መረጃዎች | 74ኛ የጨዋታ ቀን

የመጀመርያው ዙር መገባደኛ የሆነው 19ኛው ሳምንት ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀምራል፤ በወራጅ ቀጠናው የሚገኙ ሦስት ቡድኖች ዙሩን በአወንታዊ ውጤት ለማጠናቀቅ የሚፋለሙባቸውን መርሐግብሮች የተመለከቱ መረጃዎችንም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

አዳማ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

አዳማ ከተማ በመደዳ ከገጠሙት ሽንፈቶች ለመላቀቅ ሲዳማ ቡና ደግሞ ተከታታይ ሁለተኛ ድሉን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ጨዋታ የ19ኛው ሳምንት ቀዳሚ መርሐግብር ነው።

በአሠልጣኝ አብዲ ቡሊ የሚመራው አዳማ የከተማውን ቆይታ በድል ቢጀምርም ከዛ በኋላ በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች እጅ ሰጥቶ በመጥፎ የውጤት ጉዞ ላይ ይገኛል።

በአስራ አምስት ነጥቦች 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ ከወዲሁ በብዙ ነጥቦች ላለመራቅ እና አንድ ደረጃ አሻሽለው የመጀመርያውን ዙር ለማጠናቀቅ በብዙ ረገድ ተሻሽለው መቅረብ ግድ ይላቸዋል። የአሰልጣኙ ተቀዳሚ የቤት ሥራ የሚሆነው ደግሞ እስካሁን 25 ግቦችን ያስተናገደውን የሊጉን ደካማ የመከላከል ውቅር ማስተካከል እንደሚሆን ይጠበቃል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አስራ አንድ ግቦች ማስተናገድ የቻለው ቡድኑ ከዚህ ባለፈም በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር አለመቻሉ እና ግቦች ላይ ዐይናፋር የመሆኑ ነገር ተዳምሮ ያለበትን ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል።

አሰልጣኙ ከነገው ጨዋታ ነጥብ ይዞ ለመውጣት በጉዳቶች የሳሳው እና ባለፉት ጨዋታዎች በርከት ያሉ ግቦች ያስተናገደው
የመከላከል አደረጃጀታቸውን ማስተካከል ቀዳሚ ሥራቸው መሆን ይገባዋል።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ ከገጠማቸው ሽንፈት በማገገም
በመጨረሻው ጨዋታ ስሑል ሽረ ላይ ወሳኝ ድል ያሳኩት ሲዳማ ቡናዎች በደረጃ ሰንጠረዡ ባለው የነጥብ መቀራረብ ምክንያት ከነገው ጨዋታ ሦስት ነጥቦችን ማግኘት ከፍ ያለ የደረጃ መሻሻል ሊያስገኝላቸው የሚችል በመሆኑ ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው።

በሃያ ሁለት ነጥቦች በ11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች በአዳማ ቆይታቸው ያሳኩት ትልቁ ነገር ሽንፈት መቀነሳቸው ነው። በድሬዳዋ ከተማ የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች ውስጥ በአራቱ ሽንፈት በማስተናገድ በመጥፎ ትዝታ ከተማዋን የተሰናበተው ቡድኑ በስድስት ሳምንታት የአዳማ ቆይታው ያስተናገደው ሽንፈት አንድ ነው። ይህም በተደጋጋሚ ሽንፈቶች የራስ መተማመኑ ወርዶ ለነበረው ስብስብ አውንታዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። ሲዳማ ቡናዎች ምንም እንኳን ከመጥፎው ተከታታይ ውጤት ማገገም ቢችሉም በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ያላቸው ድክመት ግን አሁንም አብሯቸው ዘልቋል። ቡድኑን ከተቀላቀሉ ወዲህ የተከላካይ መስመሩን በማስተካከል ረገድ የሚደነቅ ሥራ የሠሩት አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ቡድናቸው ከመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች በአራቱ መረቡን ሳያስደፍር እንዲወጣ ያስቻለ ሁነኛ መፍትሔ ማበጀት ቢችሉም የፊት መስመሩን ጥንካሬ መመለስ ግን ቀላል አልሆነላቸውም።

በፊት መስመር ተሰላፊዎች ጥራት እና ጥልቀት
በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ካሉት ቡድኖችም ጭምር የተሻለ ፀጋ ያለው ቡድኑ የመጀመርያውን ዙር በድል ለመቋጨት የግብ ማስቆጠር ድክመቱን መቅረፍ ይኖርበታል።

በአዳማ ከተማ በኩል ዳግም ተፈራ ፣ ፍቅሩ ዓለማየሁ ፣ አድናን ረሻድ እና ፍቃዱ ደነቀው በጉዳት ምክንያት አይኖሩም። ሲዳማ ቡናዎች በተደጋጋሚ ጊዜ የቡድን ዜና ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው መረጃውን ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሁለቱ  ቡድኖች ከዚህ ቀደም በተገናኙባቸው 26 ጊዜያት ሲዳማ ቡና 9 አዳማ ከተማ ደግሞ 7 ጊዜ ድል ሲቀናቸው 10 ጨዋታዎች በአቻ የተጠናቀቁ ናቸው። በግንኙነታተቻው ሲዳማዎች 23 አዳማዎችም በተመሳሳይ 23 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

