ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ በደርቢው ደምቀዋል

በተጠባቂው የደርቢ ጨዋታ ቸርነት ጉግሳ ለጣና ሞገዶቹ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ እና መጠናቀቂያ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ታግዘው ዐፄዎቹን በመርታት የመጀመሪያውን ዙር በወሳኝ ድል ቋጭተዋል።

በመጨረሻ የሊግ ጨዋታቸው በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ያስተናገዱት ባህር ዳር ከተማዎች በጨዋታው ከተጠቀሙበት የመጀመሪያ 11 ተጫዋቾች ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ጂሮም ፊሊፕን አስወጥወተው ሄኖክ ይበልጣን ሲተኩ በአንፃሩ የሊጉን መሪ ኢትዮጵያ መድንን አሸንፈው ወደ ዛሬው ጨዋታው የመጡት ፋሲል ከነማዎች በበኩላቸው ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች ጃቢር ሙሉ እና ቢኒያም ላንቃሞን አስወጥተው በምትካቸው በረከት ግዛው እና ማርቲን ኪዛን በመጠቀም የዛሬውን ጨዋታ ጀምረዋል።

እጅግ ደካማ እንቅስቃሴን ባስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በ21ኛው ደቂቃ ማርቲን ኪዛ በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ የፔፕ ሰይዶን ከግብ ክልሉ መውጣት ተከትሎ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት እንዲሁም በ22ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞን ከቀኝ መስመር ያሻገራትን ኳስ ሙጂብ ቃሲም በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት በግቡ ቋሚ በኩል የወጣችበት አጋጣሚ ቀዳሚዎቹ ሙከራዎች ነበሩ።

በተጠበቀው ልክ ለመሆን በተቸገረው የሁለቱ የመጀመሪያ አጋማሽ የመጨረሻዎቹ አምስት ደቂቃዎች ግን ሁለት አደገኛ ሙከራዎችን ተመልክተናል ፤ በጣና ሞገዶቹ በኩል በ43ኛው ደቂቃ ቸርነት ጉግሳ ከሳጥን ጠርዝ ያቀበለውን ኳስ ፍፁም ዓለሙ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ ዮሀንስ ደርሶ ያዳነበት እንዲሁም በ45ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ በረጅሙ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ከፍፁም ፍትህዓለው ጋር ታግሎ በግራ እግሩ ያደረጋት ሙከራ የግቡን ቋሚ ለትማ ተመልሳበታለች።

ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሲመለስ ባህርዳሮች በሰከንዶች ልዩነት ቀዳሚ ሆነዋል ፤ በ46ኛው ደቂቃ ቸርነት ጉግሳ ከፍፁም ዓለሙ የተቀበለውን ኳስ ሳጥን ውስጥ በተረጋጋ አጨራረስ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ማድረግ ችሏል።

ነገርግን የባህር ዳር ከተማዎች መሪነት የዘለቀው ለአራት ያክል ደቂቃዎች ነበር ፤ መሳይ አገኘሁ ማርቲን ኪዛ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ ቢመታም ፔፕ ሰይዶ የመለሰበትን ኳስ በድጋሚ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ አድርጓል።

በአጋማሹ የመጀመሪያ ደቂቃዎች የነበረውን መነቃቃት ለማስቀጠል በተቸገረው አጋማሹ በ63ኛው ደቂቃ አምሳሉ ጥላሁን ከቆመ ኳስ ቀጥታ ሞክሯት ዮሀንስ ደርሶ በግሩም ሁኔታ ያዳነበት እንዲሁም በ83ኛው ደቂቃ ቸርነት ጉግሳ ከሳጥን ውጭ ባደረጋቸው ሙከራዎች በአንፃራዊነት የተሻለ ሙከራዎችን በአጋማሹ ያደረጉት ባህር ዳሮች በጭማሪ ደቂቃ ቸርነት ጉግሳ ከቆመ ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ የላካት ኳስ በጌታነህ ከበደ ተጨርፋ መረብ ላይ ማረፉን ተከትሎ የጣና ሞገዶቹ በወሳኙ የደርቢ ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ከማስተናገዳቸው ውጪ ጨዋታው መጥፎ እንዳልነበር ያነሱ ሲሆን በሁለተኛው ዙር የማጥቃት አፈፃፀማቸውን ለማሳደግ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል በአንፃሩ የባህር ዳር ከተማው አሰልጣኝ ደግዓረግ ይግዛው በበኩላቸው የመጀመሪያው አጋማሽ በዕቅዳቸው መሰረት የሄደ እንዳልነበር እና በሁለተኛው አጋማሽ ችግሮቻችን ቀርፈን ውጤት ይዘን መውጣት ችለናል ሲሉ ተደምጠዋል።