የመጀመርያው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጠናቀቃል። የአንደኛው ዙር መገባደጃ የሆኑት ጨዋታዎች አስመልክተን ያዘጋጀናቸው መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ አርባምንጭ ከተማ
በሁለት ነጥቦች እና በሦስት ደረጃዎች የሚበላለጡት ኤሌክትሪኮች እና አርባ ምንጭ ከተማዎች የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ መርሀ-ግብር ነው።
ከተከታታይ ሦስት ሽንፈቶች አገግመው ከሦስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦች ሰብስበው ወደ ጥሩ ብቃት የመጡት ኤሌክትሪኮች የደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ ተሻግረው የመጀመሪያው ዙር ለማገባደድ አዞዎቹን ይገጥማሉ።
ኤሌክትሪክ በቅርብ ሳምንታት ከውጤቱ ባሻገር በእንቅስቃሴ እንዲሁም በግብ ማስቆጠር ረገድ ጥሩ ለውጥ አሳይቷል። በአምስት መርሀ-ግብሮች አንድ ግብ ብቻ በማስቆጠር በከፍተኛ የግብ ድርቅ ተመቶ የነበረው ቡድኑ በቅርብ ሳምንት በተለይም በግብ ማስቆጠሩ ያሳየው ለውጥ ወደ ድል መልሶታል። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ማስቆጠሩም የለውጡ ማሳያ ነው። አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በነገው ዕለት መሻሻል ያሳየው የፊት መስመር ጥንካሬ ከማስቀጠል ባለፈ በሦስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስቆጠረው የአዞዎቹ ውጤታማ የማጥቃት ክፍል ለማቆም የመከላከል አደረጃጀታቸውን ከመቼው ጊዜ በላይ ጠንካራ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
በወጣቱ አሰልጣኝ በረከት ደሙ የሚመሩት አርባምንጭ ከተማዎች በመጀመሪያው ዙር ባደረጓቸው አስራ ስድስት ጨዋታዎች ሀያ አራት ነጥቦች በመሰብሰብ በ7ኛ ደረጃ ተቀምጠዋል። በአስገራሚ መልኩ ያስቆጠሩት(18) ሆነ የተቆጠረባቸው(18) ግብ መጠን እኩል ሆኗል።
አዞዎቹ ወሳኙ እና ሰባት ግቦች ያስቆጠረው አጥቅያቸው አሕመድ ሑሴን አጥተውም ጭምር በቀደመ የማጥቃት ጥንካርያቸው መቀጠላቸው እንደ አወንታ የሚነሳላቸው ነጥብ ቢሆንም በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሀ-ግብሮች አምስት ግቦች ያስተናገደው እና በዓመቱ በጨዋታ በአማካይ 1.12 የተመዘገበበት የመከላከል አደረጃጀት የማስተካከል የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።
ቡድኑ በነገው ዕለት ሙሉ ነጥብ ማግኘት ከቻለ ሦስት ደረጃዎች አሻሽሎ የመጀመሪያውን ዙር የማጠናቀቅ ዕድል በእጁ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በብዙ ረገድ ተገማች ባይሆንም የነገው መርሀ-ግብር ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች በተናጠል 2 እና 2.3 ግቦች በአማካይ ያስቆጠሩ ቡድኖች የሚገናኙበት ፍልምያ በመሆኑ በግቦች የታጀበ ይሆናል ብለን እንድንገምት የሚያደርግ ነው።
በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል አብዱላሂ አላዩ እና በፍቃዱ አስረሳህኝ አሁንም ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በአርባምንጭ ከተማ በኩል ሳሙኤል አስፈሪ ፣አበበ ጥላሁን፣ አሸናፊ ተገኝ፣ አህመድ ሁሴን እና ካሌብ በየነ በጉዳት ምክንያት የማያሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው። በ18ኛው የጨዋታ ሳምንት በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው አሸናፊ ፊዳ አራት ጨዋታዎች በመታገዱ የነገውን ጨዋታ ጨምሮ ቀጣይ ጨዋታዎች ያመልጡታል እንዲሁም ይሁን እንደሻው በአምስት ቢጫ ካርዶች በቅጣት በነገው ጨዋታ አይኖርም። በህመም ምክንያት ሁለት ጨዋታዎች ላይ በቋሚነት መሰለፍ ያልቻለው በፍቅር ግዛው ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠናል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 16 ጊዜ ተገናኝተዋል። ኤሌክትሪክ 6 ሲያሸንፍ አርባምንጭ 5 አሸንፏል፤ አምስት ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ 20 አርባምንጭ ከተማ ደግሞ 19 ማስቆጠር ችለዋል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን
