ሪፖርት | ሀዲያ ሆሳዕና ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ አሸንፏል

ነብሮቹ በሄኖክ አርፊጮ የቅጣት ምት ጎል ፈረሰኞቹን 1ለ0 አሸንፈዋል።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች በ18ኛው ሳምንት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር 3ለ3 ከተለያዩበት ቋሚ ስብስብ አምስት ለውጦችን አድርገው ፤ ያሬድ በቀለን በሳማኪ ሚኬል፣ ዳግም ንጉሤን በበረከት ወልደቾሐንስ ፣ አስጨናቂ ፀጋዬን በቃለአብ ውብሸት ፣ ጫላ ተሺታን በብሩክ በየነ ፣ ፀጋአብ ግዛውን በሰመረ ሀፍተይ ተክተው ሲገቡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ቋሚ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ በረከት ወልዴን አስወጥተው በአፈወርቅ ኃይሉ ተክተው ገብተዋል።

12፡00 ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በአምላክ ተሰማ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረሱ በኩል የተሻሉ የነበሩት ፈረሰኞቹ ገና በ2ኛው ደቂቃ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገው ፍጹም ጥላሁን ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ያደረገውን ኃይል የለሽ ሙከራ ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኬ በቀላሉ ይዞበታል።

ወደ ራሳቸው ግብ ተጠግተው መጫወትን የመረጡት ነብሮቹ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ 18ኛ ደቂቃ ላይ በየነ ባንጃ ከረጅም ርቀት ያደረገው ያደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራም የተሻለው የግብ ሙከራቸው ነበር።

የግብ ዕድሎች በብዛት አይፈጠሩበት እንጂ ጠንካራ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች 19ኛ ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። አብዱልሃፊዝ ቶፊቅ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ አማኑኤል ኤርቦ ከግብ ጠባቂው ቀድሞ በግንባር ገጭቶ ወደኋላ ሲመልሰው ፍጹም ጥላሁን በቀጥታ ወደግብ ቢመታውም የመሃል ተከላካዩ ከድር ኩሊባሊ በድንቅ ንቃት ኳሱን በግንባር በመግጨት አስወጥቶታል።

ከዕረፍት መልስ በተጫዋቾች መካከል በሚፈጠሩ አላስፈላጊ ጉሽሚያዎች የጨዋታው ግለት ቢቀጥልም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ሁለቱም ቡድኖች ደካማ ነበሩ። ሆኖም 52ኛው ደቂቃ ላይ የሀዲያው ኢዮብ ዓለማየሁ ከሻሂዱ ሙስጠፋ ተደርቦ ባገኘው ኳስ በግራ እግሩ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ በቀላሉ ይዞበታል።

ጨዋታው 61ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ጎል ተቆጥሮበታል። ፍጹም ጥላሁን ኢዮብ ዓለማየሁ ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ሄኖክ አርፊጮ በቀኝ መስመር ከረጅም ርቀት በቀጥታ በመምታት መረቡ ላይ አሳርፎት ሀዲያ ሆሳዕናን መሪ አድርጓል። ከግቧ መቆጠር በኋላም ጊዮርጊሶች ጫና ፈጥረው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም የሀዲያን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት አልፈው ጎል ለማስቆጠር ተቸግረው ጨዋታውም በሀዲያ ሆሳዕና 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጎል እስኪቆጠርባቸው ድረስ ጥሩ አፈጻጸም ቢኖራቸውም ከጎሉ በኋላ መረጋጋት እንደተሳናቸው እና የመስመር ማጥቃት እንቅስቃሴውን እንደፈለጉት እንዳልነበር ሲነገሩ የሀዲያ ሆሳዕና አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በበኩላቸው ድሉን ያገኙበት መንገድ ይበልጥ ደስተኛ እንዳደረጋቸው እና ከቆሙ ኳሶች ጎል ለማስቆጠር አቅደው እንደመጡ ያም እንደተሳካላቸው ሀሳባችን ሰጥተዋል።