ስሑል ሽረዎች በኤልያስ አህመድ ብቸኛ ግብ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲን በማሸነፍ ወሳኝ ሥስት ነጥብ አሳክተዋል።
ስሑል ሽረዎች በ18ኛው ሳምንት በሲዳማ ቡና 1ለ0 በተሸነፉበት ጨዋታ ላይ ከተጠቀሙበት ቋሚ አሰላለፍ ሦስት ለውጦችን ሲያደርጉ በዚህም ፋሲል ገ/ሚካኤልን በሞይስ ፓዎቲ፣ ነፃነት ገብረመድህንን በክፍሎም ገብረህይወት፣ ኤለክስ ኪታታን በጥዑመ ልሳን ሃ/ሚካኤል ተክተው ሲቀርቡ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲዎች በበኩላቸው በ18ኛው የጨዋታ ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ ሲጋሩ ይዘው ከቀረቡት ቋሚ አሰላለፍ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ቡልቻ ሹራን በአላዛር ሽመልስ ተክተው ቀርበዋል።
በጥሩ መነቃቃት ጅማሮውን ያደረገው የምሽቱ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ቀዳሚ ለመሆን በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎችን ብርቱ ጥረትን አድርገዋል።
በተለይ ወልዋሎዎች ገና በሁለተኛው ደቂቃ ከተከላካይ ጀርባ በተጣለ ኳስ ናትናኤል ሰለሞን ፍጥነቱን ተጠቅሞ ደርሶ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ የላካት ኳስ ግብ ጠባቂው የያዘበት አጋጣሚ ገና በማለዳው ቢጫዎቹን ቀዳሚ ለማድረግ የቀረበች አደገኛ ሙከራ ነበረች።
የኋላ ኋላ እየተቀዛቀዙ የመጡት ወልዋሎዎች ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ወደ የስሑል ሽረዎትን ጥቃት መከላከሉ ላይ ትኩረታቸውን አድርገው ቆይተዋል ፤ ከደቂቃዎች በኋላ የጨዋታ ብልጫን የወሰዱት ስሑል ሽረዎች የተሳካ የኳስ ቅብብል እያደረጉ ቶሎ ቶሎ ወደ ተቃራኒ ቡድን ሜዳ ክፍል መድረስ የቻሉ ሲሆን በ15ኛው ደቂቃ ላይ በቆመ ኳስ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ያደረገውን ሙከራ በረከት አማረ ጨርፎ ወደ ውጪ ካወጣባቸው በኋላ ሌላ ጠንካራ ሙከራ አስከትሎ ባደረጉት ጠንካራ ሙከራ ቀዳሚ መሆን ችለዋል።
በ28ኛው ደቂቃ ላይ ከቆመ ኳስ የተሻማች ኳስ ተጨራርፋ ጃዕፈር ሙደሲር ጋር ደርሳ ተጫዋቹ ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ ኤልያስ አህመድ በብልሃት ወደ ግብ በመምታት ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሮ ቀዳሚ መሆን እንዲችሉ አስችሏቸዋል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ምላሽ ለመስጠት የታተሩት ወልዋሎዎች የአጋማሹ መገባደጃ ላይ የአቻነት ግብ ፍለጋ ጫን ፈጥረው መጫወት ቢችሉም አጋማሹ ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክተን ተገባዷል።
ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ወልዋሎዎች የበላይነትን ይዘው መጫወታቸው በመቀጠል ተጋጣሚያቸው ላይ ስጋት ሲደቅኑ አምሽተዋል ፤ 70ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው ሲደርስ ወልዋሎዎች ኳስ ይዘው ሳጥን ውስጥ በሚገቡበት ቅፅበት ኪሩቤል ወንድሙ ላይ የስሑል ሽረ ተከላካዮች በሰሩት ጥፋት ፍፁም ቅጥት ምት ቢያገኙም የፊት መስመር ተጫዋቹ ናትናኤል ሰለሞን ሳይጠቀምባት ቀርቷል።
ስሑል ሽረዎች በአጋማሹ በአንፃራዊነት ነጥባቸውን ለማስጠበቅ ወደ መከላከሉ በማድላት በጥንቃቄ አጋማሹን ለማገባደድ ጥረዋል ፤ ነገርግን አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት አደጋ ለመፍጠር ባደረጉት ጥረት በተለይም በ79ኛው ደቂቃ መሐመድ አብዱለጢፍ በግራ መስመር በኩል ኳስ እየገፋ ይዞ በመግባት ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ብርሃኑ አዳሙ ብቻውን ሆኖ አግኝቶ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ በረከት አማረ በግሩም ቅልጥፍና ያመከነበት አጋጣሚ ምናልባትም ለሽረዎች መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርገው በእፎይታ ቀሪዎቹን ደቂቃዎች እንዲጨርሱ ሊያደርጋቸው የተቃረበ አስቆጪ አጋጣሚ ነበር።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ወልዋሎዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ በቁጥር በርከት ብለው ወደ ተጋጣሚዎቻቸው ግብ ክልል መግባታቸውን ቢቀጥሉም ሽረዎች በእጃቸው የገባውን መሪነት አስጠብቀው ጨዋታው 1-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የስሑል ሽረው አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት በዕቅዳቸው መሰረት በቡድን ጥረት ወሳኝ ነጥብ ማግኘታቸውን ሲያነሱ በአንፃሩ የወልዋሎው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በበኩላቸው በውጤቱ ቢከፉም በሁለተኛው ዙር ግን ደረጃቸውን ለማሻሻል ተሻሽለው ለመቅረብ እንደሚጥሩ አንስተዋል።