ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአቤል ሀብታሙ እና ኢዮብ ገብረማርያም ግቦች አርባ ምንጭ ከተማን 2ለ1 በማሸነፍ የመጀመርያውን ዙር በ7ኛ ደረጃነት አጠናቋል።
አርባምንጭ ከተማዎች ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር አቻ ከተለያየው ቋሚ አሰላለፍ ፋሪስ አለዊ ፣ አሸናፊ ፊዳ ፣ ይሁን እንደሻው እና ቻርለስ ሪባኑን አሳርፈው በኢድሪስ ኦጎዶጆ፣ ተመስገን ኢሳይያስ፣ መሪሁን መስቀለ እና በፍቅር ግዛው ተክተው ሲገቡ ኤሌክትሪኮች ግን አዳማ ከተማ ላይ ድል ካደረገው ቋሚ ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ጨዋታው ገብተዋል።
ጠንካራ የሚባል ፉክክር የታየበት የመጀመርያው አጋማሽ በሙከራዎች የታጀበ ነበር። በአጋማሹ ዕድሎች በመፍጠርም ሆነ በኳስ ቁጥጥር ረገድ የተሻሉ የነበሩት ኤሌክትሪኮች መሪ ለመሆን የፈጀባቸው ደቂቃም ሁለት ብቻ ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከሽመክት ጉግሳ የተሻገረችውን ኳስ ተጠቅሞ ከመታት በኋላ ግብ ጠባቂው ጨርፏት በግቡ አፋፍ የነበረው አቤል ሀብታሙ ያስቆጠራት ኳስም ኤሌክትሪክን መሪ ያደረገች ግብ ነች።
ከግቡ በኋላ ጨዋታው ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ ቢያስመለክትም ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የተሻሉ የነበሩት ግን ኤሌክትሪኮች ናቸው። በአጋማሹ አምስት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ያደረገው ቡድኑ ሽመክት ጉግሳ አሻምቷት ከግቡ ፊት ለፊት ብቻው የነበረው ሀብታሙ ሽዋለም መቷት ግብ ጠባቂው ባወጣት እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ባደረጋት ሙከራ ተጨማሪ ግቦች ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርግ አመርቂ የሚባል የማጥቃት አጨዋወት ያልነበራቸው አርባምንጭ ከተማዎችም በሁለት አጋጣሚዎች ግብ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። ቡታቃ ሸመና ከቆመ ኳስ በቀጥታ ያደረጋት ሙከራ እና ፍቃዱ መኮንን በግሉ ጥረት ተከላካዮች አልፎ መቷት ግብ ጠባቂው የመለሳት ኳስም የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ናቸው።
ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ባደረጋት ሙከራ የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው የጨዋታው ምዕራፍ የተሻለ ተመጣጣኝ ፉክክር የተደረገበት ነበር። በተሻለ የጨዋታ ፍላጎት የጀመሩት አዞዎቹ አጋማሹ በተጀመረ በአራት ደቂቃዎች ውስጥም አቻ የምታደርጋቸው ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ከማዕዝን ምት ተሻምታ የኤሌክትሪክ ተጫዋቾች በግንባር የመለሷትን ኳስ አግኝቶ አንዱዓለም አስናቀ ከሳጥን ውጭ በግሩም ሁኔታ ያስቆጠራት ኳስም አዞዎቹን አቻ ማድረግ የቻለች ግብ ነች።
ጥራት ባላቸው የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ከመጀመርያው አጋማሽ ያነሱ ዕድሎች የተፈጠረበት ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ ጥቂት ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። በአዞዎቹ በኩል መሪሁን መስቀለ ከቀኝ መስመር አሻምቷት በፍቅር ግዛው በግንባሩ ያደረጋት ሙከራ፤ በኤሌክትሪክ በኩልም ሽመክት ጉግሳ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ የተገኘችው ቅጣት ምት በቀጥታ መቷት ኢድሪስ ኢጎዶጆ የመለሳት ኳስ ይጠቀሳሉ።
ጨዋታው ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች በተቀዛቀዘ ሁኔታ ከቀጠለ በኋላ ግን በ 80ኛው ደቂቃ ኤሌክትሪኮች መሪ የምታደርቸው ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ያሬድ የማነ ከግራ መስመር አሻምቷት አካሉ አትሞ ከጨረፋት በኋላ ግብ ጠባቂው ሲያድናት ኢዮብ ገብረማርያም የተመለሰችውን ኳስ ተጠቅሞ ያስቆጠራት ግብም ኤሌክትሪክን መሪ ማድረግ ችላለች።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ያልተደረገ ሲሆን ጨዋታው በኤሌክትሪክ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ቡድኑ ደረጃውን ወደ 7ኛ ከፍ አድርጎ የመጀመርያውን ዙር አጠናቋል።
ከጨዋታው በኃላ በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ
በረከት ደሙ ጨዋታው ጥሩ እንደነበር ገልፀው ባላቸው በጠባብ አማራጭ ወደ ጨዋታው እንደገቡ ተናግረው በተከላካይ መስመር ላይ አራት ተጫዋቾች ብቻ እንዳላቸው የጠቀሱት አሰልጣኙ የተከላካይ ክፍሉ ልምድ በሌላቸው ተጫዋቾች መዋቀሩ ሊፈተን እንደሚችል ቀድመው መገመታቸውንም ገልፀዋል። አሰልጣኙ ጨምረው
“በመጀመርያው ደቂቃ የሠራነው ስህተት እና የልምድ ማነስ ዋጋ አስከፍሎናል” ካሉ በኋላ ተጫዋቾቻቸው የሚችሉትን እንዳደረጉ ገልፀዋል። የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው ጨዋታው ጥሩ እንደነበር ገልፀው በተለይም በመጀመርያው አጋማሽ ላይ ከዚህም በላይ ማስቆጠር ይችሉ እንደነበር ተናግረዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም በእቅዳቸው መሰረት ጥሩ ነገር እንዳደረጉ ገልፀው የመከላከል አደረጃጀቱ ላይ የትኩረት ማነስ እንደነበርም አንስተዋል። በስተመጨረሻም ከጨዋታው ክብደት አንፃር የተመዘገበው ውጤት ጥሩ መሆኑ በመጥቀስ በተጫዋቾቻቸው ብቃት እንደኮሩ ተናግረዋል።