ድሬዳዋ ከተማዎች ከአደጋው ክልል ይበልጥ ለመራቅ ኢትዮጵያ መድኖች ደግሞ የነጥብ ልዩነቱን አስፍቶ ዙሩ ለማጠናቀቅ የሚያደርጉት ፍልሚያ የመጀመርያው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ነው።
ውድድሩ ወደ አዳማ ከተማ ከተዘዋወረ ወዲህ ድል ማድረግ ያልቻሉት ድሬዳዋ ከተማዎች ላለፉት ሰባት ጨዋታዎች ከድል መራራቃቸው ተከትሎ በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ አደጋው ክልል ቀርበዋል።
በሀያ ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ብርቱካናማዎቹ ምንም እንኳን በወራጅ ቀጠና ካለው ቡድን በአራት ነጥቦች ልቀው ቢቀመጡም ከአደጋው ክልል ለመራቅ እና የነጥብ ልዩነቱን ለማስፋት ከነገው ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት ግድ ይላቸዋል። ከወልዋሎ ጋር ነጥብ የተጋራበት የመጨረሻ ጨዋታ ጨምሮ በውድድር ዓመቱ ስምንት የአቻ ውጤቶች ማስመዝገብ የቻለው ቡድኑ ካደረጋቸው አስራ ስድስት መርሀ-ግብሮች ግማሹ በነጥብ መጋራት የተገባደዱ ናቸው፤ በተቀሩት ጨዋታዎች ደግሞ አራት አራት በእኩሌታ የድል እና የሽንፈት ውጤቶች ሲሆኑ በተለይም በቅርብ ሳምንታት ቡድኑ ከድል ጋር ለመራራቁ እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ የማጥቃት ክፍሉ መዳከም ነው።
በመጀመርያዎቹ ዘጠኝ የሊግ መርሀ-ግብሮች አስራ አራት ግቦች በማስቆጠር ጥሩ አጀማመር አድርገው የነበሩት ብርቱካናማዎቹ በመጨረሻዎቹ ሰባት ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻሉት የግብ መጠን ግን ሦስት ብቻ ነው። ቁጥሩ እንደሚያሳየው በግብ ማስቆጠሩ ረገድ የታየው ማሽቆልቆል ከቡድኑ ውጤት መጥፋት ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት አለው። በነገው ዕለትም የሊጉ ቁንጮ የሆነ የመከላከል አደረጃጀት ያለው መድን እንደመግጠማቸው ከቡድኑ በብዙ ረገድ የተሻሻለ ብቃት ይጠበቃል።
ከተከታታይ ስድስት ድሎች በኋላ በፋሲል ከነማ ሽንፈት ያስተናገዱት እና የመጀመርያውን ዙር በመሪነቱ ማጠናቀቃቸው ያረጋገጡት ኢትዮጵያ መድኖች በ2ኛ ደረጃ ላይ ካለው ሀዲያ ሆሳዕና ያላቸው የሁለት ነጥቦች ልዩነት ወደ አምስት ከፍ አድርጎ የመጀመርያውን ዙር በምቾት ለማገባደድ ድል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ኢትዮጵያ መድን ከአስራ ሁለት ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ጉዞ በኋላ ሽንፈት ባስተናገደበት የመጨረሻው መርሀ-ግብር ላይ ጥሩ አጀማመር
ከማድረግ ባለፈ ጫና ለመፍጠር በታተረባቸው አጋጣሚዎችም ራሱን ለጥቃት አላጋለጠም ነበር።
ቡድኑ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ግብ ማስተናገድ ቢችልም የመከላከል አደረጃጀቱ አሁንም የሊጉ ጠንካራው ጥምረት መሆኑ መስካሪ አያሻውም።
ሆኖም በግብ ማስቆጠሩ ረገድ በመጨረሻው ጨዋታ ጨምሮ ባለፉት አራት መርሀ-ግብሮች የታየው መጠነኛ መፋዘዝ በነገው ዕለት ሊቀረፍ የሚገባው ጉዳይ ነው። መድኖች በሦስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ካስቆጠሩባቸው መርሀ ግብሮች በኋላ በተከናወኑ ሦስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ማስቆጠራቸውም አንዱ ማሳያ ነው።
ውጤታማ የመጀመርያ ዙር ያሳለፉት እና የተመዘገበው ውጤት ከዕቅዳቸው በላይ እንደሆነ የገለፁት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በነገው ዕለት ባለፉት ጨዋታዎች የታየው የጋለ የቡድን መንፈስ ማስቀጠል እንዲሁም የፊት መስመሩ ውጤታማነት ከፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ያለው መሐመድኑር ናስር በጉዳት አላዛር ማረነ ደግሞ በቅጣት ምክንያት አይሰለፉም። በነገው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኖች የረመዳን የሱፍ እና አብዲሳ ጀማልን አገልግሎት አያገኙም።በአንፃሩ ዮሀንስ ሴጌቦ ከጉዳቱ አገግሞ በነገው የጨዋታ ዕለት ስብስብ እንደሚካተት ይጠበቃል።
ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም 8 ጊዜ ሲገናኙ ሁለቱም በተመሳሳይ በ 3 ጨዋታዎች ድል አድርገዋል፤ የተቀሩት 2 ግንኙነቶች ደግሞ በነጥብ መጋራት የተደመደሙ ነበሩ ፤ በጨዋታዎቹ መድን 12 ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 7 ግቦችን አስቆጥረዋል።