በሉሲዎቹ ዓለቃ አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ የቅጥር ሁኔታ ዙርያ ፌዴሬሽኑ ማብራሪያ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በ2026 የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከዩጋንዳ ጋር ለሚያደርጋቸው ጨዋታዎች እያደረገ የሚገኘውን ዝግጅት አስመልክቶ ዛሬ በፌዴሬሽኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።
በስፍራው ተገኝተው ገለፃ የሰጡት የፌዴሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን በአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ የቅጥር ሁኔታ ዙርያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ዋና ስራ አስፈፃሚው በንግግራቸው
“ያለፉት አንድ ዓመት የዋናው የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አልነበረው። ይሄም የሆነበት ምንም ዓይነት ውድድሮች አልነበሩም። እንዲሁም ፌዴሬሽኑ ቀጣይ አሰልጣኝ ማን ይሁን የሚለውን በጥንቃቄ እየተመለከተ ከመሆኑ አንፃር ነበር። በዚህ መሠረት የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ባደረገው ስብሰባ አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድን ለሁለት ዓመት የኢትዮጵያ የሴቶች ዋናው ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙ ይታወቃል።”
” በውሉ ላይ የአሰልጣኙ(የፌዴሬሽኑ) ግዴታ ምድነው የሚለው አሰልጣኝ ዮሴፍ ለ2026 የአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ ግዴታ ተቀምጧል። ከዚህ በተጨማሪ በዓለም ዋንጫ የሴቶች ማጣሪያ ላይም የተሻለ ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድን መፍጠር ወይም ደግሞ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መፍጠር የሚችል አሰልጣኝ እንዲሆን በግዴታነት ተቀምጧል።”
” የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ደግሞ ለአሰልጣኙ ሙሉ የስራ ነፃነት ከመስጠት ጀምሮ አስፈላጊውን ወርሃዊ ክፍያ የመክፈል ግዴታ አለበት በዚህም መሠረት የተጣራ ሰማንያ ሺህ ብር ወርሃዊ ደሞዝ ይከፍላል። የተሻለ አፈፃፀም ካለው ደግሞ ውሉ እየተሻሻለ ሊታደስ የሚችልበት አግባብ ይኖራል” ብለዋል።”
አሰልጣኙ ዮሴፍ ገብረወልድ በበኩላቸው ከአርባምንጭ ከተማ ጋር የነበራቸውን ውል ማቋረጣቸውን አያይዘው ገልፀዋል።