የጨዋታ ሳምንት መክፈቻ በነበረው መርሃግብር አዳማ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል።
አዳማ ከተማ በ18ኛው ሳምንት በኢትዮ ኤሌክትሪክ ሽንፈት ከቀመሱበት ስብስባቸው አምስት ለውጦችን ሲያደርጉ በዚህም አሸናፊ ኤልያስን በቻላቸው መንበሩ፣ ኃይለሚካኤል አደፍርስን በፉዓድ ኢብራሂም፣ ጋዲሳ ዋዶን በኤልያስ ለገሰ፣ ነብል ኑሪን በዳንኤል ደምሴ ፣ሱራፌል ዓወልን በስንታየሁ መንግሥቱ ተክተው ሲቀርቡ በአንፃሩ ሲዳማ ቡና 18ኛው ሳምንት ስሑል ሽረን 1ለ0 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ሁለት ለውጦችን ብቻ ሲያደርጉ በዚህም ሳሙኤል ሳሊሶ እና ሬድዋን ናስርን በመላኩ አስፋው እና በደግፌ አለሙ ተክተው ገብተዋል።
ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ የጨዋታ ብልጫ በወሰዱበት በመጀመሪያው አጋማሽ በቂ የሆኑ ግልፅ የግብ ማግባት ዕድሎችን ግን መፍጠር ሳይችሉ የቀሩበት አጋማሽ ነበር።
አዳማ ከተማዎች በአንፃራዊነት በመልሶ ማጥቃት በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚዎቻቸው ግብ ክልል በመድረስ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን የጨዋታውን የመጀመርያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራም በ6ኛው ደቂቃ ኤልያስ ለገሰ ርቀት ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ወደ ውጪ ባወጣባቸው ኳስ ማድረግ ችለዋል።
ሲዳማ ቡናዎች በአጫጭር ቅብብል ወደፊት ሄደው ጥቃት ለመሰንዘር ጥረት ሲያደርጉ ባስተዋልን አጋማሹ በ34ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ከመስመር ደስታ ደሙ ያሻማውን ኳስ ይገዙ ቦጋለ ብቻውን ሆኖ በግንባሩ ገጭቶ ከፍ ብሎ የወጣበት አጋጣሚ በአጋማሹ የተመለከትነው ወርቃማ ዕድል ነበር።
ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሲመለስ ሲዳማ ቡናዎች ከመጀመሪያው በተሻለ ጠንከር ብለው የተመለሱ ሲሆን በዚህም የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ አከታትለው ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ፈጥረዋል ፤ 50ኛው ደቂቃ ላይ በቆመ ኳስ የተፈጠረውን አጋጣሚ ይገዙ ቦጋለ በግራ መስመር ላይ ብቻውን ሆኖ አግኝቶ ወደ ግብ የመታት ለትንሽ ከፍ ያለበት እንዲሁም በ52ኛ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት ተሻምቶ ተጨራርፎ የደረሰውን ኳስ ደስታ ደሙ ከግቡ በቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ ወደ ግብ የመታት እና ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ ከፍ ብላ የመጣችበት ሌላኛው ሙከራ ጠንከር ብለው መመለሳቸው ማሳያ የሆኑ አጋጣሚዎች ነበሩ።
አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው በአጋማሹ በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በፈጣን እንቅስቃሴዎች ወደፊት እየሄዱ ጥቃት መሰንዘራቸውን እንደመጀመሪያው አጋማሽ ይቀጥሉ እንጂ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ እስከ 66ኛው ደቂቃ ድረስ መጠብቅ ግድ ሆኖባቸዋል ፤ በተጠቀሰው ደቂቃ በቅብብል ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ደርሰው በቢኒያም አይተን አማካኝነት አደገኛ የግብ ማግባት ሙከራ አድርገው ግብ ጠባቂው እንዴትም ጨርፎ ወደ ውጪ ያወጣባቸው እንዲሁም በ76ኛው ደቂቃ ላይ አሜ መሐመድ በግራ መስመር ከሳጥን ጠርዝ ላይ ሆኖ አክርሮ የመታውን ኳስ ቶማስ ኢካራ ያገደበት ሌላኛው ጠንከር ያለ ሙከራ ይታወሳል።
ጨዋታው ግቦችን የሚያስተናግድ በሚመስል መልኩ ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ቢያመራም ግብ ሳያስመለክት የሳምንቱ መክፈቻ ጨዋታ ነጥብ በማጋራት ለመጠናቀቅ ተገዷል።