ዮሴፍ ታረቀኝ አዲስ ክለብ ለማግኘት ተቃርቧል

በዘንድሮው የውድድር ዓመት ሀዋሳ ከተማን ተቀላቅሎ የቆየው ዮሴፍ ታረቀኝ ወደ ሌላኛው የሊጉ ክለብ የሚያደርገውን ዝውውር ለማጠናቀቅ ከጫፍ ደርሷል።

የ2015 የዓመቱ ወጣት ኮከብ ተጫዋች በመባል የተመረጠው ዮሴፍ ታረቀኝ ከአዳማ ከተማ ጋር በመለያየት በያዝነው ዓመት በአሰልጣይ ዘርዓይ ሙሉ ይመራ የነበረወን ሀዋሳ ከተማን ተቀላቅሎ ቡድኑን ለስምንት ሳምንታት ማገልገሉ ይታወሳል።

በመሐል ከክለቡ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ዮሴፍ ያለፉትን ሁለት ወራት ከጨዋታ እንቅስቃሴ ጠፍቶ ቆይቶ ነበር። በሀዋሳ ከተማ እና በተጫዋቹ መካከል በተደረገ ውይይት ዮሴፍ ወደ ፈለገበት ክለብ እንዲሄድ ከስምምነት መድረሳቸውን ተከትሎ ከሰሞኑ ስሙ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ሲነሳ ቆይቶ በስተመጨረሻም የዮሴፍ ማረፊያ ክለብ መቻል ለመሆን ተቃርቧል።

በተጫዋቹ እና በመቻል በኩል ትናንት በተደረገው ድርድር በአብዛኞቹ ነገሮች መግባባት ላይ ተደርሷል። አንዳንድ ማለቅ ያለባቸው የወረቅት ሥራዎች ከተጠናቀቁ በኋላ ዮሴፍ ለመቻል ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር የሚያቆየውን ፊርማውን ያኖራል ተብሎ ይጠበቃል።

የእግርኳስ ሕይወቱን በአዳማ ከተማ ከተስፋ ቡድን እስከ ዋናው ቡድን ድረስ መጫወት የቻለው ዮሴፍ ከሦስት ወራት የሀዋሳ ከተማ ቆይታ በኋላ ለእርሱ የሊጉ ሦስተኛ ክለብ ወደ ሆነው መቻል የሚቀላቀል ይሆናል።

በተያያዘ ዜና መቻል በአንደኛው ዙር በተለይ የማጥቃት አቅሙ ላይ የነበረበትን መሳሳት ለማጠናከር የውጭ ሀገር አጥቂዎችን ለማምጣት እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ ሰምተናል።