ስሑል ሽረ ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ

በሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኙትን ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ለቡድኖች ካለው ትርጉም አንፃር በጉጉት ይጠበቃል።

በሊጉ የአዳማ ከተማ ቆይታ ዝቅተኛውን ነጥብ በማስመዝገብ ቀዳሚ የሆኑት ስሑል ሽረዎች ከደካማው አሁናዊ ብቃታቸው ለማገገም ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው።

በአዳማ ባከናወናቸው ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ስምንት ነጥቦች አንዱን ብቻ ያሳካው ሽረ በአራት ነጥቦች የሚበልጠውን ወልዋሎ ነገ በመፋለም ቢያንስ በወራጅ ቀጠናው ካሉ ክለቦች ጋር በነጥብ ተስተካክሎ የመጀመርያውን ዙር ለማገባደድ ድልን እያሰበ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይታመናል። ያለ ድል ያለፉትን ስድስት የጨዋታ ሳምንታት ያሳለፈው ቡድኑ ካለፉት አስራ አምስት የሊግ ጨዋታዎች ያስመዘገበው የድል መጠን አንድ ብቻ ነው። ቡድኑ ከውጤቱም ባሻገር በሊጉ ጅማሮ ከነበረው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አንፃር በብዙ ረገድ ተዳክሟል። በውድድር ዓመቱ አስራ ስምንት ግቦች ያስተናገደው እና ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር መውጣት የተሳነው የመከላከል አደረጃጀት እንዲሁም በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት ጥምረትም የቡድኑ ዋነኛ ድክመቶች ናቸው።

ስሑል ሽረ በሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ካስተናገደባቸው መርሐግብሮች ወዲህ ቢያንስ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ሳያስተናግድ በመውጣት የሚቆጠሩበት ግቦች መጠን መቀነስ ቢችልም በመጨረሻው ጨዋታ ቡድኑን ዋጋ ያስከፈሉ በርካታ ግለሰባዊ የመከላከል ስህተቶች ተስተውለውበታል። ከምንም በላይ  የማጥቃት አማራጮቹ ውስን መሆናቸው ለተጋጣሚ ቡድኖች በቀላሉ የሚተነበይ አድርጎታል።

 

ከነገው ተጋጣሚያቸው በአምስት ነጥቦች ርቀት ላይ የሚገኙት ወልዋሎዎች ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት የሚችሉ ከሆነ የነጥብ ልዩነቱን አጥብበው ዙሩን የማጠናቀቅ ዕድል ይኖራቸዋል።

በሰባት ነጥቦች በሊጉ ግርጌ የሚገኙት ቢጫዎቹ
በተከታታይ ሁለት ሳምንታት እየመሩ አቻ የሆኑበትን እና አራት ነጥብ እንዲጥሉ የተገደዱባቸውን ጨዋታዎች በቁጭት እያሰላሰሉ ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ነገ ከስሑል ሽረ ጋር ብርቱ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል።

ወልዋሎዎች ከተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ባለፉት አራት ጨዋታዎች የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ነጥብ መሰብሰብ ቢጀምሩም ውጤት ማስጠበቅ ዋነኛ ድክመታቸው ነው። ከመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ውስጥ ከሀዋሳ ከተማ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ድሬዳዋ ከተማ ጋር በተከናወኑ መርሐግብሮች ጨዋታውን መምራት ቢችሉም የተጋጣሚን እንቅስቃሴ ካለማንበብ እና ከትኩረት ማነስ ከመነጩ ምክንያቶች ውድ ነጥቦችን ጥለዋል። በነገው ጨዋታም በትኩረት ማነስ ምክንያት የሚመነጩ ግለሰባዊ እና መዋቅራዊ ድክመቶችን መቀነስ እንዲሁም ባለፉት አራት ጨዋታዎች በተከታታይ ኳስና መረብ ማገናኘት የቻለው የማጥቃት አጨዋወት ጥንካሬ ማስቀጠል የአሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማርያም የቤት ሥራዎች ናቸው።

በስሑል ሽረ በኩል አምበሉ ነፃነት ገብረመድኅን በቅጣት አይሰለፍም፤ በወልዋሎ በኩል ዳዋ ሆቴሳ፣ ናትናኤል ዘለቀ፣ ዳዊት ገብሩ፣ ዮናስ ገረመው እና ቡልቻ ሹራ በጉዳት ኤፍሬም ኃይለማርያም ደግሞ በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው አንድ አንድ ድል አስመዝግበዋል። በአጠቃላይ አራት ጎሎች ሲቆጠሩ ሁለቱም ቡድኖች ሁለት ሁለት አስቆጥረዋል (የተሰረዘው 2012 ጨዋታ አልተካተተም)።