ሪፖርት | ወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አቻ ተለያይተዋል

ከ60 ደቂቃ በላይ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት የተገደዱት ወላይታ ድቻዎች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር 1-1 በሆነ ውጤት ነጥብ ተጋርተዋል።

ወላይታ ድቻ ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት መቐለ 70 እንደርታን 1ለ0 ካሸነፈበት ቋሚ አሰላለፍ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ መሳይ ሰለሞንን በያሬድ ዳርዛ ተክተው ሲገቡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በበኩላቸው በ18ኛው ሳምንት ሀዋሳ ከተማን ከረቱበት የመጀመሪያ 11 ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል።


በጥሩ ፉክክር ጅማሮውን ያደረገው የምሽቱ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በፈጣን እንቅስቃሴ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚያቸው ግብ ክልል እየደረሱ ቀዳሚ ለመሆን ጥረት ያደረጉበት ነበር።

በ8ኛው ደቂቃ ላይ ኬኔዲ ከበደ ርቀት ላይ ሆኖ አክርሮ መጥቶ ከግቡ አግዳሚ ለትንሽ ከፍ ብሎ ኢላማውን ሳትጠብቅ የቀረችው የጨዋታው ቀዳሚ ሙከራ የነበረች ቢሆንም በ14ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ታምራት በሳጥኑ ግራ መስመር በኩል ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ ኪቲካ ጅማ ወደ ግብነት ቀይሮ ንግድ ባንኮችን ቀዳሚ አድርጓቸዋል።

ግብ ካስተናገዱ በኋላ ይበልጥ ተነቃቅተው የኳስ ቁጥጥራቸውን በማሳደግ በፈጣን ሽግግር ወደ ተጋጣሚያቸው መድረስ ላይ ትኩረት ያደረጉት የጦና ንቦች በርከት ባሉ አጋጣሚዎች ወደ ግብ ክልል ቢደርሱም አጨራረስ ላይ እየተቸገሩ ቆይተው ባልጠበቁት መንገድ በ27ኛው ደቂቃ ላይ ኬኔዲ ከበደን በሁለት ቢጫ ካርድ አጥተዋል።

ቀሪውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት የተገደዱ ወላይታ ድቻዎች ምንም እንኳን የተጫዋች ጉድለት ቢኖርባቸውም የተጫዋች ቅያሪ አድርገው ጫን ብለው የአቻነት ግብ ፍለጋ በቁጥር በርከት ብለው ወደ ጨዋታው ለመመለስ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮችን ተከላካይ መስመር ሲያጨናንቁ ተመልክተናል።

በዚህም አጋማሹ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት የሚጠናቀቅ ቢመስልም በጭማሪ ደቂቃ ላይ የጦና ንቦች የአቻነት ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል።

በረጅሙ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ ፀጋዬ ብርሃኑ ተቆጣጥሮ ወደ ግብነት ቀይሮ አቻ ሆነው ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመሩ አስችሏቸዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ጨዋታው ቀጥሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በመጀመሪያው አጋማሽ ያልተጠቀሙትን የተጫዋች ጉድለትን ለመጠቀም ጫን ብለው በተደጋጋሚ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል።

በ58ኛው ደቂቃ ላይ በቅብብል የፈጠሩትን አጋጣሚ ኪቲካ ጅማ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀም ሲቀር እራሱ ኳስ ተጨራርፎ ጠንከር ያሉ ኳሶችን ወደ ግብ ቢመቱም የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች ተረባርበው ያወጡባቸው ሙከራ ዳግም መሪ ሊያደርጋቸው የቀረበ ተጠቃሽ የጎል ማግባት እንቅስቃሴ ነበር።

ወላይታዎች በአንፃሩ ከእረፍት መልስ በመልሶ ማጥቃት በተወሰኑ አጋጣሚዎች ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ይድረሱ እንጂ አብዛኛውን ጊዜ መከላከሉ ላይ ሲያሳልፉ ተመልክተናል።

ጨዋታው 55ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የንግድ ባንኩ ግብ ጠባቂ በሰራው ስህተት መነሻነት የተገኘውን ኳስ ፀጋዬ ብርሃኑ አግኝቶ ፖላክ ቾል ወደ ውጪ መውጣቱን ተከትሎ ከፍ አድርጎ ወደ ግብ ቢመታም ፈቱድን ጀማል ወደ ውጪ ያወጣባቸው ክስተት መሪነት ለመረከብ አቅርቧቸው የነበረ አጋጣሚ ነበር።

ደቂቃዎች ይበልጥ እየገፉ በሄዱ ቁጥር ንግድ ባንኮች በሙሉ ሃይላቸው መሪ ለመሆን የተጋጣሚያቸውን ግብ ክልል እየጎበኙ ቢቀጥሉም ወላይታ ድቻ መከላከሉ በጠጣር መከላከል ግባቸውን ሳያስደፍሩ ጨዋታው አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በጎዶሎ ተጫዋች ነጥብ ተጋርተው መውጣታቸው ትልቅ ውጤት መሆኑን አንስተው በውጤቱም ደስተኛ መሆናቸውን ሲገልፁ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ በአንፃሩ በርካታ የግብ አጋጣሚዎችን ፈጥረው ባለመረጋጋት በተነሳ ሳይጠቀሙ እንደቀሩና ተጋጣሚዎቻቸው ጓዶሎ ከመሆናቸውም አንፃር ማሸነፍ እንደነበረባቸው ተናግረዋል።