በቅርቡ በአንድ ዓመት ውል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነው የተሾሙት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የአሰልጣኝ ቡድን አባላታቸውን በአዲስ ለማዋቀር ሰለማሰባቸው ተሰምቷል።
ከያዝነው ዓመት ህዳር ወር ጀምሮ በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት እየሰሩ የቆዩት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በቅርቡ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች የሚያስመዘገቡትን ውጤት ተንተርሶ ሊታደስ በሚችል የአንድ ዓመት ውል ብሔራዊ ቡድኑን እንዲመሩ መሾማቸው ይታወሳል።
አሰልጣኙ ብሔራዊ ቡድኑን ከተረከቡት ጊዜ አንስቶ በረዳት አሰልጣኝነት አብረዋቸው ሲሰሩ የቆዩት አሰልጣኝ ተመስገን ዳና እና የግብጠባቂ አሰልጣኝ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ መሆናቸው ይታወቃል።
ሁለቱ ረዳቶቻቸው አብረዋቸው የሚቀጥሉ መሆኑ ሲረጋገጥ ሌላው አብሯቸው የነበረው የስነ ምግብ ባለሙያው ዳንኤል እና ፊዚዮቴራፒስቱ ብሩክ ደበበ ባሉበት ሲቀጥሉ በተጨማሪ የቡድኑን አቅም ለማሳደግ ሲባል የአካል ብቃት እና የቪዲዮ አናሊስት ባለሙያዎችን በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የፊታችን መጋቢት ወር አጋማሽ ከጅቡቲ እና ከግብፅ ጋር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታውን በገለልተኛ ሀገር እንደሚያደርግ ይታወቃል።