ሀዋሳ ከተማ በቋሚነት አዲስ አሰልጣኝ አግኝቷል

ላለፉት ወራት በጊዜያዊ አሰልጣኝ ሲመራ የቆየው ሀዋሳ ከተማ በቋሚነት አሰልጣኝ መሾሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በዘንድሮው የ2017 የውድድር ዘመን ጅማሮውን በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ እየተመራ ለአስር ሳምንታት መዝለቅ የቻለው ሀዋሳ ከተማ ከውጤት መጥፋት ጋር ተያይዞ አሰልጣኙን ማሰናበቱ ይታወቃል።

ቡድኑ አዲስ አሰልጣኝ ከመሾም ይልቅ በጊዜያዊነት በአሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ አማካኝነት ያለፉትን ዘጠኝ ሳምንታት መመራቱ ይታወሳል። ትናንት ዘለግ ላሉ ሰዓታት የቡድኑን አጠቃላይ የአንደኛውን ዙር የውድድር ዘመን ሲገመግም ያመሸው የክለቡ ቦርድ አዲስ አሰልጣኝ መቀጠር እንዳለበት ከውሳኔ ደርሷል። በዕጩነት ከቀረቡት በርከት ካሉ አሰልጣኞች ዝርዝር መካከል ቦርዱ የሥራ ልምድን መርምሮ የመጨረሻ ምርጫ ለማድረግ አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን እና አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረትን በመለየት አስቀምጦ ከብዙ ውይይት በኋላ የቀድሞ ተጫዋቹ እና አሰልጣኙን ሙሉጌታ ምሕረት እንዲሆን አብዛኛው የቦርድ አባል መርጦታል።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝነት፣ በሀዋሳ ከተማ በምክትል እንዲሁም በዋና አሰልጣኝነት ያገለገለ ሲሆን በማስከተል በሀዲያ ሆሳዕና እና ወልቂጤ ከተማ መሥራቱ ይታወቃል።