ሪፖርት | ተጠባቂው ጨዋታ በቡናማዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል

ኢትዮጵያ ቡና በአንተነህ ተፈራ ብቸኛ ጎል መቻልን 1ለ0 በመርታት ወሳኝ ሦስት ነጥብ ተጎናጽፏል።

ኢትዮጵያ ቡና ሸገር ደርቢ ላይ ከተጠቀሙት ቋሚያቸው አንድ ለውጥ ብቻ አድርገው ኤርሚያስ ሹምበዛን በአማኑኤል አድማሱ ተክተው ሲቀርቡ መቻሎች በበኩላቸው አራፊ ከመሆነቸው በፊት በሀዋሳ ከተማ 1ለ0 ሲሸነፉ ይዘው ከገቡት ቋሚ ስብስብ ሁለት ለውጦችን አድርገው በኃይሉ ግርማን በግሩም ሀጎስ አቤል ነጋሽን በአብዱ ሙታላቡ ተክተው ገብተዋል።

በዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ ፊሽካ የተጀመረው ተጠባቂው ጨዋታ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እያስመለከተ ቀጥሎ ኳስ በጥሩ አንድ ለአንድ ቅብብል በአንድ ቡድን እግር ስር እየቆየ በፈጣን ሽግግር ወደ ግብ ለመቀየር ጥረት እየተደረገበት የመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ተቆጥረዋል።

መቻሎች የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን በመፍጠር ረገድ የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል ፤ ከአጋጣሚዎቹም መካከል 25ኛው ደቂቃ ላይ ዮሐንስ መንግሥቱ ርቀት ላይ ሆኖ አክርሮ የመታው ኳስ ከግቡ አግዳሚ ለትንሽ ከፍ ብሎ ያለፈበት ፤ በ33ኛው ደቂቃ ቀኝ መስመር ላይ ሆኖ ግሩም ሀጎስ ወደ ጎል ያሻማውን ኳስ አብዱ ሙታለቡ በግንባሩ ገጭቶ አሻግሮለት በረከት ደስታ በግሩም ሁኔታ ጠንከር ያለ ኳስ ወደ ግብ መጥቶ ዳንላድ ኢብራሂም እንዴትም ያገደባቸው አጋጣሚ ቀዳሚ ሊያደርጓቸው የቀረቡ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንፃራዊነት በአጫጭር ኳስ ቅብብል የተጋጣሚያቸውን ተከላካይ መስመር ሰብረው ለመግባት እየጣሩ ተጭነው ይጫወቱ እንጂ ወደ ግብ ክልል ለመግባት የሚያደርጉት አጋጣሚ በሚቆራረጡ ኳሶች የጠራ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ አልቻሉም። አጋማሹ በእንቅስቃሴ ደረጃ ውበት እና ጠንከር ያለ ፉክክር እያስመለከተ የቀጠለ ቢሆንም  ከአጨዋወታቸው አንፃር በግልፅ ግብ ማግባት ሙከራዎች ጋመታጀብ ሳይችል ቀርቷል። እንዲሁም ቡድኖቹ ወደፊት ከመሄድ ይልቅ ኳስ ተቆጣጥረው በመጫወት የጨዋታ ብልጫ ለመውሰድ የጣሩበትን የመጀመሪያ አጋማሽ አሳልፈዋል።

ጨዋታው ከእረፍት ሲመለስ በፈጣን አጀማመር ቡናማዎቹ ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። 49ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን ሽግግር ኳሷ ዲቫይን ዋቹኩዋ ጋር ደርሳ ሲያሻግር ተጨራርፋ የቀረችውን ኳስ አማኑኤል አድማሱ ድጋሚ አግኝቶ ሳጥን ውስጥ በግራ መስመር በኩል ክፍት ሆኖ ሲጠባብቅ ለነበረው አንተነህ ተፈራ አሻግሮለት አንተነህ ኳሷን ተቆጣጥሮ በእርጋታ ወደ ግብ በመምታት መረብ ላይ አሳርፎ መሪ አድርጓቸዋል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ጨዋታው ግለቱን ጨምሮ በአንፃራዊነት ቶሎ ቶሎ ወደ ተቃራኒ ሳጥን በመድረሱ ኳሶች ተጨማሪ ግቦችን ለማስመልከት የተቃረቡ እድሎችን አስመልክቶናል። በተለይም መቻሎች የአቻነች ግብ ፍለጋ በንቃት ግብ ማስቆጠሩ ላይ እየተሳተፉ ሙከራዎችን አድርገዋል ፤ 55ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አብዱ ሙታላቡ አክርሮ ወደ ግብ ቢመታም ዳንላድ ኢብራሂም ያገደበት አጋጣሚ እንዲሁም 73ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ለአንድ ቅብብል የተገኘውን ኳስ አብዱ ሙታላቡ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ ቢመታም ለጥቂት ከፍ ብላ ያለፈችባቸው ሌላኛዋ አጋጣሚ ትጠቀሳለች።

ቡናማዎች ግቧን ካስቆጠሩ በኋላ ተረጋግተው ውጤት ማስጠበቁ ላይ ትኩረት እያደረጉ በመልሶ ማጥቃት ሌላ ጎል ፍለጋ እድሎችን መፍጠር የቻሉ ቢሆንም አስቆጪ የሚባል አጋጣሚ ሳይፈጥሩ ደቂቃው እየገፋ ሲሄድ ይበልጥ ወደ እራሳቸው ሜዳ ወረድ ብሎ መጫወቱን ምርጫቸው አድርገው ወደ መከላከሉ ያደላ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተመልክተናል።

ጨዋታው ወደመገባደጃ ሲቃረብ መቻሎች ጫን ብለው ቢያንስ ነጥብ ለመጋራት በሙሉ ኃይላቸው በቁጥር በዛ ብለው እየገቡ ግብ ለማስቆጠር መጣራቸውን ያጎልብቱ እንጂ ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው ጥንቃቄ በተሞላበት እንቅስቃሴ አንደኛውን የሜዳ ክፍላቸውን በተጫዋቾቻቸው በማጠራቸው ግብ ማስቆጠሩ እንዳሰቡት ሳይሆንላቸው ቀርቶ ጨዋታው በአንተነህ ተፈራ ብቸኛ ጎል ለኢትዮጵያ ቡና ወሳኝ ሦስት ነጥብ በማጎናጸፍ ተቋጭቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ”ወደ ጎል ስንሄድ አሁንም ተበታትነን ነው ምንሄደው ፣ ቦክስ ውስጥ የሚጨርስ አጥቂ የለንም።” የሚል አስተያየት ሲሰጡ አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬም በሰጡት አስተያየት ”አሁን ዋንጫ ነው እንደዚህ ነው የምንልበት ነገር የለም ፤እኛ እያንዳንዷን ጌም በትኩረት ያለንን ነገር እየሰጠን ቢያንስ ኢትዮጵያ ቡናን የሚመጥን ውጤት ለማምጣት ነው።” ብለዋል።