግብ ለማግኝነት ጥረት ያደረጉት ዐፄዎቹ 76ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር ችለዋል።

ተካልኝ ደጀኔ ከቆመ ኳስ አሻምቷት የመድን ተከላካዮች ከጨረፏት በኋላ አንዋር ሙራድ በአግባቡ አብርዶ ከመረብ ጋር ያዋሃዳት ግብም ዐፄዎቹን መሪ ያደረገች ግብ ነች። ከግቡ በኋላ መድኖች የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ተጭነው ቢጫወቱም ጥድፍያ የነበረው አጨዋወታቸው የግብ ዕድል አልፈጠረም፤ የተቀሩት ደቂቃዎችም በተደጋጋሚ ፊሽካዎች እየተቆራረጡ የተከናወኑ ነበሩ።

 

ቀደም ብለው የሀዲያ ሆሳዕናን የተከታታይ ድሎች ጉዞ የገቱት ፋሲሎች ዛሬም በተመሳሳይ የመድንን ተከታታይ ጉዞ መግታታቸውን ተከትሎ ደረጃቸው ወደ 8ኛነት ከፍ ብሏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጨዋታው ጠንካራ እንደነበር ከገለፁ በኋላ ነጥብ ይዘው የሚወጡበት ዕቅድ ይዘው እንደገቡ በመግለፅ ቡድናቸው በሁለቱም አጋማሾች ዕድል በመፍጠር ረገድ መጥፎ እንዳልነበር ገልፀዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም ጨዋታው ጠንካራ እንደሚሆን ገምተው እንደነበር በመጥቀስ ካሉበት ቀጠና ለመውጣት ድሉ አስፈላጊ እንደነበር ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መድን አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በበኩላቸው ውጤቱ መጥፎ እንደሆነ በመግለፅ ሽንፈት ሊያጋጥም የሚችል እንደሆነ ጠቅሰው በተጫዋቾቻቸው ተነሳሽነት እና ፍላጎት ደስተኛ እንደሆኑ ገልፀዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም ጨዋታው በኃይል አጨዋወት የተሞላ እንደነበር ገልፀው ተጋጣሚያቸው ሙሉ ኃይሉን መከላከሉ ላይ ማድረጉ እንዲሁም የሜዳው ምቾት በምንፈልገው መጠን ሙከራዎች እንዳናደርግ አድርጎናል ብለዋል።  በስተመጨረሻም ያስመዘገቡት የመጀመርያው ዙር ውጤት ከዕቅዳቸው በላይ እንደሆነ ጠቅሰዋል።