ከባለፉት አራት ዓመታት አንጻር ዘንድሮ የቀጥታ ስርጭት ሽፋኑ የቀነሰው ሱፐር ስፖርት ዳግም መቼ የሊጉን ጨዋታዎች ለማስተላለፍ ይከሰታል? ስትል ሶከር ኢትዮጵያ ማጣራት አድርጋለች።
የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንደኛው ዙር ሊገባደድ የዛሬ ሁለት የመጨረሻ ጨዋታዎችን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። ላለፉት ዓመታት የሊጉን ጨዋታዎች የቀጥታ የምስል ስርጭት ባለ መብት ሆኖ ጨዋታዎችን ሲያስተላለፍ የቆየው ሱፐር ስፖርት (ዲ ኤስ ቲቪ) የውል ዘመኑ ዘንድሮ የሚጠናቀቅ ይሆናል።
ከባለፉት አራት ዓመታት አንፃር ሲታይ ዘንድሮ ከተጠበቀው በታች የቀጥታ ስርጭቱ የቀነሰው ሱፐር ስፖርት በዚህ ዓመት ያስተላለፋቸው ጨዋታዎች ከአራት ሳምንታት አይበልጥም። የመጨረሻ የአንደኛው ዙር መገባደጃ 18ኛ እና 19ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ቀጥታ ሽፋን የሰጠው ሱፐር ስፖርት ዳግም መቼ ይመለሳል? ስትል ሶከር ኢትዮጵያ ማጣራት አድርጋለች።
ከአስራ ሰባት ቀን ዕረፍት በኋላ ሊጉ በሁለተኛው ዙር ሲመለስ ዲ ኤስ ቲቪ የ20ኛ፣ 21ኛ እና 22ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን የቀጥታ ስርጭት ሽፋን የማይሰጥ ሲሆን በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ምክንያት ከመቋረጥ በኋላ ሊጉ ወደ ሀዋሳ ከተማ ሲመለስ ዲኤስ ቲቪ በሀዋሰ የሚኖሩ ጨዋታዎችን እንደሚያስተላለፍ አውቀናል።
ሆኖም የቀጥታ ስርጭት ባለ መብቱ ተቋም በሀዋሳ ሁሉንም ጨዋታዎች ወይስ የተመረጡ ጨዋታዎች ያስተላልፋል የሚለውን ለማወቅ ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። በሀዋሳ ውድድሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ሱፐር ስፖርት በድጋሚ ወደ ወደ አዳማ በመጓዝ የመጨረሻዎቹን የመዝጊያ ጨዋታዎችን እንደሚያስተላለፍ ግን እርግጥ ሆኗል።
በአክሲዮን ማኅበሩ እና በሱፐር ስፖርት መካከል ባለው ውል መሠረት በዚህ ዓመት መተላለፍ ከሚገባቸው የስምንት ሳምንት ጨዋታዎች መካከል አራት ሳምንቱ ሲተላለፍ ቀሪ አራት ሳምንት ጨዋታዎች እንደሚቀሩ ይታወቃል።