ዐበይት ጉዳዮች 1 | የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን !

ዓርብ መስከረም 10 አሃዱ ብሎ ለ143 ቀናት ከተካሄደ በኋላ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የተጋመሰው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በርከት ያሉ ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮችን በአንደኛው ዙር አስተናግዷል። ተስፈኛ ክዋክብት፣ ድንቅ ግቦች፣ ተከታታይ ሽንፈቶች፣ ያልተጠበቁ ውድቀቶች እና በሌሎች ለውይይት በሚበቁ ጉዳዮች ታጅቦ በተካሄደው ዙር ትኩረት የሳቡ ነጥቦች ብለን የመረጥናቸውን በተከታታይ ወደ እናንተ እናደርሳለን። የዛሬን ከሊጉ መሪ እንጀምር!

ኢትዮጵያ መድኖች ከመጀመሪያዎቹ አራት ጨዋታዎች ሦስት ነጥቦች ብቻ አስመዝግበው ሊጉን ከጀመሩ በኋላ በቡድኑ ብቃት ያልተጠራጠረ አልነበረም። ሆኖም ከአምስተኛው ሳምንት በኋላ ታሪክ ተቀይሮ አስራ ሰባት ክለቦችን ባሳተፈው የሀገሪቱ ትልቁ የእግርኳስ ድግስ የመጀመሪያ መንፈቅ ላይ እንደ ገብረመድኅን ኃይሌው መድን ስኬታማ ጊዜ ያሳለፈ ክለብ አልነበረም።

ወልዋሎን እስካሸነፉበት የአምስተኛው ሳምንት መርሐግብር ድረስ ድል ሳያደርጉ እና ግብ ሳያስቆጥሩ ከቆዩ በኋላ በድሎች የታጀቡ ሳምንታትን ያሳለፉት መድኖች ካስመዘገቡት ውጤት በተጨማሪ በተጫዋቾቹ ያለው መንፈስ ቡድኑ ምን ያህል ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ እንደሆነ ማሳያዎች ናቸው። በሊግ ውድድሮች በተለይም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቦታህን ማስከበር ትልቁ ፈተና ነው፤ በ17 ሳምንታት ቆይታ ስለ ዋንጫ እና ተያያዥ ጉዳዮች ማንሳት ከባድ ቢሆንም በአምስት ነጥቦች ልዩነት ሊጉን ያጋመሰው መድን ለ23 ዓመታት የዘለቀ የዋንጫ ጥማቱን ለማስታገስ እና በክለቡ ታሪክ የመጀመሪያውን የሊግ ክብር ለማንሳት በሁለተኛው ዙር ከባድ ግዳጅ ይጠብቀዋል።

የቡድኑ ውጤታማነት ምስጢር?

ከአስከፊው የባለፈው ዓመት አጀማመር በኋላ በ2016 የውድድር ዓመት አጋማሽ ቡድኑን በአዲስ መልክ በሚባል ደረጃ በማዋቀር ወደ ውጤት ጎዳና የመለሱት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ የተከተሉት ሚዛናዊው አጨዋወት የቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎን ነው። ከዚህ ቀደም ከሚታወቁበት ቀጥተኛ አጨዋወት በብዙ መልክ የተለወጠ እና ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ የሚሰጥ ቡድን የገነቡት አሰልጣኙ በመከላከሉ እና በማጥቃቱ ረገድ ያላቸው ጥንካሬ ተመጣጣኝ ነው። በሚሊዮን ሰለሞን የሚመራው እና በሊጉ ጥቂት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍል በ17 ጨዋታዎች ያስተናገዳቸው ግቦች 5 ብቻ ናቸው። በወጣት ተጫዋቾች የተገነባው የፊት መስመርም ከሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጥሪ መቻል በሁለት ግቦች አንሶ በሁለተኛ ደረጃነት ተቀምጧል። በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ውጤታማ አፈጻጸም የነበራቸው እና ዳግም የተወለዱት ሀይደር ሸረፋ እና ዳዊት ተፈራ እንዲሁም ዘንድሮም በጥሩ ብቃቱ የዘለቀው ወገኔ ገዛኸኝ እና በዘጠኝ ጨዋታዎች ተሰልፎ ከቡድኑ ጋር የተለያየው ጋቶች ፓኖም ደግሞ የቡድኑ ሚዛን በመጠበቅ ረገድ ትልቅ ድርሻ ተወጥተዋል።

ልምድ ያላቸው እና ወጣቶችን በማቀናጀት ጥሩ ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ከብሔራዊ ቡድኑ ኃላፊነት በኋላ ወደ ክለቡ ብቻ ማተኮራቸውም በውጤቱ ላይ የራሱ አስተዋጽኦ አለው።